1እነዚህ የይሁዳ ንጉስ፣ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዷቸው ተጨማሪ የሰለሞን ምሳሌዎች ናቸው፡፡
2ነገርን መሰወር የእግዚአብሔር ክብር ነው፣ የነገስታት ክብር ግን ነገርን መርምሮ ማውጣት ነው፡፡
3ሰማያት ከፍ ያሉ እንደሆኑ፣ ምድርም ጥልቅ እንደሆነች ሁሉ፣ የነገስታት ልብም አይመረመርም፡፡
4ቆሻሻውን ከብር አስወግድ፣ የብረት ሰራተኛውም ብሩን ለእጅ ሙያው ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
5እንደዚሁ ክፉ ሰዎችን ከንጉስ ፊት አርቃቸው፣ ዙፋኑ ጽድቅን በማድረግ ይጸናል፡፡
6በንጉስ ፊት ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፣ ለታላቅ ሰዎች መቆሚያ በተዘጋጀም ስፍራ ላይ አትቁም፡፡
7በተከበሩ ሰዎች ፊት ከምትዋረድ ይልቅ፣ እርሱ “ወደዚህ ና” ቢልህ ይሻላል፡፡ ያየኸውን ነገርም፣
8ወደ ፍርድ ፈጥነህ አታምጣው፡፡ ጎረቤትህ ባሳፈረህ ጊዜ በመጨረሻ ምን ታርጋለህ?
9ጉዳይህን በአንተና በጎረቤትህ መካከል ተከራከር፣ የሌላ ሰው ምስጢር ግን አታውጣ፣
10አለበለዚያ ግን አንተን የሰማ ሰው በአንተ ላይ ሃፍረትን ያመጣብሃል፣ ስለ አንተም ልትመልሰው የማትችለው መጥፎ ወሬ ይወራብሃል፡፡
11በጥንቃቄ የተመረጠ ቃል መናገር፣ በብር ላይ እንደተቀረጻ የወርቅ ንድፍ ነው፡፡
12ለሚሰማ ጆሮ የጥበበኛ ተግሳጽ እንደ ወርቅ ቀለበት፣ ከንጹህ ወርቅም እንደተሰራ ጌጥ ነው፡፡
13በምርት መሰብሰቢያ ወቅት እንዳለ የበረዶ ቅዝቃዜ ታማኝ መልዕክተኛ ለላኩት ሰዎች እንዲሁ ነው፤ የጌቶቹን ሕይወት ይመልሳል፡፡
14የማይሰጠውን ስጦታ እሰጣለሁ ብሎ የሚመካ ሰው ዝናብ እንደሌለው ደመናና ንፋስ ነው፡፡
15በትዕግስት ገዢን እንዲለዝብ ማድረግ ይቻላል፣ መልካም ምላስም አጥንትን ትሰብራለች፡፡
16ማር ካገኘህ፣ ለአንተ በቂ የሆነውን ብላ፣ አለበለዚያ ግን ከመጠን በላይ ከበላህ ትተፋዋለህ፡፡
17ወደ ጎረቤትህ ቤት እግር አታብዛ፣ ሊሰለችህና ሊጠላህ ይችላልና፡፡
18በጎረቤቱ ላይ በሐሰት የሚመሰክር ሰው በጦርነት ላይ ጥቅም ላይ እንደሚውል ዱላ፣ ሰይፍ ወይም የተሳለ ቀስት ነው፡፡
19በችግር ጊዜ የታመንከው ወስላታ ሰው እንደ ተበላሸ ጥርስ ወይም እንደሚያነክስ እግር ነው፡፡
20ላዘነ ልብ መዝሙር የሚዘምር፣ በብርድ ጊዜ ልብሱን እንደሚያወልቅ ወይም በሶዳ ላይ ኮምጣጤ እንደሚጨምር ነው፡፡
21ጠላትህ ቢራብ እንዲበላ ምግብ ስጠው፣ ቢጠማም እንዲጠጣ ውኃ ስጠው፣
22በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህና፣ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይከፍልሃልና፡፡
23የሰሜን ንፋስ በእርግጠኝነት ዝናብን ይዞ እንደሚመጣ፣ ሚስጥርን የሚያባክን ሰው ሰዎችን ያስቆጣል፡፡
24ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር በጣራ ማእዘን ላይ ተጠግቶ መኖር ይሻላል፡፡
25ለተጠማ ሰው ቀዝቃዛ ውሃ እንደሚያረካው ሁሉ፣ ከሩቅ አገር የመጣ የምስራችም እንዲሁ ነው፡፡
26በክፉ ሰዎች ፊት የሚንበረከክ መልካም ሰው፣ እንደ ተበከለ ፈሳሽና እንደተበላሸ ምንጭ ነው፡፡
27እጅግ በጣም ብዙ ማር መብላት ጥሩ አይደለም፤ በክብር ላይ ክብር እንደመፈለግ ነው፡፡
28ራሱን መግዛት የማይችል ሰው እንደፈረሰችና ቅጥር እንደሌላት ከተማ ነው፡፡