1ልጄ ሆይ፣ ለጥበቤ ትኩረት ስጥ፤ የማስተዋል ቃሌንም በጥንቃቄ አድምጥ፡፡
2ይህም ልባምነትን ትማር ዘንድ፣ ከንፈሮችህም እውቀትን ይጠብቁ ዘንድ ነው፡፡
3የአመንዝራ ሴት ከንፈር ማርን ያንጠባጥባልና፣ አንደበቷም ከዘይት ይልቅ የለሰለሰ ነውና፣
4ነገር ግን ፍጻሜዋ እንደ እሬት መራራ ናት፣ እንደ ስለታም ሰይፍ የምትቆርጥ ናት፡፡
5እግሮቿ ወደ ሞት ይወርዳሉ፣ እርምጃዎቿም ወደ ሲኦል መንገድ ይሄዳሉ፡፡
6ስለ ሕይወት መንገድ ምንም አታስብም፡፡ አረማመዷ የተቅበዘበዘ ነው፣ ወዴት እንደምትሄድም አታውቅም፡፡
7አሁንም ልጆቼ ሆይ፣ አድምጡኝ፣ የአፌን ቃል ከማድመጥ ፈቀቅ አትበሉ፡፡
8መንገድህን ከእርሷ አርቅ፣ ወደ ቤቷም በር አትቅረብ፡፡
9እንዲህ ካደረግህ ክብርህን ለሌሎች ሰዎች፣ የሕይወት ዘመንህንም ለጨካኝ ሰው አሳልፈህ አትሰጥም፤
10ባዕዳን በሀብትህ አይፈነጥዙም፣ የደከምክበት ነገር ወደ ባዕዳን ቤት አይገባም፡፡
11በሕይወትህ መጨረሻ ስጋህና ሰውነትህ ሲጠፋ ታቃስታለህ፡፡
12እንዲህም ትላለህ፡- “ተግሳጽን እንዴት ጠላሁ፣ መታረምን ልቤ ናቀ!
13አስተማሪዎቼን አልታዘዝሁም፣ አሰልጣኞቼንም አላደመጥሁም፡፡
14በጉባኤና ሰዎች በተሰበሰቡበት መካከል ሙሉ በሙሉ ወደ ጥፋት ተቃርቤ ነበር፡፡”
15ከማጠራቀሚያህ ውሃ ጠጣ፣ ከጉድጓድህም የሚፈልቀውን ውሃ ጠጣ፡፡
16ምንጮችህ በሁሉም ቦታ ያለገደብ ሊፈስሱ፣ ወንዞችህስ በአደባባዩ ሁሉ ሊጎርፉ ይገባልን?
17እነርሱ ለአንተ ብቻ ይሁኑ፣ ከአንተ ጋር ላሉ ባዕዳን አይሁኑ፡፡
18ምንጭህ የተባረከ ይሁን፣ በወጣትነት ሚስትህም ደስ ይበልህ፡፡
19ምክንያቱም እርሷ በፍቅር እንደተሞላች ዋላ፣ ግርማ ሞገስ እንዳላትም ሚዳቋ ናት፡፡ ጡቷም ሁልጊዜ ያስደስትህ፣ ሁልጊዜም በፍቅሯ ተማረክ፡፡
20ልጄ ሆይ፣ ስለምን በጋለሞታ ሴት ትማረካለህ፤ የሌላይቱንስ ሴት ሰውነት ለምን ታቅፋለህ?
21እግዚአብሔር ሰው የሚሰራውን በሙሉ ያያል፣ የሚሄድበትንም መንገድ ሁሉ ይመለከታል፡፡
22ክፉ ሰው በራሱ ኃጢአት ይጠመዳል፤ የኃጢአቱም ገመድ አጥብቆ ይይዘዋል፡፡
23አልተቀጣምና ይሞታል፤ ከሞኝነቱም ብዛት የተነሳ መንገድ ይስታል፡፡