1ያህዌ ይመስገን፡፡ በቅኖች ሸንጐ በጉባኤም መካከል በፍጹም ልቤ ያህዌን አመሰግናለሁ፡፡
2የያህዌ ሥራ ታላቅ ናት፤ የሚፈልጓትም ሁሉ አጥብቀው ይናፍቋታል፡፡
3ሥራው ባለ ግርማና ባለ ክብር ነው ጽድቁም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡
4ያህዌ ቸርና መሐሪ ነው ሲታወስ የሚኖር ድንቅ ሥራ አደረገ፡፡
5ለሚፈሩት ምግባቸውን ይሰጣል ኪዳኑንም ዘወትር ያስባል፡፡
6ለእነርሱ የአሕዛብን ርስት በመስጠት የአሠራሩን ብርታት አሳይቶአል፡፡
7የእጁ ሥራ እውነተኛና ቅን ነው ትእዛዞቹም የታመኑ ናቸው፡፡
8እነርሱም ለዘላለም የጸኑ ናቸው በታማኝነትና በቅንነት ይጠበቃሉ፡፡
9ለሕዝቡ ድልን ሰጠ ኪዳኑን ለዘላለም አዘዘ ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው፡፡
10ያህዌን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው ትእዛዙንም የሚጠብቁ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፡፡ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል፡፡