1ቸር ነውና ያህዌን አመስግኑት ምሕረቱም ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች፡፡
2የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ «ምሕረቱ ለዘላለም ነው» ይበል፡፡
3የአሮን ቤት፣ «ምሕረቱ ለዘላለም ነው» ይበል፡፡
4ያህዌን የሚፈሩ ሁሉ፣ «ምሕረቱ ለዘላለም ነው» ይበሉ፡፡
5በተጨነቅሁ ጊዜ ያህዌን ጠራሁት እርሱም ሰማኝ፤ ነጻም አወጣኝ፡፡
6ያህዌ ከእኔ ጋር ነው፤ አልፈራም ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
7ይረዳኝ ዘንድ ያህዌ ከእኔ ጋር ነው የጠላቶቼንም ውድቀት አያለሁ፡፡
8በሰው ከመታመን ይልቅ ያህዌን መከታ ማድረግ ይሻላል፡፡
9በመሪዎች ከመመካት ይልቅ ያህዌን መጠጊያ ማድረግ ይሻላል፡፡
10ሕዝቦች ሁሉ ከበቡኝ ነገር ግን በያህዌ ስም አሸነፍኃቸው
11መክበቡንስ፣ ዙሪያዬን ከበቡኝ ነገር ግን በያህዌ ስም አሸነፍኃቸው፡፡
12እንደ ንብ መንጋ ከበቡኝ ሆኖም፣ እንደሚነድ እሾኽ ከሰሙ በእርግጥም በያህዌ ስም አሸነፍኃቸው፡፡
13ሊጥሉኝ ገፈተሩኝ ያህዌ ግን ረዳኝ፡፡
14ያህዌ ብርታቴና ደስታዬ ነው፤ የሚታደገኝም እርሱ ነው፡፡
15በጻድቃን ድንኳን፣ የእልልታና የሆታ ድምፅ፣ እንዲህ እያለ ያስተጋባል የያህዌ ቀኝ እጅ አሸነፈ፡፡
16የያህዌ ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አለ፤ የያህዌ ቀኝ እጅ አሸነፈ፡፡
17በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፣ አልሞትም የያህዌንም ሥራ ገና እናገራለሁ፡፡
18ያህዌ ክፉኛ ቀጥቶኝ ነበር ነገር ግን ለሞት አሳልፎ አልሰጠኝም፡፡
19የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ ወደዚያ ገብቼ ያህዌን አመሰግናለሁ፡፡
20ይህች የያህዌ ደጅ ናት፤ ጻድቃንም በእርሷ በኩል ይገባሉ፡፡
21ሰምተህ መልሰህልኛና፣ አዳኝም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ፡፡
22ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማእዘን ራስ ሆነ፡፡
23ይህም የያህዌ ሥራ ነው ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፡፡
24ያህዌ የሠራት ቀን ይህች ናት፣ በእርሷ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም እናደርጋለን፡፡
25ያህዌ ሆይ፣ እባክህ ድል አቀዳጀን! ያህዌ ሆይ፣ እባክህ አከናውንልን፡፡
26በያህዌ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እኛም ከያህዌ ቤት ባረክናችሁ፡፡
27ያህዌ አምላካችን ነው፤ ብርሃኑንም በላያችን አበራ መሥዋዕቱን መሠዊያው ቀንዶች ላይ በገመድ እሰሩ፡፡
28አንተ አምላኬ ነህ፤ አመሰግንሃለሁ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፡፡
29ቸር ነውና ያህዌን አመስግኑ ምሕረቱም ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች፡፡