መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

መጽሐፈ መዝሙር 105

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ያህዌን አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ ሥራውንም በሕዝቦች መካከል ግለጡ፡፡
2ለእርሱ የምስጋና መዝሙር አቅርቡ ድንቅ ሥራዎቹን ሁሉ ተናገሩ፡፡
3በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ ያህዌን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው፡፡
4ያህዌንና ብርታቱን ፈልጉ ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ፡፡
5ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች ተአምራቱንና ከአፉ የወጣውን ፍርድ ፈልጉ፡፡
6እናንት የአገልጋዩ የአብርሃም ዘሮች እርሱ የመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ አስታውሱ፡፡
7እርሱ አምላካችን ያህዌ ነው ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው፡፡
8ኪዳኑን ለዘላለም፣ ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺህ ትውልድ ዘመን ያስታውሳል፡፡
9ከአብርሃም ጋር ያደረገውን ኪዳን ለይስሐቅም በመሐላ የሰጠውን ተስፋ አይረሳም፡፡
10ይህን ለያዕቆብ ሥርዐት ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጐ አጸናው፡፡
11እንዲህም አለ፣ «የርስትህ ድርሻ እንዲሆን የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ፡፡
12ይህን ያለው እነርሱ በቁጥር አነስተኞች፣ እጅግ ጥቂትና ባይተዋሮች ሳሉ፣
13ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ሲንከራተቱ፣ ከአንዱ መንግሥት ወደ ሌላው መንግሥት ሲቅበዘበዙ ነበር፡፡
14ማንም እንዲጨቁናቸው አልፈቀደም ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፡፡
15«የቀባኋቸውን አትንኩ፤ ነቢያቶቼንም አትጉዱ» አለ፡፡
16በምድር ላይ ችጋርን ጠራ የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፡፡
17ከእነርሱ አስቀድሞ በባርነት የተሸጠው ዮሴፍን ላከ፡፡
18እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ አንገቱም ላይ የብረት ማነቆ ገባ፡፡
19የተናገረው እስኪፈጸም ድረስ የያህዌ ቃል ፈተነው፡፡
20እርሱን እንዲፈቱ ንጉሡ አገልጋዮቹን ላከ፤ የሕዝቦችም ገዢ ነጻ አወጣው፡፡
21የቤቱ ጌታ የንብረቱም ሁሉ አስተዳዳሪ አደረገው፡፡
22በንጉሡ ባለ ሥልጣኖች ላይ አዛዥ ሆነ ለንጉሡም አማካሪዎች ጥበብን እንዲያስተምር ሥልጣን ተሰጠው፡፡
23ከዚያም እስራኤል ወደ ግብፅ ሄደ እስከ ጊዜው ድረስ ያዕቆብ በካም ምድር ተቀመጠ፡፡
24ያህዌ ሕዝቡን እጅግ አበዛ ከጠላቶቻቸውም ይልቅ ብርቱ አደረጋቸው፡፡
25ሕዝቡን እንዲጠሉ ባርያዎቹንም እንዲበድሉ ልባቸውን አስጨከነ፡፡
26ባርያውን ሙሴን እርሱ የመረጠውንም አሮንን ላከ፡፡
27በግብፃውያን መካከል ምልክቶችን በካም ምድርም ድንቆችን አደረጉ፡፡
28ጨለማን ልኮ ምድርን ጽልመት አለበሳት ይሁን እንጂ ትእዛዞቹን አልፈጸሙም፡፡
29ውሃቸውን ወደ ደም ለወጠ ዓሣዎቻቸውንም ፈጀ፡፡
30የነገሥታት እልፍኝ እንኳ ሳይቀር ምድራቸው በእንቁራሪት ተሸፈነች፡፡
31እርሱ ሲናገር ተናካሽ ዝንቦችና ተናዳፊ ትንኞች በአገራቸው ተርመሰመሱ፡፡
32በአገራቸው ላይ የበረዶ ድንጋይና መብረቅ አወረደ፡፡
33ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ ሌሎች ዛፎቻቸውንም ሰባበረ፡፡
34እርሱ ሲናገር አንበጣ መጣ ስፍር ቁጠር የሌለውም ኩብኩባ ከተፍ አለ፡፡
35አንበጣ የምድሪቱን ዕፅዋት ሁሉ በላ እህላቸውንም ሁሉ ፈጀ፡፡
36ደግሞም የእያንዳንዱን ግብፃዊ በኩር ሁሉ የኃይላቸውንም ሁሉ በኩራት መታ፡፡
37እስራኤላውያንን ከወርቅና ከብር ጋር ከዚያ መርቶ አወጣ፤ ከነገዶቻቸው አንዱ እንኳ አልተደናቀፈም፡፡
38እጅግ ፈርተዋቸው ነበርና እስራኤላውያን አገር ለቀው ሲወጡ ግብፅ ደስ አላት፡፡
39በሚሄዱበት ጊዜ በደመና ጋረዳቸው እሳትም በሌሊት አበራላቸው፡፡
40ምግብ እንዲሰጣቸው በለመኑት ጊዜ ድርጭት አመጣላቸው የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው፡፡
41ዐለቱን ሰነጠቀ፤ ውሃም ተንዶለዶለ
42ለባርያው ለአብርሃም የሰጠውን ቅዱስ የተስፋ ቃል አስታውሶአልና
43ሕዝቡን በደስታ፣ ምርጦቹንም በእልልታ መራቸው፡፡
44የሕዝቦችን ምድር ሰጣቸው የእነርሱንም ሀብት ወረሱ፡፡
45ይህም ሥርዐቱን ይጠብቁ ዘንድ ሕጉንም ይፈጽሙ ዘንድ ነው፡፡ ያህዌ ይመስገን
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።