1አምላኬና ንጉሤ ሆይ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም ከዘላለም እስከ ዘላለም እባርካለሁ፡፡
2በየቀኑ እባርክሃለሁ ስምህንም ከዘላለም እስከ ዘላለም እባርካለሁ፡፡
3ያህዌ ምስጋናው ታላቅ ነው ታላቅነቱም አይመረመርም፡፡
4አንዱ ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ ሥራህን ያስተላልፋል ድቅ ሥራህንም ያውጃል፡፡
5የክብርህን ግርማ፣ የሥራህንም አስደናቂነት አሰላስላለሁ፡፡
6ስለ ድንቅ ሥራህ ኃይል ይናገራሉ እኔም ታላቅነትህን ዐውጃለሁ፡፡
7የበጐነትህን ብዛት ያወሳሉ ስለ ጽድቅህም ይዘምራሉ፡፡
8ያህዌ ቸር ነው፤ ርኅሩኅም ነው ለቁጣ የዘገየ ምሕረቱም የበዛ ነው፡፡
9ያህዌ ለሁሉም ቸር ነው ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው፡፡
10ያህዌ ሆይ፣ ፍጥረቶችህ ሁሉ ያመሰግኑሃል ቅዱሳንህም ይባርኩሃል፡፡
11ቅዱሳንህ የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ ስለ ኃይልህምይነጋገራሉ፡፡
12የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ለሰው ልጆች ያሳውቃሉ የመንግሥቱንም ክብር ይናገራሉ፡፡
13መንግሥትህ የዘላለም መግሥት ነው ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል፡፡
14ያህዌ የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል፡፡
15የሁሉም ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል በተገቢ ጊዜ ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ፡፡
16እጅህን ትዘረጋለህ የሕያዋንን ሁሉ ፍላጐት ታረካለህ፡፡
17ያህዌ በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው፡፡
18ያህዌ ለሚጠሩት ሁሉ በእምነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው፡፡
19የሚፈሩትን ፍላጐት ይፈጽማል ጩኸታቸውንም ሰምቶ ያድናቸዋል፡፡
20ያህዌ የሚወዱትን ይጠብቃል ዐመፀኞችን ሁሉ ግን ያጠፋል፡፡
21አፌ የያህዌን ምስጋና ይናገራል የሰው ልጅ ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ቅዱስ ስሙን ይባርክ፡፡