መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 119

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት በያህዌም ሕግ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው፡፡
2ትእዛኦቹን የሚጠብቁ በሙሉ ልባቸውም የሚፈልጉት የተባረኩ ናቸው፡፡
3በመንገዱ ይሄዳሉ እንጂ ዐመፅ አያደርጉም፡፡
4ጠንቅቀን እንጠብቃት ዘንድ አንተ ሥርዐትን አዝዘሃል፡፡
5ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ ምነው መንገዴ ጽኑ በሆነልኝ ኖሮ!
6ትእዛዞችህን ሁሉ በጥንቃቄ ካስተዋልሁ እፍረት ከቶ አይደርስብኝም፡፡
7የጽድቅ ፍርድህን ስማር በቅን ልብ ምስጋና አቀርብልሃለሁ፡፡
8ሥርዐትህን እጠብቃለሁ አንተ ፈጽሞ አትተወኝ፡፡ ቤት
9ጐልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? ቃልህን በመጠበቅ ነው፡፡
10በሙሉ ልቤ እፈልግሃለሁ ከትእዛዞችህ እንድርቅ አትተወኝ፡፡
11አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ አኖራለሁ፡፡
12ያህዌ ሆይ፣ አንተ ቡሩክ ነህ ሥርዐትህን አስተምረኝ፡፡
13አንተ የገለጥኸውን የጽድቅ ሥርዐት ሁሉ በአንደበቴ እናገራለሁ፡፡
14ከብዙ ሀብት ይልቅ በኪዳንህ ሥርዐት ደስ ይለኛል፡፡
15ድንጋጌህን አሰላስላለሁ መንገድህም ላይ አተኩራለሁ፡፡
16በሥርዐትህ ደስ ይለኛል ቃልህንም አልዘነጋም፡፡ ጋሜል
17በሕይወት እንድኖርና ቃልህን እንድጠብቅ ለባርያህ መልካም አድርግ፡፡
18ከሕግህ ድንቅ ነገር እንዳይ ዐይኖቼን ክፈት፡፡
19በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ ትእዛዞችህን ከእኔ አትሰውር፡፡
20ጻድቅ ሥርዐትህን ለማወቅ ዘወትር ከመናፈቄ የተነሣ ነፍሴ እጅግ ዛለች፡፡
21ከትእዛዞችህ የሳቱትን የተረጉሙ ዕቡያንን ገሠጽህ፡፡
22ሥርዐቶችህን ጠብቄአለሁና ስድብና ውርደትን ከእኔ አርቅ፡፡
23ገዦች ተሰብስበው በእኔ ላይ ቢዶልቱም እንኳ ባርያህ ሥርዐትህን ያሰላስላል፡፡
24ትእዛዝህ ለእኔ ደስታዬ ነው መካሪየም ነው፡፡ ዳሌጥ
25ነፍሴ ከዐፈር ጋር ተጣበቀች በቃልህ ሕይወት ስጠኝ፡፡
26ስለ መንገዴ ገልጬ ነገርሁህ አንተም መልሰህልኝ ሥርዐትህን አስተምረኝ፡፡
27ድንቅ ሥራህን አሰላስል ዘንድ የድንጋጌህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፡፡
28ሐዘን በርትቶብኛል በቃልህ አበርታኝ፡፡
29የሽንገላን መንገድ ከእኔ አርቅ በቸርነትህ ሕግህን አስተምረኝ፡፡
30የእውነትን መንገድ መርጫለሁ ሕግህንም ፊት ለፊቴ አድርጌአለሁ፡፡
31ከሥርዐትህ ጋር ተጣብቄአለሁ ያህዌ ሆይ፣ ለውርደት አሳልፈህ አትስጠኝ፡፡
32ያን እንዳደርግ አንተ ልቤን አስፍተኸዋል በትእዛዞችህ መንገድ እሮጣለሁ፡፡ ሄ
33ያህዌ ሆይ፣ የሥርዐትህን መንገድ አስተምረኝ እኔም እስከ መጨረሻው እጠብቀዋለሁ፡፡
34ሕግህን እንድጠብቅ፣ በፍጹም ልቤም እንድታዘዘው ማስተዋልን ስጠኝ፡፡
35በዚያ መሄድ ደስ ይለኛልና በትእዛዞችህ መንገድ ምራኝ፡፡
36ጽድቅ ከሌለበት ጥቅም ይልቅ ልቤን ወደ ሥርዐትህ አዘንብል፡፡
37ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ በጽድቅህ ሕይወቴን አድስልኝ፡፡
38ለእኔ ለአገልጋይህና ለሚፈሩህ ሁሉ የሰጠኸውን ተስፋ ቃል ፈጽም፡፡
39ጻድቅ ፍርድህ መልካም ነውና የምፈራውን ስድብ አርቅልኝ፡፡
40እነሆ፣ ድንጋጌህን ናፈቅሁ በጽድቅህም ሕያው አድርገኝ፡፡ ዋው
41ያህዌ ሆይ፣ ዘላለማዊ ፍቅርህን ስጠኝ በተስፋ ቃልህ መሠረት አድነኝ፡፡
42በቃልህ ታምኛለሁና ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ፡፡
43ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና የእውነትን ቃል ከአፌ አታርቅ፡፡
44ከዘላለም እስከ ዘላለም ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ፡፡
45ሥርዐትህን እሻለሁና በፍጹም ነጻነት እኖራለሁ፡፡
46ትእዛዞችህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ ይህን በማድረጌም እፍረት አይሰማኝም፡፡
47አጥብቄ እወደዋለሁና በትእዛዞችህ ደስ ይለኛል፡፡
48እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዞችህ አነሣለሁ፤ ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ፡፡ ዛይ
49በዚያ ተስፋ ሰጥተኸኛልና ለባርያህ የገባኸውን ቃል አስብ፡፡
50የተስፋ ቃልህ ሕያው አድርጐኛልና ይህ በመከራዬ መጽናኛዬ ሆነ፡፡
51ትዕቢተኞች እጅግ ተሳለቁብኝ እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አላልሁም፡፡
52ያህዌ ሆይ፣ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን አሰብሁ በዚህም ተጽናናሁ፡፡
53ሕግህን ከናቁ ክፉዎች የተነሣ እጅግ ተቆጣሁ፡፡
54በእንግድነቴ አገር ሥርዐትህ መዝሙሬ ሆነ፡፡
55ያህዌ ሆይ፣ ስምህን በሌሊት አስባለሁ ሕግህንም እጠብቃለሁ፡፡
56ሥርዐትህን ጠብቄአለሁና ይህ የሁልጊዜ ልምዴ ሆነ፡፡ ሔት
57ያህዌ ዕድል ፈንታዬ ነው ቃልህን ለመታዘዝ ቆርጫለሁ፡፡
58በፍጹም ልቤ የአንተን ሞገስ እፈልጋለሁ እንደ ቃልህ ቸርነት አሳየኝ፡፡
59መንገዴን መረመርሁ አካሄዴንም ወደ ሥርዐትህ አቀናሁ፡፡
60ትእዛዝህን ለመጠበቅ ቸኮልሁ፤ አልዘገየሁም፡፡
61የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም፡፡
62ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ አንተን ለማመስገን በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ፡፡
63እኔ አንተን የሚፈሩና ሥርዐትህንም የሚጠብቁ ሁሉ ባልንጀራ ነኝ፡፡
64ያህዌ ሆይ፣ ምድር በምሕረትህ ተሞላች ሥርዐትህን አስተምረኝ፡፡ጤት
65ያህዌ ሆይ፣ እንደ ቃልህ ለአገልጋይህ መልካም አድርገሃል፡፡
66በትእዛዞችህ አምናለሁና ተገቢውን ማስተዋልና ዕውቀትን አስተምረኝ፡፡
67አንዳች ጉዳት ሳይደርስብኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ፡፡
68አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገውም መልካም ነው እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ፡፡
69እብሪተኞች በሐሰት ስሜን አጠፉ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዝህን እጠብቃለሁ፡፡
70ልባቸው የሰባና የደነደነ ነው እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል፡፡
71ሥርዐትህን እማር ዘንድ በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ፡፡
72ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍህ ሕግ ይሻለኛል፡፡ ዮድ
73እጆችህ ሠሩኝ፣ አበጃጁኝም ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ፡፡
74ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና የሚፈሩህ እኔን ዐይተው ደስ ይላቸዋል፡፡
75ያህዌ ሆይ፣ ፍርድህ እውነተኛ እንደ ሆነ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፡፡
76ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት ምሕረትህ መጽናኛዬ ይሁንልኝ፡፡
77ሕግህ ደስታዬ ነውና በሕይወት እንድኖር ራራልኝ፡፡
78በሐሰት የሚከሱኝ ትዕቢተኞች ይዋረዱ እኔ ግን ሥርዐትህን አሰላስላለሁ፡፡
79አንተን የሚፈሩህ ሥርዐቶችህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ፡፡
80እፍረት እንዳይደርስብኝ ልቤ በሥርዐትህ ያለ ነቀፋ ይሁን፡፡ ካፍ
81ነፍሴ ማዳንህን እጅግ ናፈቀች ቃልህንም ተስፋ አድርጌአለሁ፡፡
82«መቼ ታጽናናኛለህ?» እያልሁ በመጠባበቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ፡፡
83ጢስ እንደ ጠገበ የወይን ጠጅ አቁማዳ ሆኛለሁ ሥርዐትህን አልረሳሁም፡፡
84እኔ አገልጋይህ እስከ መቼ ልቆይ? በሚያሳድዱኝ ላይ የምትፈርደው መቼ ነው?
85ሕግህን የማያከብሩ፤ ትዕቢተኞች ጉድጓድ ቆፈሩልኝ፡፡
86ትእዛዞችህ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው ሰዎች ያለ ምክንያት እያሳደዱኝ ስለሆነ ርዳኝ፡፡
87ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀራቸው እኔ ግን ትእዛዞችህን ችላ አላልሁም፡፡
88ሕግህን እጠብቅ ዘንድ በዘላለማዊ ፍቅርህ ሕያው አድርገኝ፡፡ ላሜድ
89ያህዌ ሆይ፣ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡
90ታማኝነትህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሁሉ ነው ምድርን መሠረትሃት እርሷም ጸንታ ትኖራለች፡፡
91ነገሮች ሁሉ አገልጋዮችህ ስለሆኑ በሕግህ መሠረት እስከ ዛሬ ድረስ ጸንተው ይኖራሉ፡፡
92ሕግህ ደስታዬ ባይሆን ኖሮ፣ በደረሰብኝ መከራ በጠፋሁ ነበር፡፡
93በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ትእዛዞችህን ከቶ አልረሳሁም፡፡
94እኔ የአንተ ነኝ፤ እባክህ አድነኝ ሕግህንም ፈልጌአለሁ፡፡
95ክፉዎች ሊያጠፉኝ አድብተዋል እኔ ግን ሕግህን መረዳት እፈልጋለሁ፡፡
96ማንኛውም ነገር የራሱ ወሰን እንዳለው አየሁ፤ ትእዛእህ ግን እጅግ ሰፊ ነው፡፡ ሜም
97አቤቱ ሕግህን ምንኛ ወደዱሁ ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ፡፡
98ዘወትር ከእኔ ጋር በመሆኑ፣ ሕግህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ፡፡
99ሥርዐቶችህን አሰላስላለሁና ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የበለጠ ማስተዋል አለኝ፡፡
100መመሪያህን ተከትዬ ስለምሄድ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ፡፡
101ቃልህን እጠብቅ ዘንድ እግሬን ከክፉ መንገድ ከለከልሁ፡፡
102አንተው ራስህ አስተምረኸኛልና ከድንጋጌህ ዘወር አላልሁም፡፡
103ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው፡፡
104ከመመሪያህ ማስተዋል አገኘሁ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ሁሉ ጠላሁ፡፡ ኖን
105ቃልህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው፡፡
106ጻድቅ ትእዛዞችህን ለመጠበቅ በመሐላ የገባሁትን ቃል አጸናለሁ፡፡
107እጅግ ተጐድቻለሁና ያህዌ ሆይ፣ እንደ ቃል ሕያው አድርገኝ፡፡
108ያህዌ ሆይ፣ ፈቅጄ የማቀርበውን የአፌን ምስጋና መሥዋዕት ተቀበል፡፡
109ነፍሴ ዘወትር አደጋ ላይ ናት፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም፡፡
110ክፉዎች ወጥመድ ዘረጉብኝ እኔ ግን ከመመሪያህ ፈቀቅ አላልሁም፡፡
111ሕግህ የዘላለም ውርሴ ነው የልቤም ደስታ ይኸው ነው፡፡
112ትእዛዝህን እስከ መጨረሻው ለዘላለም ለመፈጸም ልቤን ወደዚያው አዘነበልሁ፡፡ ሳምኬት
113መንታ ልብ ያላቸው ወላዋዮችን ጠላሁ፤ ሕግህን ግን ወደድሁ፡፡
114አንተ ጋሻዬና መሸሸጊያ ነህ ቃልህን በተስፋ እጠብቃለሁ፡፡
115የአምላኬን ትእዛዞች እጠብቅ ዘንድ እናንት ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ራቁ
116በሕይወት እኖር ዘንድ በቃልህ ደግፈኝ ተስፋዬም መና ቀርቶ አልፈር፡፡
117ያለ ስጋት እንድኖር ደግፈህ ያዘኝ ሥርዐትህንም ዘወትር አሰላስላለሁ፡፡
118አታላዮችና የማያስተማምኑ ስለሆኑ ከሥርዐትህ የሚያፈነግጡትን ሁሉ ወዲያ አስወገድሃቸው፡፡
119የምድርን ክፉዎች ሁሉ እንደ ጥራጊ አስወገድሃቸው፡፡ ስለዚህ እኔ ትእዛዞችህን ወደድሁ፡፡
120አንተን በመፍራት ሥጋዬ ተንቀጠቀጠ ፍርድህን እፈራለሁ፡፡ ዔ
121ትክክልና መልም የሆነውን አድርጌአለሁና ለሚጨቁኑኝ አሳልፈህ አትስጠኝ፡፡
122ለባርያህ ደኅንነት ዋስትና ሁን ትዕቢተኛ እንዲረግጠኝ አትፍቀድለት፡፡
123ማዳንህንና የጽድቅ ቃልህን በመጠባበቅ ዐይኖቼ ደከሙ፡፡
124ለእኔ ለአገልጋይህ ታማኝትህን አሳይ፣ ሥርዐቶችህንም አስተምረኝ፡፡
125እኔ አገልጋይህ ነኝ፤ ሥርዐትህንም እንዳውቅ ማስተዋልን ስጠኝ፡፡
126ያህዌ ሆይ፣ ሕግህ እየተጣሰ ነውና ጊዜው አንተ የምትሠራበት ነው፡፡
127ከወርቅ፣ ከንጹሕም ወርቅ ይልቅ በእውነት ትእዛዞችህን ወደድሁ፡፡
128ስለዚህ መመሪያዎችን በጥንቃቄ ጠበቅሁ የሐሰትንም መንገድ ጠላሁ፡፡ ፌ
129ሥርዐቶችህ አስደናቂ ናቸው እኔም በሙሉ ልቤ እታዘዛቸዋለሁ፡፡
130የቃልህ ፍቺ ያበራል አላዋቂዎችን አስተዋይ ያደርጋል፡፡
131ትእዛዝህን በመናፈቄ አፌን ከፊትሁ አለከለክሁም፡፡
132ስምህን ለሚፈሩ ዘወትር እንደምታደርገው ወደ እኔ ተመልሰህ ምሕረት አድርግልኝ፡፡
133እንደ ቃልህ አካሄዴን ቀና አድርግልኝ ኃጢአት እንዲሠለጥንብኝም አትፍቀድ፡፡
134ትእዛዝህን መጠበቅ እንድችል ከሰዎች ጥቃት አድነኝ፡፡
135ፊትህ በባርያህ ላይ ያብራ ሥርዐትህንም አስተምረኝ፡፡
136ሰዎች ሕግህን ስለ ጣሱ እንባዬ እንደ ወራጅ ውሃ ፈሰሰ፡፡
137ያህዌ ሆይ፣ አንተ ጻድቅ ነህ ፍርድህም ትክክል ነው፡፡
138ሕግህ በፍጹም እውነትና ትክክል ነው፡፡
139ጠላቶቼ ቃልህን መዘንጋታቸው በጣም አበሳጨኝ፡፡
140ቃልህ እጅግ የነጠረ ነው ባርያህም ወደደው፡፡
141እኔ የማልጠቅምና የተናቅሁ ብሆን እንኳ፣ መመሪያህን አልዘነጋሁም፡፡
142ጽድቅህ ለዘላለም ትክክል ነው ሕግህም የታመነ ነው፡፡
143መከራና ስቃይ ቢደርስብኝ እንኳ አሁንም ትእዛዝህ ደስታዬ ነው፡፡
144ሥርዐትህ ለዘላለም ጻድቅ ነው በሕይወት መኖር እንድችል ማስተዋል ስጠኝ፡፡ ቆፍ
145ያህዌ ሆይ፣ በፍጹም ልቤ እጮኻለሁና መልስልኝ፤ ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ፡፡
146ወደ አንተ እጣራለሁና አድነኝ ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ፡፡
147ጐሕ ከመቅደዱ በፊት ርዳታህን በመፈለግ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ቃልህንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
148ቃልህን አሰላስል ዘንድ ሌሊቱን ሙሉ ዐይኔ ሳይከደን ያድራል፡፡
149እንደ ቸርነትህ መጠን ድምፄን ስማ ያህዌ ሆይ፣ በትእዛዝህ መሠረት ሕይወቴን ጠብቅ፡፡
150የሚያሳድዱኝ ወደ እኔ ቀርበዋል ከሕግህ ግን ርቀዋል፡፡
151ያህዌ ሆይ፣ አንተ ቅርብ ነህ መመሪያዎችህም የታመኑ ናቸው፡፡
152ለዘላለም እንደ መሠረትሃቸው ጥንት ከሥርዐትህ ተምሬአለሁ፡፡ ሬስ
153ሕግህን አልረሳሁምና መከራዬን ተመልከት አድነኝም፡፡
154ተሟገትልኝ አድነኝም እንደ ተስፋ ቃልህም ጠብቀኝ፡፡
155ሥርዐትህን ስለማይፈልጉ ድነት ከክፉዎች የራቀ ነው፡፡
156ያህዌ ሆይ፣ ርኅራኄህ ታላቅ ነው፤ እንደ ሁልጊዜው በሕይወት ጠብቀኝ፡፡
157አሳዳጆቼና ጠላቶቼ በዝተዋል፤ እኔ ግን ከሥርዐትህ ፈቀቅ አላልሁም፡፡
158ቃህን አልጠበቁም ከዳተኞችን ዐይቼ ተጸየፍኃቸው፡፡
159መመሪያህን እንዴት እንደምወድ እይ፤ ያህዌ ሆይ፣ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፡፡
160የቃልህ ሥረ መሠረት እውነት ነው ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው፡፡ ሳን
161መመሪያህን እንዴት እንደምወድ እይ፤ ያህዌ ሆይ፣ እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፡፡
162የቃልህ ሥረ መሠረት እውነት ነው ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው፡፡ ሳን
163ሐሰትን እጠላለሁ፤ እጸየፋለሁ ሕግህን ግን ወደድሁ፡፡
164ጻድቅ ስለሆነው ሕግህ በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሃለሁ፡፡
165ሕግህን ለሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው ዕንቅፋትም የለባቸውም፡፡
166ያህዌ ሆይ፣ ማዳንህን እጠብቃለሁ ትእዛዞችህንም እፈጽማለሁ፡፡
167ትእዛዝህን እጠብቃለሁ በሙሉ ልቤም እወዳቸዋለሁ፡፡
168ትእዛዝህንና ሕግህን አከብራለሁ አንተ የምሠራውን ሁሉ ታውቃለህ፡፡ ታው
169ያህዌ ሆይ፣ እንድትረዳኝ ወደ አንተ ስጮኽ ስማኝ እንደ ቃልህም ማስተዋልን ስጠኝ፡፡
170ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ፡፡
171ሥርዐትህን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አፈለቁ፡፡
172ትእዛዞችህ ሁሉ ትክክል ስለሆኑ ስለ ቃልህ እዘምራለሁ፡፡
173መመሪያህን መርጫለሁና እጅህ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ይሁን፡፡
174ያህዌ ሆይ፣ ማዳንህን ናፈቅሁ ሕግህም ደስታዬ ነው፡፡
175አመሰግንህ ዘንድ በሕይወት ልኑር ሕግህም ይርዳኝ፡፡
176እንደ ጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ ትእዛዞችህን አልረሳሁምና ባርያህን ፈልገው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።