1የልመናዬን ድምፅ ስለ ሰማ ያህዌን ወደድሁት፡፡
2እርሱ ሰምቶኛልና በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ወደ እርሱ እጣራለሁ፡፡
3የሞት ወጥመድ ያዘኝ የሲኦልም ጣር አገኘኝ ጭንቅና ሐዘን በረታብኝ፡፡
4እኔም የያህዌን ስም ጠራሁ «ያህዌ ሆይ፣ እባክህ ነፍሴን አድናት፡፡»
5ያህዌ ቸርና መሐሪ ነው፡፡ አምላካችን ርኅሩኅ ነው፡፡
6አምላካችን ገሮችን ይጠብቃል እኔም በተቸገርኩ ጊዜ አድኖኛል፡፡
7ያህዌ መልካም ነገር አድርጐልኛልና ከእንግዲህ ነፍሴ ወደ እረፍት ቦታ ትመለሳለች፡፡
8አንተ ነፍሴን ከሞት፣ ዐይኔን ከእንባ እግሮቼን ከመሰናክል አድነሃልና፡፡
9እኔም በሕያዋን ምድር ያህዌን አገለግላለሁ፡፡
10«እጅግ ተጨንቄአለሁ» ባልሁ ጊዜ እንኳ በእርሱ ማመኔን አልተውሁም፡፡
11ግራ በተጋባሁ ጊዜ፣ «ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው» አልሁ፡፡
12ስላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለያህዌ ምን ልክፈለው?
13የመዳንን ጽዋ አነሣለሁ የያህዌንም ስም እጠራለሁ፡፡
14በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለያህዌ እፈጽማለሁ፡፡
15የቅዱሳኑ ሞት በያህዌ ፊት የከበረ ነው፡፡
16ያህዌ ሆይ፣ እኔ በእውነት ባርያህ ነኝ፣ የሴት ባርያህም ልጅ ነኝ፡፡ ከእስራቴም ፈታኸኝ፡፡
17ለአንተ የምስጋና መሥዋዕት አቀርባለሁ የያህዌንም ስም እጠራለሁ፡፡
18በሕዝቡ ሁሉ ፊት ስእለቴን ለያህዌ እፈጽማለሁ
19ኢየሩሳሌም ሆይ፣ በመካከልሽ በያህዌ ቤት አደባባይ ይህን አደርጋለሁ፡፡