1ልጆች ሆይ፣ የአባትን ተግሳጽ አድምጡ፣ ማስተዋል ምን እንደሆነ እንድታውቁ ልብ በሉ፡፡
2እኔ መልካም ትምህርት እሰጣችኋለሁ፣ ትምህርቴን አትተዉ፡፡
3የአባቴ ልጅ ሳለሁ፣ ለእናቴም ተወዳጅና ብቸኛ ልጅ ሳለሁ፣
4አባቴ አስተማረኝ፣ እንዲህም አለኝ፡- “ቃሎቼን ሁሉ በልብህ ያዝ፤ ሕግጋቴን ጠብቅ በሕይወትም ኑር፡፡”
5ጥበብንና ማስተዋልን አግኝ፤ የአፌን ቃላቶች አትርሳ፣ እነርሱንም አትተው፤
6ጥበብን አትተዋት፣ እርሷ ከለላ ትሆንሃለች፤ ውደዳት፣ ትጠብቅሃለች፡፡
7ጥበብ እጅግ በጣም ጠቃሚ ናት፣ ስለዚህ ጥበብን አግኛት፣ ያለህን ሀብት ሁሉ ከፍለህ ማስተዋልን የራስህ አድርጋት፡፡
8ለጥበብ ከፍተኛ ስፍራ ስጣት፣ እርሷም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ እርሷን አጥብቀህ ስትይዛት ታከብርሃለች፡፡
9በራስህ ላይ የክብር አክሊል ታስቀምጥልሃለች፤ ውብ የሆነ ዘውድም ትሰጥሃለች፡፡
10ልጄ ሆይ፣ አድምጠኝ፣ ለቃሎቼም ትኩረት ስጥ፣ በሕይወት ዘመንህም ብዙ አመታት ይጨመሩልሃል፡፡
11በጥበብ ጎዳና አስተምርሃለሁ፤ በቀጥተኛ መንገዶችም እመራሃለሁ፡፡
12በምትራመድበት ጊዜ ማንም በመንገድህ ላይ አይቆምም፣ በሮጥህ ጊዜ አትሰናከልም፡፡
13ምክርን ያዝ፣ አትልቀቀው፤ ጠብቀው፣ እርሱ ሕይወትህ ነውና፡፡
14የክፉዎችን መንገድ አትከተል፣ ክፋትን በሚያደርጉ ሰዎች መንገድ አትሂድ፡፡
15ከእርሷ ራቅ፣ በዚያ አትሂድ፤ ከዚያ ተመለስ፣ በሌላ መንገድ ሂድ፡፡
16ክፋትን እስኪፈጽሙ ድረስ መተኛት አይችሉምና፣ አንድ ሰው እስኪያሰናክሉ ድረስ እንቅልፋቸው አይመጣምና፡፡
17የክፋትን እንጀራ ይበላሉና፣ የአመጽንም ወይን ጠጅ ይጠጣሉና፡፡
18ጽድቅን የሚያደርግ ሰው መንገድ ግን እየፈካ እንደሚሔድ የንጋት ብርሃን ነው፤ ሙሉ ቀን እስከሚሆን ድረስ ብርሃኑ የበለጠ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
19የክፉዎች መንገድ ግን እንደ ጨለማ ነው፣ምን እንደሚያሰናክላቸው በፍጹም አያውቁም፡፡
20ልጄ ሆይ፣ ቃሎቼን ልብ በል፣ ንግግሮቼን አድምጥ፡፡
21ከአይኖችህ አይራቁ፣ በልብህ ውስጥ ጠብቃቸው፡፡
22ቃሎቼ ለሚያገኘኟቸው ሰዎች ሕይወት፣ ለመላው ሰውነታቸውም ፈውስ ናቸውና፡፡
23ልብህን በጥንቃቄ ጠብቅ፣ በትጋትም ከልለው፣ የሕይወት ምንጭ የሚፈልቀው ከእርሱ ነውና፡፡
24ጠማማ ንግግርን ከአንተ አስወግድ፣ ብልሹ ወሬ ከአንተ አርቅ፡፡
25ዓይኖችህ ወደ ፊት በቀጥታ ይመልከቱ፣ በቀጥታ ፊት ለፊት አተኩረህ እይ፡፡
26ለእግርህ ደልዳላ ጎዳና አበጅለት፤ ከዚያ በኋላ መንገድህ በሙሉ አስተማማኝ ይሆናል፡፡
27ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ አትበል፤ እግርህን ከክፉ መልስ፡፡