1ያህዌ ሆይ ጸሎቴን ሰማ ጩኸቴንም አድምጥ፡፡
2በመከራዬ ጊዜ ፊትህን ከእኔ አትሰውር ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል ወደ አንተ ስጣራ ፈጥነህ አድምጠኝ፡፡
3ዘመኔ እንደ ጢስ እየበነነ ነው ዐጥንቶቼም እንደ እሳት እየነደዱ ነው፡፡
4ልቤ ተሰብሮአል፤ እኔም እንደ ደረቀ ሣር ሆኛለሁ፡፡ እህል መብላትንም ዘንግቻለሁ፡፡
5ዘወትር ከመቃተቴ የተነሣ ዐጥንቴ ከቆዳዬ ጋር ተጣበቀ፡፡
6በምድረ በዳ እንዳለ እርኩም መሰልሁ፤ በፍርስራሽ መካከል እንዳ ጉጉት ሆንሁ፡፡
7ያለ እንቅልፍ አድራለሁ፤ በቤት ጣራ ላይ እንዳለ ብቸኛ ወፍ ሆኛለሁ
8ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ ይሳለቁብኛል የሚያፌዙብኝም ስሜን እንደ ርግማን ቆጥረውታል፡፡
9ዐመድ እንደ እህል ቅሜአለሁ! እንባዬም ከምጠጣው ነገር ጋር ተደባልቆአል፡፡
10ወደ ላይ አነሣኸኝ፤ ከቁጣህና ከመዓትህም የተነሣ መልሰህ ጣልኸኝ፡፡
11ዘመኖቼ ቶሎ እንደሚያልፍ ጥላ ናቸው እኔም እንደ ሣር ደረቅሁ
12አንተ ግን ያህዌ ሆይ፣ ለዘላለም ትኖራለህ ስምህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ገናና ነው፡፡
13ትነሣህ፤ ጽዮንንም ትምራታለህ ለእርሷ ርኅራኄህን የምታሳይበት ጊዜ ነው፤
14አገልጋዮችህ ድንጋዮዋን ወደዋልና ለፍርስራሾቿ ራርተዋል፡፡
15ሕዝቦች የያህዌን ስም የምድር ነገሥታትም ክብርህን ይፈራሉ፡፡
16ያህዌ ጽዮንን እንደ ገና ይሠራታልና በክብሩም ይገለጣል፡፡
17በዚያ ጊዜ እርሱ ለችግረኞች ጸሎት መልስ ይሰጣል፤ ልመናቸውንም አይንቅም፡፡
18ገና ያልተወለዱ ሰዎች እንዲያመሰግኑት ይህ ያህዌ ያደረገው ድንቅ ነገር ለሚመጣው ትውልድ ይጻፍ፡፡
19በከፍታ ካለው መቅደሱ ወደ ታች ተመልክቶአልና ያህዌ ከሰማይ ምድርን ዐይቶአል፡፡
20ይኸውም የእስረኞችን መቃተት ይሰማ ዘንድ ሞት የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ ነው፡፡
21ስለዚህ የያህዌ ስም በጽዮን፣ ምስጋናውም በኢየሩሳሌም ይነገራል፡፡
22ይህም የሚሆነው ሕዝቦችና መንግሥታት ያህዌን ለማምለክ በአንድት ሲሰበሰቡ ነው፡፡
23በሕይወቴ እኩሌታ ብርታቴን ቀጨው ዕድሜዬንም ባጭሩ አስቀረው፡፡
24እኔም፣ «አምላኬ ሆይ፣ የአንተ ዘመን ከትውልድ እስከ ትውልድ ስለሆነ በዕድሜዬ እኩሌታ አትውሰደኝ» አልሁ፡፡
25አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው፡፡
26እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ እነርሱ እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጐናጸፊያ ትለውጣቸዋለህ እነርሱም ወዲያ ይጣላሉ፡፡
27አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዘመኖችህም ፍጻሜ የላቸውም፡፡
28የአገልጋዮችህ ልጆች በሰላም ይኖራሉ ትውልዳቸውም በፊትህ ጸንቶ ይኖራል፡፡