1ክፉ በሆኑ ሰዎች አትቅና፣ ከእነርሱም ጋር ለመተባበር አትፈልግ፣
2ምክንያቱም ልባቸው ግጭትን ያሴራል፣ ከንፈራቸውም ችግርን ያወራል፡፡
3ቤት በጥበብ ይሰራል፣ በማስተዋልም ይጸናል፡፡
4በእውቀትም ውድና ባማሩ እቃዎች ክፍሎቹ ይሞላሉ፡፡
5ጥበበኛ ሰው ብርቱ መሆኑን ያረጋግጣል፣ እውቀት ያለውም ሰው ከጠንካራ ሰው ይልቅ ይሻላል፣
6በጥበበኛ ምክር ጦርነትህን መዋጋት ትችላለህ፣ በብዙ አማካሪዎችም ድል ይገኛልና፡፡
7ለሞኝ ሰው ጥበብ እጅግ ትርቃለች፤ በበርም አፉን አይከፍትም፡፡
8ክፋትን ለማድረግ የሚያስብ አንድ ሰው አለ፣ ሰዎችም የተንኮል አለቃ ብለው ይጠሩታል፡፡
9የስንፍና እቅድ ኃጢአት ነው፣ ሰዎችም ፌዘኛን ይንቁታል፡፡
10በችግር ጊዜ ፍርሃትህን ካሳየህ፣ እንግዲያው አቅምህ ትንሽ ነው፡፡
11ወደ ሞት የሚወሰዱትን አድናቸው፣ እየተጎተቱ ለመታረድ የሚነዱትንም ይዘህ መልሳቸው፡፡
12አንተም “እዚያ! ስለዚህ ነገር ምንም አናውቅም” ብትል ልብን የሚመረምረው እርሱ ንግግርህን አያስተውለውምን? ሕይወትህን የሚጠብቀው እርሱ አያውቅምን? ለእያንዳንዱ እንደ ስራው መጠን እግዚአብሔር አይሰጠውምን?
13ልጄ ሆይ፣ መልካም ነውና ማር ብላ፣ የማር ወለላ ጠብታዎች ለጣዕምህ ጣፋጭ ናቸው፡፡
14ጥበብም ለነፍስህ እንዲህ ነው፣ ካገኘኸውም፣ ወደፊት ዋስትና ይኖርሃል፣ ተስፋህም አይጠፋም፡፡
15ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎችን ቤት እንደሚዘርፉ ክፉ ሰዎች አድፍጠህ አትጠብቅ፡፡ የጻድቁንም ቤት አታፍርስ፡፡
16ጽድቅን የሚያደርግ ሰው ሰባት ጊዜ ቢወድቅ፣ እንደገና ከወደቀበት ይነሳልና፣ ክፉዎች ግን ይቀሰፋሉ፡፡
17ጠላትህ በወደቀ ጊዜ ደስ አይበልህ፣ በተሰናከለም ጊዜ ልብህ ደስ አይበለው፣
18እግዚአብሔር ያያል፣ ተመልሶም ቁጣውን ከእርሱ ይመልሳልና፡፡
19ክፋትን በሚያደርጉ ሰዎች አትጨነቅ፣ በክፉዎችም አትቅና፣
20ክፉ ሰው ተስፋ የለውምና፣ የክፉ ሰውም መብራት ይጠፋልና፡፡
21እግዚአብሔርን ፍራ፣ ንጉስንም ፍራ፣ ልጄ ሆይ፤ በእነርሱ ላይ ከሚያምጹ ሰዎችም ጋር አትተባበር፣
22ጥፋታቸው በድንገት ይመጣልና፣ ከሁለቱም የሚመጣባቸውን ጥፋት ምን ያህል እንደሆነ ማን ያውቃል?
23እነዚህ ደግሞ የጥበበኛ ሰው ንግግር ናቸው፡፡ በዳኝነት አድልዎ ማድረግ መልካም አይደለም፡፡
24ወንጀለኛውን “ጻድቅ ነህ” የሚለው በሕዝብ ዘንድ ይረገማል፣ በመንግስታትም ዘንድ ይጠላል፡፡
25ነገር ግን በደለኛውን የሚገስጹ ደስታ ይሆንላቸዋል፣ የደግነት ስጦታዎችም ወደ እነርሱ ይመጣሉ፡፡
26እውነተኛ መልስ የሚሰጥ ሰው ከንፈሮችን ይስማል፡፡
27የውጪ ስራህን አዘጋጅ፣ በመስክም ሁሉንም ነገር ለራስህ ዝግጁ አድርግ፣ ከዚያም በኋላ ቤትህን ስራ፡፡
28ያለ ምክንያት በጎረቤትህ ላይ አትመስክር፣ በከንፈሮችህም አታታልል፡፡
29“እርሱ በእኔ ላይ ያደረገውን እኔም በእርሱ ላይ አደርግበታለሁ፤ በእኔ ላይ ላደረገው ነገር ዋጋውን እከፍለዋለሁ” አትበል፡፡
30በሰነፍ ሰው እርሻ በኩል ሄድሁ፣ አእምሮ በሌለውም ሰው የወይን እርሻ አለፍሁ፡፡
31እሾህም በየቦታው በቅሎ ነበር፣ መሬቱም በሳማ ተሸፍኖ ነበር፣ የድንጋይ ካቡም ፈርሶ ነበር፡፡
32ከዚያም አየሁና አሰብኩኝ፤ ተመለከትሁና ተግሳጽን ተቀበልሁ፡፡
33ጥቂት መተኛት፣ ጥቂት እንቅልፍ፣ ጥቂት ለማረፍ እጅን ማጣጠፍ፣
34ድህነት እንደ ሌባ በአንተ ላይ ይመጣል፣ ችግርህም መሳርያ እንደታጠቀ ወታደር ይመጣብሃል፡፡