1እግዚአብሔር ሆይ፣ ልቤ ጽኑ ነው፡፡ እዘምራለሁ፤ በፍጹም ልቤም እዘምራለሁ፡፡
2በገናና መሰንቆም ተነሡ፤ እኔም ማልጄ እነሣለሁ፡፡
3ያህዌ ሆይ፣ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ በመንግሥታት መካከል የምስጋና መዝሙር አቀርብልሃለሁ
4ምሕረትህ ከሰማያት በላይ ታላቅ ናትና ታማኝነትህም እስከ ጠፈር ይደርሳል፡፡
5አምላክ ሆይ፣ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል ክብርህም በምድር ሁሉ ይንሰራፋ፡፡
6የምትወደው ሕዝብህ ይድን ዘንድ በቀኝ እጅህ ታደግ መልሰልኝም፡፡
7እግዚአብሔር በቅድስናው እንዲህ አለ፤ ደስ እያለኝ ሴኬምን እከፍላለሁ የሱከትንም ሸለቆ እለካለሁ፡፡
8ገለዓድ የእኔ ነው፤ ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራስ ቁሬ፣ ይሁዳም በትረ መንግሥቴ ነው፡፡
9ሞዓብ መታጠቢያ ገንዳዬ ነው በኤዶም ላይ ጫማዬን እወረውራለሁ፤ በፍልስጥኤም ላይ በድል አድራጊነት እፎክራለሁ፡፡
10ወደ ተመሸገችው ከተማ ማን ይወስደኛል? ወደ ኤዶምስ ማን ያደርሰኛል?
11እግዚአብሔር ሆይ፣ ያጣልኸን አንተ አይደለህምን? ከሰራዊታችንም ጋር ወደ ጦርነት አልወጣህም፡፡
12አሁንም የሰው ማዳን ከንቱ ነውና በጠላታችን ላይ ድል አቀዳጀን፡፡
13በእግዚአብሔር ረድኤት ድል እናደርጋለን ጠላቶቻችንንም ከእግሩ በታች የሚረግጥ እርሱ ነው፡፡