1ልጄ ሆይ፣ ቃሎቼን ጠብቅ፣ ትእዛዜንም በአንተ ውስጥ አኑር፡፡
2ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ኑር፣ ሕጌንም እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቅ፡፡
3በጣቶችህም ላይ እሰራቸው፤ በልብህም ጽላት ጻፋቸው፡፡
4ጥበብ “አንቺ እህቴ ነሽ” በላት፣ ማስተዋልን ደግሞ ዘመዴ ብለህ ጥራው፣
5ከአመንዝራ ሴት፣ ቃሏንም ከምታለዝብ ከዘማዊም ሴት ትጠብቅህ ዘንድ፡፡
6በቤቴ መስኮት ላይ ሆኜ ወደ ውጭ ተመለከትሁ፣
7ብዙ እውቀት አልባ ወጣቶች ተመለከትሁ፡፡ ከመካከላቸው አንድ የማያስተውል ወጣት ተመለከትሁ፡፡
8ያ ወጣት በቤቷ ማዕዘን አጠገብ ባለው መንገድ አለፈ፣ ከዚያም ወደ ቤቷ አቅጣጫ ሄደ
9ብርሃን ደንገዝገዝ፣ ቀኑ መሸትሸት ብሎ ነበር፣ በምሽትና በሌሌት ጨለማ፡፡
10በዚያ አንዲት ሴት አገኘችው፣ እንደ ሴተኛ አዳሪ የለበሰች፣ እዚያ ለምን እንደ መጣች በሚገባ ታውቃለች፡፡
11ጯኺና እምቢተኛ ናት፣ እግሮቿ በቤት አይቀመጡም
12አንዴ በመንገድ፣ አንዴ በገበያ፣ በየማዕዘኑም ተጋድማ ታደባለች፡፡
13ስለዚህም ትይዘዋለች፣ ትስመውማለች፣ ፊቷም እፍረት ሳይታይበት እንዲህ አለችው፣
14ዛሬ የሰላም መስዋዕቴን አቅርቤአለሁ፣ ስእለቴንም ፈጽሜአለሁ፣
15ስለዚህ አንተን ለማግኘት፣ ፊትህን ለመፈለግ ወጣሁ፣ አግኝቼሃለሁም፡፡
16በአልጋየ ላይ መሸፈኛ ዘርግቼበታለሁ፣ ከግብጽ የመጣ ባለቀለም የአልጋ ልብስ አንጥፌበታለሁ፡፡
17አልጋየን ከርቤ፣ አልሙንና ቀረፋ ረጭቼበታለሁ፡፡
18ና፣ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፤ ፍቅራችንን በምንገልጥባቸው የተለያዩ መንገዶች በታላቅ ደስታ እንፈንድቅ፡፡
19ባሌ በቤት የለም፤ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዷል፡፡
20በገንዘብ የተሞላ ቦርሳ ወስዷል፤ ሙሉ ጨረቃ በወጣበት ቀን ይመለሳል፡፡”
21በሚያባብል ንግግሯ ታሳስተዋለች፣ በለሰለሰ ንግሯም ታታልለዋለች፡፡
22ለመታረድ እንደሚነዳ በሬ፣ ፍላጻ ጉበቱን እስኪወጋው ድረስ በወጥመድ እንደተያዘ አጋዘን፣
23ወደ ወጥመድ በርራ እንደምትገባ ወፍ፣ ሕይወቱን እንደሚያሳጣው ሳያውቅ እርሷን ይከተላታል፡፡
24አሁን፣ ልጆቼ ሆይ፣ አድምጡኝ፤ የምናገረውንም ልብ ብላችሁ ስሙኝ፡፡
25ልባችሁ ወደ መንገዷ እንዲያዘነብል አትፍቀዱ፤ በጎዳናዋም አትሳቱ፡፡
26ብዙ ተጎጂዎችን አጥምዳ ጥላለች፤ ቁጥራቸውም እጅግ ብዙ ነው፡፡
27ቤቷ ወደ ሲኦል በሚወስደው መንገድ ነው፤ ወደ ሞት ማደርያም የሚያወርድ ነው፡፡