1ልጄ ሆይ፣ ጎረቤትህ ለወሰደው ብድር ዋስ ብትሆንና ገንዘብህን ለዋስትና ብታስይዝ፣ የማታውቀው ሰው ለወሰደው ብድር መተማመኛ ሰጥተህ ከሆነ፣
2የዚያን ጊዜ በቃልህ ምክንያት በራስህ ላይ ወጥመድ ዘርግተሃል፣ በአፍህም ቃል ተጠምደህ ተይዘሃል፡፡
3ልጄ ሆይ፣ ይህን አድርግ፣ ራስህንም አድን፣ አንተ በጎረቤትህ ምህረት ስር ነህና፡፡ ሂድ፣ ጎረቤትህም እንዲተውህ ሄደህ በትህትና ለምነው፡፡
4ለአይንህ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶችህም እንጉልቻን አትስጥ፡፡
5የሜዳ ፍየል ከአዳኝ እጅ፣ ወፍም ከአጥማጅ እጅ እንደምታመልጥ እንዲሁ ራስህን አድን፡፡
6አንተ ሰነፍ ሰው፣ ወደ ጉንዳን ተመልከት፣ መንገዷን አስተውል፣ ጥበበኛም ሁን፡፡
7አዛዥ፣ አለቃ ወይም ገዥ የላትም፣
8ይሁን እንጂ ምግቧን በበጋ ታዘጋጃለች፣ በመኸር ደግሞ የምትበላውን ታከማቻለች፡፡
9አንተ ሰነፍ፣ የምትተኛው እስከ መቼ ነው? ከእንቅልፍህስ የምትነሣው መቼ ነው?
10“ጥቂት ማንቀላፋት፣ ጥቂት ማንጎላቸት፣ ጥቂት እጅን አጣጥፎ ማረፍ”
11ድህነትህ እንደ ወንበዴ፣ ችግርህም መሳርያ እንደ ታጠቀ ወታደር ይመጣብሃል፡፡
12የማይረባ፣ ክፉ ሰው፣ በጠማማ ንግግሩ ይኖራል፣
13በዓይኑ ይጠቅሳል፣ በእግሩም ምልክት ያስቀምጣል፣ በጣቶቹም ይጠቁማል፡፡
14በልቡ ውስጥ ባለው አጭበርባሪነት ክፋትን ይዶልታል፣ ግጭትንም ሁልጊዜ ይጭራል፡፡
15ስለዚህ ጥፋቱ ሳይታሰብ በቅጽበት ይደርስበታል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደማይድን ሆኖ ይሰበራል፡፡
16እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች አሉ፣ የሚጸየፋቸውም ሰባት ናቸው፡-
17የትዕቢተኛ ሰው አይን፣ ሐሰትን የሚናገር ምላስ፣ የንጹሃን ሰዎችን ደም የሚያፈስስ እጅ፣
18ክፋትን የሚፈጥር ልብ፣ ክፋት ለማድረግ በፍጥነት የሚሮጥ እግር፣
19ውሸትን የሚለፈልፍ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ብጥብጥ የሚዘራ ሰው፡፡
20ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትዕዛዝ ፈጽም፣ የእናትህንም ትምህርት አትተው፡፡
21ሁልጊዜ በልብህ አኑራቸው፣ በአንገትህም ዙርያ እሰራቸው፡፡
22ስትሄድ፣ ይመሩሃል፤ በተኛህ ጊዜ ይጠብቁሃል፤ በነቃህም ጊዜ ያስተምሩሃል፡፡
23ትዕዛዛቱ መብራት ናቸው፣ ትምህርቱም ብርሃን ነው፤ የተግሳጽም ዘለፋዎች የሕይወት መንገድ ናቸውና፡፡
24ከምግባረ ብልሹ ሴት፣ ከአመንዝራ ሴትም ጣፋጭ ቃላት ይጠብቅሃል፡፡
25በልብህ ውበቷን አትመኝ፣ በሽፋሽፍትዋም አትጠመድ፡፡
26ከጋለሞታ ሴት ጋር መተኛት የአንድ ቁራሽ ዳቦ ዋጋ ያሳጣሃል፤ ከሌላ ሰው ሚስት ጋር መተኛት ግን ሕይወትህን ያሳጣሃል፡፡
27አንድ ሰው ልብሱ ሳይቃጠል በደረቱ እሳት መያዝ ይችላልን?
28አንድ ሰው እግሩ ሳይቃጠል በፍም ላይ መራመድ ይችላልን?
29ከጎረቤቱ ሚስት ጋር የሚተኛም ሰው እንዲሁ ነው፤ ከእርሷ ጋር የሚተኛም ሳይቀጣ አይቀርም፡፡
30ሌባ በተራበ ጊዜ ፍላጎቱን ለማሟላት ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም፡፡
31ሆኖም ሌባው ሲሰርቅ ከተያዘ፣ የሰረቀውን ሰባት እጥፍ ይመልሳል፤ በቤቱም ያለውን ንብረት ሁሉ መስጠት አለበት፡፡
32የሚያመነዝር ሰው አእምሮው አያመዛዝንም፤ እንዲህ የሚያደርግ ራሱን ያጠፋል፡፡
33ቁስልና ውርደት ይገባዋል፣ ውርደቱም አይደመሰስለትም፡፡
34ቅናት ሰውን ቁጡ ያደርገዋልና፤ በሚበቀልበት ጊዜ ምህረትን አያደርግም፡፡
35እርሱ ምንም ዓይነት ካሳ አይቀበልም፣ ብዙ ስጦታዎችን ብታቀርብለትም እሺ አይልም፡፡