መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 21

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ያህዌ ሆይ፣ ንጉሥ በኃይልህ ደስ ይለዋል! በምትሰጠውም ድል እጅግ ሐሤት ያደርጋል፡፡
2የልቡን መሻት ሰጠኸው፤ የለመንህንም አልከለከልኸውም፡፡ ሴላ
3ብዙ በረከት ሰጠኸው፤ በራሱ ላይ የንጹሕ ወርቅ ዘውድ አደረግህለት፡፡
4ሕይወትን ለመነህ አንተም ረጅም ዘመንን ለዘላለም ሰጠኸው
5ከሰጠኸው ድል የተነሣ ክብሩ እጅግ በዛ ክብርንና ሞገስንም አጐናጸፍኸው፡፡
6ዘላለማዊ በረከት ሰጠኸው በፊትህ ባለው ፍስሐም ደስ አሰኘኸው፡፡
7ንጉሡ በያህዌ ተማምኖአልና ከልዑል ታማኝነት የተነሣ ከቶውንም አይናወጥም፡፡
8እጅህ ጠላቶችህን ትይዛቸዋለች ቀኝ እጅህም የሚጠሉህን ሁሉ ታገኛቸዋለች፡፡
9በቁጣህ ቀን እሳት በሚንቀለቀልበት ምድጃ ታቃጥላቸዋለህ፤ ያህዌ በመዓቱ ይፈጃቸዋል፤ እሳትም ይበላቸዋል፡፡
10ትውልዳቸውን ከምድር ላይ ታጠፋለህ ዘራቸውንም ከሰዎች መካከል ለይተህ ትደመስሳለህ፡፡
11በአንተ ላይ ክፋት ቢያስቡም፣ ሤራ ቢያውጠነጥኑም፣ አይሳካላቸውም፡፡
12በመጡበት ትመልሳቸዋለህና ቀስትህንም በእነርሱ ላይ ታነጣጥራለህ፡፡
13ያህዌ ሆይ፣ በብርታትህ ከፍ ከፍ በል እኛም ኃይልህን እንዘምራለን፤ እንወድሳለንም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።