መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ምሳሌ 27

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ነገ በሚሆነው አትመካ፣ ቀኑ የሚያመጣው ምን እንደሆነ አታውቅምና፡፡
2ሌላ ያመስግንህ እንጂ በራስህ አፍ ራስህን አታመስግን፤ የማያውቅህ ሰው እንጂ የራስህ ከንፈሮች አያመስግኑህ፡፡
3የድንጋይን ክብደትና የአሸዋንም ክብደት አስብ፣ የሞኝ ሰው ትንኮሳ ግን ከሁለቱም እጅግ የከበደ ነው፡፡
4የንዴት ጨካኝነትና የቁጣ ጎርፍ አለ፣ በቅናት ፊት መቆም የሚችል ግን ማን ነው?
5ከተሰወረ ፍቅር ይልቅ የተገለጠ ተግሳጽ ይሻላል፡፡
6የጓደኛ ማቁሰል የታመኑ ናቸው፣ ጠላት ግን ከመጠን በላይ ይስማል፡፡
7በጣም ጠግቦ የበላ ሰው የማር ወለላንም አይቀበልም፣ ለራበው ሰው ግን ማንኛውም መራራ ነገር እንኳ ጣፋጭ ነው፡፡
8ከጎጆዋ ወጥታ የምትንከራተት ወፍ ከመኖሪያው አካባቢ ወጥቶ እንደሚባዝን ሰው ናት፡፡
9ሽቶና እጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፣ የጓደኛ ጣፋጭነት ግን ከምክሩ ይበልጣል፡፡
10በችግርህ ጊዜ ጓደኛህንና የጓደኛህን አባት ትተህ ወደ ወንድምህ ቤት አትሂድ፡፡ በቅርብ ያለ ወዳጅ በሩቅ ካለ ወንድም ይሻላልና፡፡
11ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኛት፤ በዚያን ጊዜ ለሚያፌዝብኝ ሰው እኔ መልስ እሰጣለሁ፡፡
12ጥንቁቅ ሰው ችግር ሲያይ ራሱን ይሸሽጋል፣ አላዋቂዎች ግን ቀድመው ሄደው በችግሩ ምክንያት ይጎዳሉ፡፡
13ለማይታወቅ ሰው ብድር በዋስትና ገንዘብ ያስያዘውን ሰው ልብስ ውሰድበት፤ ዝሙት ለምትፈጽም ሴት ዋስትና አስይዞ ከሆነ ውሰድበት፡፡
14ጎረቤቱን በማለዳ ድምጹን በጣም ከፍ አድርጎ የሚባርክ ሰው፣ ባርኮቱ እንደ እርግማን ይቆጠራል!
15ጠበኛ ሚስት በዝናብ ቀን እንደማያቋርጥ ነጠብጣብ ናት፤
16እሷን ማቆም ንፋስን እንደማቆም ወይም ዘይትን በቀኝ እጅህ ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው፡፡
17ብረት ብረትን ይስለዋል፤ በተመሳሳይ መንገድ ሰው ጓደኛውን ይስለዋል፡፡
18የበለስ ዛፍ የሚጠብቅ ፍሬውን ይበላል፣ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል፡፡
19ውኃ የሰውን ፊት እንደሚያሳይ፣ የሰው ልብ ሰውየውን ያሳያል፡፡
20ሲዖልና የሙታን ዓለም መቼም እንደማይጠግቡ፣ የሰውም ዓይኖች መቼም አይጠግቡም፡፡
21ማቅለጫ ለብር ከውርም ለወርቅ ነው፣ ሰውም በሚመሰገንበት ጊዜ ይፈተናል፡፡
22ሰነፍን ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠውም፣ ሞኝነቱ ግን እርሱን አይለቀውም፡፡
23የመንጋህን ሁኔታ በእርግጠኝነት እወቅ፣ ስለ ከብቶችህም ግድ ይበልህ፣
24ሐብት ለዘላለም አይኖርምና፡፡ ዘውድ ለትውልድ ሁሉ ይጸናልን?
25የነበረው ሳር ጠፍቶ፣ አዲሱ ቡቃያ አድጎ ሲታይ፣ በተራሮች ደግሞ ለከብቶች የሚሆን መብል ተሰብስቦ ይገባል፡፡
26ለልብስህ የሚሆን ከበጎች ታገኛለህ፣ ለእርሻህ ዋጋ የሚሆን ደግሞ ከፍየሎችህ ታገኛለህ፡፡
27ለአንተና ለቤተሰብህ መብል፣ ሴት አገልጋዮችህንም ለመመገብ የሚበቃ የፍየሎች ወተት ይኖራል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።