1ጥበብ ቤቷን ሰራች፤ ሰባት ምሰሶዎችን ከድንጋይ ጠርባ አቆመች፡፡
2ለእራት እንስሳዎቿን አረደች፤ የወይን ጠጇንም ደባለቀች፤ ማዕዷንም አዘጋጀች፡፡
3በሴት ሰራተኞቿ በኩል የጥሪ ወረቀት ላከች፣ ከከተማይቱ ከፍተኛ ቦታ ተጣራች፡፡
4እርሷም አእምሮ ለጎደላቸው “እውቀትን ያላገኙ ሁሉ ወደዚህ ይምጡ!” አለች፡፡
5“ኑ፣ ምግቤን ተመገቡ፣ የደባለቅሁትንም የወይን ጠጄን ጠጡ፡፡
6የአላዋቂነት መንገዳችሁን ወደኋላ በመተው በሕይወት ኑሩ፤ በማስተዋል መንገድ ተመላለሱ፡፡
7ፌዘኛን የሚገስጽ ሰው በራሱ ላይ ስድብን ያመጣል፣ ክፉን ሰው የሚገስጽ ደግሞ ይጎዳል፡፡
8ፌዘኛን ሰው አትገስጽ፣ ይጠላሃል፤ ጥበበኛን ሰው ገስጽ፣ ይወድድሃል፡፡
9ለጥበበኛ ሰው ትምህርትን ስጠው፣ ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል፤ ጻድቅን ሰው አስተምረው፣ እርሱም ይበልጥ እውቀትን ይጨምራል፡፡
10የጥበብ መጀመርያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፣ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው፡፡
11በእኔ ዘመንህ ይበዛልና፣ በሕይወትህም ዓመታት ይጨመሩልሃል፡፡
12ጥበበኛ ከሆንህ፣ ጥበበኛ የምትሆነው ለራስህ ነው፣ ነገር ግን የምታፌዝ ከሆንህ፣ ፌዘኛነትህን ለብቻህ ትሸከመዋለህ፡፡”
13ሞኝ ሴት ለፍላፊ ናት፣ ትምህርት የሌላትና ምንም የማታውቅ ናት፡፡
14በከተማዋ ከፍተኛ ስፍራ በቤቷ በር በመቀመጫ ላይ ትቀመጣለች፡፡
15እርሷ በመንገድ የሚያልፉትን፣ በመንገዳቸውም ቀጥ ብለው የሚሄዱትን ሰዎች ትጣራለች፡፡
16እርሷም አእምሮ ለጎደላቸው “እነዚህ ትምህርት የሌላቸው ሰዎች ወደዚህ ይምጡ!” አለች፡፡
17“የተሰረቀ ውኃ ጣፋጭ ነው፣ በምስጢር የበሉት እንጀራም አስደሳች ነው፡፡”
18ነገር ግን እርሱ ሙታን በዚያ እንዳሉ አያወቅም፣ ተጋባዦቿ በሲዖል ጥልቀት ውስጥ እንዳሉ አያውቅም፡፡