1ልጄ ሆይ፣ ትእዛዛቴን አትርሳ፣ ትምህርቴንም በልብህ ጠብቅ፣
2በሕይወትህ ብዙ ቀኖችንና ዓመቶችን እንደዚሁም ሰላምን ይጨምሩልሃል፡፡
3በኪዳን የተመሰረተ ታማኝነትና እውነተኛነት አይለዩህ፣ በአንገትህ ዙርያ በአንድ ላይ እሰራቸው፣ በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው፡፡
4በዚያን ጊዜ ሞገስና መልካም ስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ታገኛለህ፡፡
5በሙሉ ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል ላይ አትደገፍ፤
6በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም መንገድህን ቀና ያደርገዋል፡፡
7በራስህ አስተያየት ጥበበኛ አትሁን፤ እግዚብሔርን ፍራ፣ ከክፉም ራቅ፡፡
8ይህም ለስጋህ ፈውስ፣ ለሰውነትህም መታደስ ይሆንልሃል፡፡
9እግዚአብሔርን በሀብትህና በምርትህ ሁሉ በኩራት አክብረው፣
10ጎተራህ ሙሉ ይሆናል፣ ገንዳህ ደግሞ በአዲስ ወይን ጠጅ ተትረፍርፎ ይሞላል፡፡
11ልጄ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቅጣት አትናቅ፣ ተግሳጹንም አትጥላ፣
12አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ እንደዚሁ እግዚአብሔርም የሚወዳቸውን ይቀጣልና፡፡
13ጥበብን የሚያገኛት ሰው ደስተኛ ነው፣ እውቀትንም ያገኛል፡፡
14ከጥበብ የምታገኘው ጥቅም ብር ከሚሰጥህ ትርፍ ይልቅ እጅግ ይበልጣል፣ የጥበብ ትርፍ ከወርቅም ይበልጣል፡፡
15ጥበብ ከከበረ ዕንቁ ይልቅ እጅግ ውድ ናት፣ አንተ ከምትመኘው ነገር ሁሉ እርሷን የሚተካከላት ምንም ነገር የለም፡፡
16በቀኝ እጇ ረጅም ዕድሜ አለ፤ በግራ እጇ ደግሞ ባለጠግነትንና ክብርን ይዛለች፡፡
17መንገዷ የደግነት መንገድ ነው፣ ጎዳናዋም ሰላም ነው፡፡
18እርሷ አጥብቀው ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፣ የሚደገፉባትም ደስተኞች ናቸው፡፡
19እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሰረተ፣ ሰማያትን ደግሞ በማስተዋል አጸና፡፡
20በእወቀቱ ጥልቆች ተሰንጥቀው ተከፈቱ፣ ደመናትም ጠልን አንጠበጠቡ፡፡
21ልጄ ሆይ፣ ትክክለኛ ፍርድንና ነገሮችን በሚገባ መለየትን ጠብቅ፣ እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፡፡
22እነዚህ ለነፍስህ ሕይወት፣ በአንገትህ ዙርያ የምታስራቸው የሞገስ ጌጥ ይሆናሉ፡፡
23በዚያን ጊዜ በመንገድህ ተማምነህ በሰላም ትራመዳለህ፣ እግርህም አይሰናከልም፤
24በምትተኛበት ጊዜ አትፈራም፤ ስትተኛ እንቅልፍህ ጣፋጭ ይሆናል፡፡
25በድንገተኛ ሽብርና በክፉዎች አማካይነት በሚደርስ ጥፋት አትፍራ፣
26እግዚአብሔር በአጠገብህ ይሆናልና፣ እግርህም በወጥመድ እንዳያያዝ ይጠብቅሃልና፡፡
27ልታደርግ የሚቻልህ ሲሆን፣ ለሚገባቸው ሰዎች መልካምን ነገር ከማድረግ አትከልክል፡፡
28አሁን በእጅህ ገንዘብ እያለ ለጎረቤትህ “አሁን ሂድ፣ እንደገና ተመልሰህ ና፣ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው፡፡
29በአጠገብህ የሚኖረውንና በአንተ የሚተማመነውን ጎረቤትህን ለመጉዳት አትምከርበት፡፡
30አንድ ሰው አንተን ለመጉዳት ክፉ ካልሰራብህ ያለ በቂ ምክንያት ከዚህ ሰው ጋር አትከራከር፡፡
31በክፉ ሰው አትቅና፣ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ፡፡
32ጠማማ ሰው በእግዚብሔር ፊት የተጠላ ነውና፣ ቅን ሰውን ግን ወዳጁ ያደርገዋል፡፡
33የእግዚአብሔር እርግማን በክፉ ሰዎች ቤት ላይ ነው፣ የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል፡፡
34እርሱ በፌዘኞች ላይ ያፌዛል፣ ለትሁታን ግን ሞገሱን ይሰጣቸዋል፡፡
35ጥበበኞች ክብርን ይወርሳሉ፣ የሞኞች ከፍታ ግን ውርደታቸው ነው፡፡