1ያህዌን አመስግኑ ቸር ነውና ያህዌን አመስግኑ ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፡፡
2የያህዌን ብርቱ ሥራ ማን ሊናገር ይችላል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ተናግሮ ይጨርሳል?
3ዘወትር መልካሙንና ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው፡፡
4ያህዌ ሆይ፣ ለሕዝብህ ሞገስ ስታደርግ አስበኝ፤ በምታድናቸውም ጊዜ ርዳኝ፡፡
5ይኸውም፣ አንተ የመረጥሃቸውን መበልጸግ እንዳይ፣ በሕዝብህ ደስ መሰኘት እኔንም ደስ እንዲለኝ በርስትህም ክብር መመካት እንድችል ነው፡፡
6እኛም እንደ አባቶቻችን ኃጢአት ሠራን፣ በደልን፣ ክፉም አደረግን፡፡
7አባቶቻችን በግብፅ ምድር ያደረግኸውን አላስተዋሉም፡፡ ብዙዎቹን የቸርነት ሥራዎቹን አላስተዋሉም፡፡ በባሕሩ አጠገብ፣ ቀይ ባሕር አጠገብ ዐመፁብህ፡፡
8እርሱ ግን የኃይሉን ታላቅነት ለማሳየት ስለ ስሙ አዳናቸው፡፡
9ቀይ ባሕርን ገሠጸ፤ እርሱም ደረቀ በምድረ በዳ እንደሚታለፍ በጥልቅ ውሃ መካከል መራቸው፡፡
10ከባላጋራቸው እጅ አዳናቸው ከጠላትም እጅ ታደጋቸው፡፡
11ባላጋራዎቻቸውን ውሃ ዋጣቸው ከእነርሱ አንድ አልተረፈም፡፡
12ከዚያ በኋላ የተስፋ ቃሉን አመኑ በዝማሬም አመሰገኑት፡፡
13ሆኖም፣ ወዲያውኑ እርሱ ያደረገውን ረሱ በምክሩም ለመሄድ አልታገሡም፡፡
14በምድረ በዳ ብዙ ነገር ተመኙ፤ በበረሐም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፡፡
15እርሱም የለመኑትን ሰጣቸው ነገር ግን የሚያኮሰምን ደዌ ሰደደባቸው፡፡
16ሰፈር ውስጥ በሙሴ ላይ የተቀደሰው የያህዌ ካህን ላይ ቀኑ፡፡
17ምድር ተከፍታ ዳታንን ዋጠች የአቤሮንንም ሰዎች ሰለቀጠች፡፡
18በመካከላቸው እሳት ነድዶ ነበልባልም ክፉዎችን ፈጅቶ አስወገደ፡፡
19በኮሬብ ጥጃ ሠሩ ቀልጦ ለተሠራ ምስል ሰገዱ፡፡
20ክብራቸውን ሣር በሚበላ የበሬ ምስል ለወጡ፡፡
21በግብፅ ታላላቅ ነገሮች ያደረገውን ያዳናቸውን እግዚአብሔርን ረሱ፡፡
22እርሱ በካም ምድር ድንቅ ሥራ በቀይ ባሕርም አስደናቂ ነገር አደረገ፡፡
23ቁጣውን እንዲመልስ እርሱ የመረጠው ሙሴ በመካከል ባይገባ ኖሮ እነርሱን ለማጥፋት ወስኖ ነበር፡፡
24መልካሚቱን ምድር ናቁ በተስፋ ቃሉም አላመኑም፡፡
25ድንኳናቸው ውስጥ አጉረመረሙ ለያህዌም አልታዘዙም፡፡
26ስለዚህ በምድረ በዳ እንደሚያጠፋቸው እጁን አንሥቶ ማለ፡፡
27ዘሮቻቸውን በአሕዛብ መካከል ለመጣል እነርሱንም ወደ ተለያየ አገሮች እንደሚበትናቸው ማለ፡፡
28ብዔል ፌጐርን አመለኩ ለሙታን የተሠዋውን በሉ፡፡
29በተግባራቸውም እግዚአብሔርን አስቆጡት፤ በዚህም ምክንያት በመካከላቸው መቅሠፍት ተነሣ፡፡
30ፊንሐስ ተነሥቶ ጣልቃ ገባ፤ መቅሠፍቱም ተገታ፡፡
31ይህም ከትውልድ እስከ ትውልድ ለዘላለም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት፡፡
32ደግሞም በመሪባ ውሃ አጠገብ ያህዌን አስቆጡት ሙሴም በእነርሱም ምክንያት ችግር ላይ ወደቀ፡፡
33ሙሴን ስላስመረሩት ራሱን ባለ መቆጣጠር ተናገረ፡፡
34እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት ሕዝቦችን ከማጥፋት ወደ ኃላ አሉ፡፡
35እንዲያውም ከእነርሱ ጋር በመደባለቅ የእነርሱን መንገድ ተማሩ፡፡
36ጣዖቶቻቸውን አመለኩ፤ ይህም ወጥመድ ሆነባቸው፡፡
37ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ፡፡
38የወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደም ለከነዓን ጣዖቶች መሥዋዕት በማቅረባቸው ንጹሕ ደም አፈሰሱ ምድሪቱንም አረከሱ፡፡
39እነርሱ በሥራቸው ረከሱ በድርጊታቸውም አመንዝሮች ሆኑ፡፡
40ስለዚህ ያህዌ በሕዝቡ ላይ እጅግ ተቆጣ ርስቱንም ተጸየፈ፡፡
41ለአሕዛብ አሳልፎ ሰጣቸው ጠላቶቻቸውም በላያቸው ገዢዎች ሆኑባቸው፡፡
42ጠላቶቻቸው ጨቆኑአቸው በሥልጣናቸውም ሥር አደረጓቸው፡፡
43እርሱ ብዙ ጊዜ ታደጋቸው እነርሱ ግን ዐመፅ ማድረጋቸውን ገፉበት፡፡ በገዛ ኃጢአታቸው ተዋረዱ፡፡
44ይህም ሆኖ እንዲረዳቸው ወደ እርሱ ሲጮኹ ጩኸታቸውን ሰማ ጭንቀታቸውንም ተመለከተ፡፡
45ለእነርሱ ሲል ቃል ኪዳኑን አሰበ እንደ ምሕረቱም ብዛት ከቁጣው ተመለሰ፡፡
46የሚጨቁኑአቸው ሁሉ እንዲራሩላቸው አደረገ፡፡
47አምላካችን ያህዌ ሆይ፣ አድነን፤ ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣ አንተን በመወደስ እንድንከብር ከሕዝቦች መካከል ሰብስበህ አምጣን፡፡
48የእስራኤል አምላክ ያህዌ ከዘላለም እስከ ዘለላም ይባረክ፡፡ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል፡፡ ያህዌ ይባረክ፡፡