1ብዙ ተግሳጽን ተቀብሎ አንገቱን ያደነደነ ሰው እንደማይድን ሆኖ በቅጽበት ይሰበራል፡፡
2ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎች ሲበዙ፣ ሕዝብ ደስ ይለዋል፣ ክፉ ሰው ገዢ ሲሆን ግን ሕዝብ ያቃስታል፡፡
3ጥበብን የሚወድ ሁሉ አባቱን ደስ ያሰኛል፣ አመንዝራዎች ወዳጅ ግን ሀብቱን ያጠፋል፡፡
4ንጉስ አገሩን በፍትህ ያጸናል፣ ጉቦን የሚፈልግ ግን ያፈራርሳታል፡፡
5ጎረቤቱን የሚሸነግል ሰው ለገዛ እግሩ መረብ እየዘረጋ ነው፡፡
6ክፉ ሰው በራሱ ኃጢአት በወጥመድ ይያዛል፣ ጽድቅን የሚያደርግ ግን ይዘምራል፣ ይደሰታልም፡፡
7ጽድቅን የሚያደርግ ሰው ለድሆች ፍትሕ ይጨነቃል፤ ክፉ ሰው ግን እንዲህ ዓይነት እውቀት የለውም፡፡
8ፌዘኞች ከተማን ያቃጥላሉ፣ ጥበበኞች ግን ቁጣን ይመልሳሉ፡፡
9ጥበበኛ ሰው ከሞኝ ጋር በሚከራከርበት ጊዜ፣ ሞኝ ይቆጣል ይስቃልም፣ እረፍትም አይኖርም፡፡
10ደም የተጠማ ሰው ንጹሐንን ይጠላሉ፣ ቅን የሆነውንም ሕይወት ለማጥፋት ይፈልጋሉ፡፡
11ሞኝ ቁጣውን ሁሉ ይገልጣል፣ ጥበበኛ ሰው ግን ቁጣውን ይቆጣጠራል፣ ራሱንም ያረጋጋል፡፡
12ገዢ ለሐሰተኛ ወሬ ትኩረት የሚሰጥ ከሆነ፣ ሹማምንቶቹ ሁሉ ክፉ ይሆናሉ፡፡
13ድሃና ጨቋኝን አንድ የሚያደርጋቸው አለ፣ እግዚአብሔር ለሁለቱም የዓይን ብርሃንን ሰጥቷቸዋልና፡፡
14ንጉስ ለድሃ በእውነት ከፈረደ፣ ዙፋኑ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፡፡
15በትርና ተግሳጽ ጥበብን ይሰጣሉ፣ ያልተቀጣ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል፡፡
16ክፉ ሰዎች ስልጣን ሲይዙ፣ አመጸኝነት ይጨምራል፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ግን የክፉዎችን ውድቀት ያያሉ፡፡
17ልጅህን ቅጣው እረፍትም ይሰጥሃል፤ ለሕይወትህም ደስታን ያመጣል፡፡
18ትንቢታዊ ራዕይ በሌለበት ሕዝብ መረን ይሆናል፣ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተባረከ ነው፡፡
19አገልጋይ በቃል አይታረምም፣ ቢገባውም ምላሽ አይሰጥም፡፡
20በቃሎቹ የሚቸኩለውን ሰው ተመልክተሃል? ከእርሱ ይልቅ ለሞኝ የበለጠ ተስፋ አለው፡፡
21አገልጋዩን ከወጣትነቱ ጀምሮ የሚያሞላቅቅ፣ በመጨረሻ ችግር ይገጥመዋል፡፡
22ቁጡ ሰው ሁከትን ያነሳሳል፣ ቁጣ የሞላበትም ሰው ብዙ ኃጢአቶችን ይሰራል፡፡
23የሰው ትዕቢት ያዋርደዋል፣ ትሁት መንፈስ ያለው ግን ይከበራል፡፡
24ከሌባ ጋር የሚካፈል ሰው ሕይወቱን ይጠላል፤ እርግማንን ይሰማል መልስ ግን አይሰጥም፡፡
25ሰውን መፍራት ወጥመድ ውስጥ ይከትታል፣ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ይጠበቃል፡፡
26ብዙዎች የገዢን ፊት ይሻሉ፣ ፍትህ ለሰው የሚመጣው ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡
27ፍትህን የሚያጓድል ሰው ጽድቅን በሚያደርጉ ሰዎች ፊት የተጠላ ነው፣ መንገዱ ቅን የሆነ ሰው ግን በክፉዎች የተጠላ ነው፡፡