1ቸር ነውና ምሕረቱም ለዘላለም ነውና ያህዌን አመስግኑ፡፡
2ያህዌ የተቤዣቸው ከጠላትም እጅ የታደጋቸው ይናገሩ፡፡
3ለባዕድ ምድር፣ ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ ሰበሰባቸው፡፡
4በበረሐ መንገድ ጠፍቶአቸው በምድረ በዳ ተንከራተቱ የሚኖሩበትም ከተማ አላገኙም፡፡
5ተራቡ፤ ተጠሙ ከድካም የተነሣ ዛሉ፡፡
6በተጨነቁ ጊዜ ወደ ያህዌ ጮኹ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው፡፡
7ወደሚኖሩበት ከተማ በቀና መንገድ መራቸው፡፡
8ለሰው ልጆች ስላደረገው ድንቅ ነገርና ስለዘላለማዊ ፍቅሩ ሕዝቡ ያህዌን ያመስግኑ፡፡
9እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቶአልና የተራበችውን ነፍስ በመልካም ነገር አጥግቦአል፡፡
10አንዳንዶች በሰንሰለት ታስረው ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡
11ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ቃል በማመፃቸው የልዑልንም ምክር በማቃለላቸው ነበር፡፡
12በከባድ ሥራ ልባቸውን አዛለ ተዘለፈለፉ፤ የሚረዳቸውም አላገኙም፡፡
13በተጨነቁ ጊዜ ወደ ያህዌ ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው፡፡
14ከነበሩበት ድቅድቅ ጨለማ አወጣቸው የታሰሩበትንም ሰንሰለት ሰባበረ፡፡
15ለሰው ልጆች ስላደረገው ድንቅ ነገርና ስለ ዘላለማዊ ፍቅሩ ሕዝቡ ያህዌን ያመስግኑ፡፡
16እርሱ የናሱን በሮች ሰብሮአልና የብረቱንም መወርወሪያ ቆርጦአል፡፡
17አንዳንዶች የዐመፃን መንገድ በመከተላቸው ቂሎች ሆኑ ከበደላቸው የተነሣ ችግር ውስጥ ወደቁ፡፡
18ምግብ የመብላት ፍላጐት አጡ፤ ወደ ሞት በሮችም ተቃረቡ፡፡
19በተጨነቁ ጊዜ ወደ ያህዌ ጮኹ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው፡፡
20ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፡፡ ከመቃብር አፋፍ መለሳቸው፡፡
21ለሰው ልጆች ስላደረገው ድንቅ ነገርና ስለ ዘላለማዊ ፍቅሩ ሕዝቡ ያህዌን ያመስግኑ፡፡
22የምስጋና መሥዋዕት ያቅርቡለት በዝማሬም ሥራውን ያውጁ፡፡
23አንዳንዶች በመርከብ እየተጓዙ ንግዳቸውን ያካሄዱ ነበር፡፡
24እነርሱ የያህዌን ሥራ አዩ ድንቅ አድራጐቱንም በጥልቅ ውስጥ ተመለከቱ፡፡
25ትእዛዝ በሰጠ ጊዜ ባሕሩን የሚያናውጥ ዐውሎ ነፋስ ነፈሰ፡፡
26ወደ ሰማይ ወጡ፤ ወደ ጥልቅም ወረዱ ከመከራቸው የተነሣ ልባቸው ቀለጠ፡፡
27እንደ ሰካራም ዞሮባቸው ወዲያ ወዲህ ተንገዳገዱ፤ መላው ጠፍቶባቸው የሚያደርጉትን አጡ፡፡
28በመከራቸው ጊዜ ወደ ያህዌ ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው፡፡
29ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ አደረገ ሞገዱም ረጭ አለ፡፡
30ባሕሩ ጸጥ በማለቱ ደስ አላቸው ወዳሰቡትም ወደብ አደረሳቸው፡፡
31ለሰው ልጆች ስላደረገው ድንቅ ነገር ስለ ዘላለማዊ ፍቅሩ ሕዝቡ ያህዌን ያመስግኑ፡፡
32በሕዝቦች ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያደርጉት በሽማግሌዎችም ሸንጐ ያመስግኑት፡፡
33ወንዞችን ወደ ምድረ በዳ የውሃ ምንጮችንም ወደ ደረቅ ምድር ለወጠ፡፡
34ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን መሬት ደረቅ ምድር አደረገ፡፡
35ምድረ በዳውን ወደ ኩሬ ደረቁንም ምድር ወደ ውሃ ምንጭ ቀየረ፡፡
36የተራቡትን በዚያ አኖረ የሚኖሩበትንም ከተማ ሠሩ፡፡
37በእርሻዎች እህል ዘሩ ወይንን ተከሉ፤ ብዙ መከርም ሰበሰቡ፡፡
38ይባርካቸዋል፤ እነርሱም እጅግ ይበዛሉ የከብቶቻቸውም ብዛት እንዲያንስ አያደርግም፡፡
39በጭንቅ፣ በመከራና በሐዘን፣ ቁጥራቸው አንሶ ተዋርደው ነበር፤ በመኳንንቱም ላይ መናቅን አወረደባቸው
40መውጪያ መግቢያው በማይታወቅ በረሐ ውስጥም አንከራተታቸው፡፡
41ሆኖም፣ ችግረኞችን ከስቃይ አወጣቸው ለቤተ ሰቡም እንደ በግ መንጋ ተጠነቀቀ፡፡
42ቅኖች ይህን ዐይተው ደስ ይላቸዋል ክፋትም አፏን ትዘጋለች፡፡
43አስተዋይ የሆነ ሰው ይህን ልብ ይበል፤ እርሱም የያህዌን ምሕረት ያስተውል፡፡