መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 18

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ጉልበት የሆንኸኝ ያህዌ እወድሃለሁ፡፡
2ያህዌ ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፡፡ እርሱ አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ፣ ጋሻዬ፣ የድነቴ ቀንድና ዐምባዬ ነው፡፡
3ምስጋና የሚገባውን ያህዌን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ፡፡
4የሞት ገመድ አነቀኝ፤ የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ፡፡
5የሲኦል ማሰሪያ ተጠመጠመብኝ የሞት ወጥመድም ተጠመደብኝ፡፡
6በጨነቀኝ ጊዜ ያህዌን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም ከፊቱ ደረሰ፤ ወደ ጆሮውም ገባ፡፡
7ምድር ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፤ የተራሮችም መሠረት ተናጋ፤ ጌታ እግዚአብሔር ተቆጥቶአልና ተንቀጠቀጡ፡፡
8ከአፍንጫው ጢስ፣ ከአፉም የሚባላ እሳት ወጣ፤ የፍም ነበልባል ከእርሱ ፈለቀ፡፡
9ሰማያትን ከፍቶ ወረደ፤ ከእግሮቹም በታች ድቅድቅ ጨለማ ነበረ፡፡
10በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ መጠቀ፡፡
11ጨለማን እንደ ድንኳን፣ ዝናብ አዘል ጥቁር ደመናን በዙሪያው አደረገ፡፡
12በፊቱ ካለው መብረቅ የተነሣ የበረዶ ድንጋይና የእሳት ፍም ወጣ፡፡
13ያህዌ ከሰማያት አንጐደጐደ! የልዑልም ድምፅ አስተጋባ፡፡
14ቀስቱን አስፈንጥሮ ጠላቶቹን በተናቸው፤ መብረቅ አዥጐድጉዶ አሳደዳቸው፡፡
15ያህዌ ሆይ፣ ከቁጣህ የተነሣ፣ ከአፍንጫህም እስትንፋስ የተነሣ፣ የባሕር ወለል ታዬ የዓለምም መሠረት ተገለጠ፡፡
16ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሃም ስቦ አወጣኝ፡፡
17ከኃያላን ጠላቶቼ፣ ከሚጠሉኝ ከዐቅሜ በላይ ከሆኑ ባላንጣዎቼ ታደገኝ፡፡
18በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤ ያህዌ ግን ድጋፍ ሆነኝ፡፡
19በጣም ሰፊ ወደ ሆነ ቦታ አወጣኝ፤ ወዶኛልና አዳነኝ፡፡
20ያህዌ እንደ ጽድቄ ከፍሎኛል፤ እጆቼ ንጹሕ ስለ ነበሩ ታድጐኛል፡፡
21የያህዌን መንገድ ጠብቄአለሁና፤ በዐመፅ ተነሣሥቼ ከእርሱ ዘወር አላልሁም፡፡
22ሕጐቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤ ሥርዐቱንም ከፊቴ አላራቅሁም፡፡
23በእርሱ ፊት ንጹሕ ነበርሁ፤ ከኃጢአትም ራሴን ጠብቄአለሁ፡፡
24ያህዌ እንደ ጽድቄ መጠን፤ በዐይኖቹ ፊት ንጹሕ እንደ ነበሩት እጆቼ መጠን ከፍሎኛል፡፡
25አንተ ታማኝ ለሆኑት ታማኝ ነህ እውነተኞች ለሆኑት እውነተኛ ነህ
26ለንጹሖች ንጹሕ ነህ፡፡ ለጠማሞች ግን ጠማማ ትሆንባቸዋለህ፡፡
27አንተ ትሑታንን ታድናለህ ትዕቢተኛውን ዐይን ግን ታዋርዳለህ፡፡
28አንተ መብራቴን ታበራለህ፤ አምላኬ ያህዌ ጨለማዬን ብርሃን ታደርገዋለህ፡፡
29በአንተ ጉልበት በሰራዊት እረማመዳለሁ፤ በአምላኬም ኃይል ቅጥሩን እዘላለሁ፡፡
30የእግዚአብሔር መንገድ ፍጹም ነው፤ የያህዌ ቃል የነጠረ ነው። መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ እርሱ ጋሻ ነው።
31ከእግዚአብሔር በቀር ማን አምላክ አለ? ከአምላካችንስ በቀር ዐምባ ማን ነው?
32ኅይልን የሚያስታጥቀኝ፣ መንገዴንም የሚያቃና እግዚአብሔር ነው።
33እርሱ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያጠነክራል፣ በከፍታዎችም ላይ ያቆመኛል፡፡
34እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናቸዋል የናስ ቀስቶች መሳብ እንዲችሉ ክንዶቼን ያበረታል፡፡
35የማዳን ጋሻህን ሰጠኸኝ፤ ቀኝ እጅህ ደግፎኛል፤ ሞገስህም ታላቅ አድርጐኛል፡፡
36እግሮቼ እንዳይንሸራተቱ ከበታቼ ያለውን ቦታ አሰፋህልኝ፡፡
37ጠላቶቼን አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፤ እስኪጠፉ ድረስ ወደ ኃላ አልልም፡፡
38እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቀቅኋቸው ከእግሬም ሥር ወደቁ፡፡
39አንተ ለጦርነት ኃይልን አስታጠቅኸኝ፤ በእኔ ላይ የተነሡትንም ከበታቼ አደረግህልኝ፡፡
40ጠላቴቼ ወደ ኋላ እንዲሸሹ አደረግህ የሚጠሉኝንም አጠፋኋቸው፡፡
41ለእርዳታ ጮኹ፤ ግን ማንም አላዳናቸውም ወደ ያህዌ ጮኹ፤ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም፡፡
42ነፋስ ጠርጐ እንደሚወስደው ትቢያ አደቀቅኋቸው መንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ ረጋገጥኋቸው፡፡
43ከሕዝብ ክርክር ታደገኸኝ፤ መንግሥታት ላይ መሪ አደረግኸኝ፤ የማላውቀውም ሕዝብ ያገለግለኛል፡፡
44ዝናዬን እንደ ሰሙ ታዘዙልኝ፤ ባዕዳንም በፊቴ ራሳቸውን ዝቅ አደረጉ፡፡
45ባዕዳን በፍርሃት ተዋጡ እየተንቀጠቀጡም ከምሽጋቸው ወጥተው መጡ፡፡
46ያህዌ ሕያው ነው፤ ዐለት የሆነልኝ ይባረክ የድነቴ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል፡፡
47እርሱ ጠላቶቼን ይበቀልልኛል፤ ሕዝቦችን ከእግሬ ሥር የሚያስገዛልኝም እርሱ ነው፡፡
48ከጠላቶቼም የሚታደገኝ እርሱ ነው! በእርግጥም አንተ ከተነሡብኝ በላይ ከፍ አደረግኸኝ! ከጨካኞችም አዳንኸኝ፡፡
49ያህዌ ሆይ፣ ስለዚህ ለአንተ ውዳሴ እሰጣለሁ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ፡፡
50እግዚአብሔር ለንጉሡ ታላቅ ድል ይሰጠዋል ለቀባው ለዳዊትና ለዘሮቹም ለዘላለም ታማኝነቱን ይገልጣል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።