1የያቄ ልጅ የአጉር ቃል፡- ይህ ሰው ለኢቲኤል፣ ለኢቲኤልና ለኡካል ተናገረ፡-
2በእርግጠኝነት እኔ ከሰው ሁሉ ይልቅ እንደ እንስሳ ሞኝ ነኝ፣ የሰው ልጅ ማስተዋልም የለኝም፡፡
3ጥበብን አልተማርሁም፣ ስለ ቅዱሱም እውቀት የለኝም፡፡
4ወደ ሰማይ ከፍ ብሎ የሄደና ወደታች የተመለሰ ማን ነው? ነፋሳትን በእጁ መዳፍ ሰብስቦ የያዘ ማን ነው? ውሆችንስ በካባው ላይ የሰበሰበ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ስሙ ማን ነው፣ የልጁስ ስም ማን ነው? አንተ በእርግጠኝነት ታውቃለህ!
5የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትኗል፣ በእርሱ ለሚታመኑ ጋሻ ነው፡፡
6በቃሉ ላይ ምንም አትጨምር፣ አለዚያ ይገስጽሃልና፣ ሐሰተኛም ትሆናለህ፡፡
7ሁለት ነገር እጠይቅሃለሁ፣ ከመሞቴም በፊት እነዚህን ነገሮች አትከልክለኝ፡
8ከንቱነትንና ውሸትን ከእኔ አርቅ፡፡ ድህነትንም ብልጽግናንም አትስጠኝ፣ የሚያስፈልገኝን መብል ብቻ ስጠኝ፡፡
9ብዙ ሃብት ካለኝ፣ አንተን ከድቼ “እግዚአብሔርን ማን ነው?” እላለሁና፣ ድሃ ከሆንኩኝ ደግሞ እሰርቃለሁ፣ የአምላኬንም ስም አሰድባለሁና፡፡
10አገልጋዩን በጌታው ፊት ስሙን አታጥፋ፣ ይረግምሃል አንተም በደለኛ ሆነህ ትገኛለህና፡፡
11አባቱን የሚረግም፣ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ፣
12ይህ ትውልድ ራሱን ንጹህ አድርጎ የሚያይ፣ ነገር ግን ከእድፉ ያልጸዳ ትውልድ ነው፡፡
13ይህ ትውልድ ዓይናቸው ምንኛ ትዕቢተኛ ነው፣ ሽፋሽፍቶቻቸውም ምንኛ ወደ ላይ ከፍ ያሉ ናቸው!
14ጥርሳቸው ሰይፍ የሆነ፣ መንጋጋቸውም ካራ የሆነ ትውልድ ናቸው፣ ድሆችን ከምድር፣ ችግረኞችንም ከሰው ልጆች መካከል ያጠፉ ዘንድ፡፡
15አልቅት “ስጡን፣ ስጡን” እያሉ የሚጮሁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉት፡፡ ፈጽሞ የማይጠግቡ ሦስት ነገሮች አሉ፣ ፈጽሞ “በቃኝ” የማይሉ አራት፤
16እነርሱም ሲኦል፣ የማትወልድ ማህጸን፣ ውሃ የተጠማች መሬትና፣ “በቃኝ” የማትል እሳት ናቸው፡፡
17በአባት ላይ የሚያፌዝ ለእናት መታዘዝን የሚንቅ ዓይን፣ ዓይኑ በሸለቆ አሞራዎች ይጎጠጉጡአታል፣ በአሞራዎችም ይበላል፡፡
18እጅግ የሚያስደንቁኝ ሦስት ነገሮች አሉ፣ አራት ደግሞ ፈጽሞ የማላስተውለው፡-
19የንስር መንገድ በሰማይ ውስጥ፤ የእባብ መንገድ በቋጥኝ ላይ፤ የመርከብ መንገድ በባህር ልብ ውስጥ፤ የሰውም መንገድ ከወጣት ሴት ጋር ናቸው፡፡
20ይህም የአመንዝራ ሴት መንገድ ነው፣ ትበላለች አፏንም ትጠርጋለች፣ “ምንም ስህተት አልሰራሁም” ትላለች፡፡
21በሶስት ነገሮች ምድር ትናወጣለች፣ አራተኛውንም መቋቋም አትችልም፡-
22ባርያ ንጉስ ሲሆን፤ ሞኝ በመብል በጠገበ ጊዜ፤
23የተጠላች ሴት ትዳር ስትይዝና፤ የቤት ሰራተኛ የእመቤቷን ቦታ ስትወስድ፡፡
24በምድር ላይ አራት ነገሮች ትንሽ ናቸው፣ ሆኖም እጅግ ጥበበኞች ናቸው፡-
25ጉንዳኖች ጠንካራ ያልሆኑ ፍጡራን ናቸው፣ ነገር ግን ምግባቸውን በበጋ ያዘጋጃሉ፤
26ሽኮኮዎች ብርቱ ያልሆኑ ፍጡሮች ናቸው፣ ነገር ግን ቤታቸውን በአለት ውስጥ ይሰራሉ፡፡
27አንበጣዎች ንጉስ የላቸውም፣ ነገር ግን ሁሉም በሰልፍ ይሄዳሉ፡፡
28እንሽላሊቶችም በሁለት እጅህ ልትይዛቸው ትችላለህ፣ ይሁን እንጂ በነገስታት ቤተ መንግስታት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
29ግርማ ሞገስ ያለው አረማመድ ያላቸው ሶስት ነገሮች አሉ፣ በአካሄዳቸው ግርማ ሞገስ ያላቸው አራት አሉ፡-
30አንበሳ፣ ከዱር እንስሳት ሁሉ ብርቱ የሆነና ከምንም ነገር ወደኋላ የማይመለስ ነው፤
31እየተንጎራደደ የሚሄድ አውራ ዶሮ፤ ፍየል፤ እና በወታደሮቹ የታጀበ ንጉስ ናቸው፡፡
32ሞኝ ከሆንህ፣ ራስህንም ከፍ ከፍ የምታደርግ ከሆነ ወይም ክፉ ሃሳብን እያሰብክ ከሆነ፣ እጅህን በአፍህ ላይ አድርግ፡፡
33የተናጠ ወተት ቅቤ እንደሚወጣው፣ በጣም የታሸ አፍንጫም ደም እንደሚወጣው፣ በቁጣ የሚፈጸሙ ድርጊቶችም ጠብን ያመጣሉ፡፡