1ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይ ጠፈርም የእጁን ሥራ ያውጃል።
2አንዱ ቀን ለሌላው ቀን ቃል ይናገራል፤ አንዱም ሌሊት ለሌላው ሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል፡፡
3ንግግር የለም፤ ቃልም የለም፤ ድምፃቸውም አልተሰማም፡፡
4ያም ሆኖ ቃላቸው ወደ ምድር ሁሉ ወጣ፣ ንግግራቸውም ወደ ዓለም ዳርቻ ወጣ፡፡ በመካከላቸውም ለፀሐይ ድንኳኑን ተከለ
5ፀሐይ ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ ይወጣል ወደ ግቡም እንደሚሮጥ ብርቱ ሰው ደስ ይለዋል፡፡
6ፀሐይ ከአንዱ አድማስ ሰማይን አቋርጦ ወደ ሌላው አድማስ ይወጣል፤ ከሙቀቱም የሚሰወር የለም፡፡
7የያህዌ ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን መልሶ ያለመልማል፤ የያህዌ ምስክር የታመነ ነው፤ ዐላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።
8የያህዌ ሕግ ትክክል ነው፤ ልብን ደስ ያሰኛል፡፡ የያህዌ ትእዛዝ ንጹሕ ነው፤ ዐይንንም ያበራል፡፡
9ያህዌን መፍራት ንጹሕ ነው፤ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡ የያህዌ ፍርድ የታመነ ነው፤ ሁለንተናውም ጽድቅ ነው፡፡
10ከወርቅ ይልቅ የከበረ፤ እጅግ ከጠራ ወርቅም የበለጠ ነው፡፡ ከማር ይልቅ ይጣፍጣል፤ ከማር ወለላም ይበልጥ ይጥማል፡፡
11እንዲሁም አገልጋይህ በእርሱ ይመከራል፤ ሕግህን በመጠበቁም ወሮታ አለው፡፡
12ስሕተቱን ሁሉ ማን ማስተዋል ይችላል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ፡፡
13ባርያህን ከድፍረት ኃጢአት ጠብቅ ያኔ ፍጹም እሆናለሁ ከታላቅ በደልም እነጻለሁ፡፡
14ዐለቴና አዳኜ ያህዌ ሆይ፣ የአፌ ቃልና የልቤም ሐሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን፡፡