1ኃጢአተኛ ማንም ሳያባርረው ይሸሻል፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ግን እንደ አንበሳ ደፋር ናቸው፡፡
2በአገር አመጽ ምክንያት ብዙ ገዢዎች አሏት፣ ማስተዋልና እውቀት ባለው ሰው ግን፣ አገር ለረዥም ዘመን ትቆያለች፡፡
3ድሃ ሆኖ ሌሎች ድሆችን የሚያስጨንቅ ሰው፣ ሰብልን እንሚያጠፋ ዶፍ ዝናብ ነው፡፡
4ሕግን የሚተዉ ሰዎች ክፉዎችን ያመሰግናሉ፣ ሕግን የሚጠብቁ ግን ከእነርሱ ጋር ይዋጋሉ፡፡
5ክፉ ሰዎች ፍትህን አያውቁም፣ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ግን ሁሉን ነገር ያውቃሉ፡፡
6በመንገዱ ጠማማ ከሆነ ባለጠጋ ይልቅ፣ በሐቀኝነቱ የሚራመድ ድሃ ሰው ይሻላል፡፡
7ሕግን የሚጠብቅ ማስተዋል ያለው ልጅ ነው፣ የሆዳሞች ጓደኛ ግን አባቱን ያሳፍራል፡፡
8ከፍተኛ ወለድ በመሰብሰብ ሀብቱን የሚያከማች ለድሀዎች ለሚራራ ለሌላ ሰው ሀብቱን ይሰበሰብለታል፡፡
9አንድ ሰው ሕግን ከማድመጥ ጆሮውን የሚያዞር ከሆነ፣ ጸሎቱ እንኳ የተጠላ ነው፡፡
10ቅኑን ሰው ወደ ክፋት መንገድ የሚመራ ሁሉ ራሱ በቆፈረው ጉድጓድ ይገባል፣ ንጹሐን ግን መልካምን ነገር ይወርሳሉ፡፡
11ባለጠጋ ሰው በራሱ ዓይኖች ጥበበኛ ሊሆን ይችላል፣ አስተዋይ የሆነ ድሃ ሰው ግን እርሱን ይመረምረዋል፡፡
12ጽድቅን የሚያደርጉ ድል በሚያገኙበት ጊዜ፣ ታላቅ ክብር አለ፣ ክፉዎች በሚነሱበት ጊዜ ግን ሰዎች ራሳቸውን ይሸሽጋሉ፡፡
13ኃጢአቱን የሚሸሽግ አይሳካለትም፣ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምህረትን ያገኛል፡፡
14ዘወትር እግዚአብሔርን እየፈራ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፣ ልቡን የሚያደነድን ግን ወደ መከራ ይወድቃል፡፡
15እንደሚያገሳ አንበሳ ወይም እንደ ተቆጣ ድብ በድሆች ላይ የሚገዛ ክፉ ገዥም እንዲሁ ነው፡፡
16ማስተዋል የሌለው ገዥ በጭካኔ የሚያስጨንቅ ነው፣ ማታለልን የሚጠላ ግን እድሜውን ያረዝማል፡፡
17አንድ ሰው የሌላውን ደም በማፍሰሱ ምክንያት በደለኛ ከሆነ፣ እስከ ሞቱ ቀን ድረስ ኮብላይ ይሆናል፣ ማንም ሰው አይረዳውም፡፡
18በሐቀኝነት የሚራመድ ሰው በደህና ይጠበቃል፣ መንገዱ በጠማማነት የተሞላ ግን በድንገት ይወድቃል፡፡
19መሬቱን የሚያርስ ሰው ብዙ መብል ይኖረዋል፣ የማይጠቅም ሞያ የሚከተል ግን እጅግ በጣም ይደኸያል፡፡
20ታማኝ ሰው ታላቅ በረከት ያገኛል፣ በጥድፊያ ሃብታም የሆነ ግን ሳይቀጣ አይቀርም፡፡
21አድልዎን ማሳየት መልካም አይደለም፣ ነገር ግን ለቁራጭ ዳቦ ሲል ሰው ስህተትን ይሰራል፡፡
22ስስታም ሰው ሐብትን ያሳድዳል፣ ድህነት በላዩ ላይ እንደሚመጣ ግን አያውቅም፡፡
23ሰውን በምላሱ ከሚያሞግስ ይልቅ የሚገስጽ ሰው በኋላ ውሎ አድሮ ከገሰጸው ሰው ብዙ ሞገስ ያገኛል፡፡
24አባቱንና እናቱን ሰርቆ “ኃጢአት አይደለም” የሚል ሰው የአጥፊ ተባባሪ ነው፡፡
25ስግብግብ ሰው ግጭትን ያነሳሳል፣ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ይባረካል፡፡
26በራሱ ልብ የሚታመን ሰው ሞኝ ነው፣ በጥበብ የሚራመድ ግን ከአደጋ ይርቃል፡፡
27ለድሃ የሚሰጥ ምንም ነገር አይጎድልበትም፣ በድሆች ላይ ዓይኖቹን የሚከድን ሰው ግን ብዙ እርግማን ይቀበላል፡፡
28ክፉ ሰዎች ሲነሱ፣ ሰዎች ራሳቸውን ይሸሽጋሉ፣ ክፉ ሰዎች ሲጠፉ ግን፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ይበዛሉ፡፡