1ለእኛ ሳይሆን፣ ያህዌ ሆይ ለእኛ ሳይሆን ስለ ፍቅርህ፣ ስለ ታማኝነትህ ስምህን አክብረው፡፡
2ስለ ምን ሕዝቦች፣ «አምላካቸው የት አለ?» ይበሉ
3አምላካችን በሰማይ ነው እርሱ ደስ የሚለውን አደረገ፡፡
4የአሕዛብ ጣዖቶች ብርና ወርቅ የሰው እጅ ሥራዎችም ናቸው፡፡
5አፍ አላቸው ግን አይናገሩም ዐይን አላቸው ግን አያዩም
6ጆሮ አላቸው ግን አይሰሙም አፍንጫ አላቸው ግን አያሸቱም፡፡
7እጅ አላቸው ግን አይዳሰስም እግር አላቸው ግን አይራመዱም ድምፅም ማሰማት አይችሉም፡፡
8የሠሩአቸውና የሚታመኑባቸው ሁሉ እንደ እነዚህ ጣዖቶች ናቸው፡፡
9የእስራኤል ቤት ሆይ፣ በያህዌ ታመኑ ረዳታችሁና ጋሻችሁ እርሱ ነው፡፡
10የአሮን ቤት ሆይ፣ በያህዌ ታመኑ ረዳታችሁና ጋሻችሁ እርሱ ነው፡፡
11እናንት ያህዌን የምትፈሩ፣ በእርሱ ታመኑ ረዳታችሁና ጋሻችሁ እርሱ ነው፡፡
12ያህዌ ያስበናል፤ ይባርከናልም፤ እርሱ የእስራኤልን ቤት ይባርካል የአሮንንም ቤት ይባርካል፡፡
13ታላላቆችም ሆኑ ታናናሾች እርሱ የሚፈሩትን ሁሉ ይባርካል፡፡
14ያህዌ እናንተንና ልጆቻችሁን በባርኮቱ ይባርካችሁ፡፡
15ሰማይና ምድርን የፈጠረ ያህዌ ይባርካችሁ፡፡
16ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት፡፡
17ወደ ዝምታ ዓለም፣ ወደ መቃብር የወረዱ ሙታን ያህዌን ሊያመሰግኑ አይችሉም፡፡
18እኛ ግን፣ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም ያህዌን እንባርካለን፡፡ ያህዌ ይመስገን፡፡