መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ምሳሌ 22

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ከብዙ ሐብት ይልቅ ጥሩ ስም ይመረጣል፣ ሞገስም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል፡፡
2ሃብታምና ድሃ ሰዎች የሚጋሩት አንድ ነገር አለ፤ ይህም እግዚአብሔር የሁሉም ፈጣሪ መሆኑ ነው፡
3ጠንቃቃ ሰው ችግር ሲያይ ራሱን ይሸሽጋል፣ አላዋቂዎች ግን በዚያው ገፍተው ይሄዳሉ በሱም ምክንያት ይጎዳሉ፡፡
4የትህትናና እግዚአብሔርን የመፍራት ሽልማት ባለጠግነት፣ ክብርና ሕይወት ነው፡፡
5እሾህና አሜኬላ በጠማማ ሰው መንገድ ላይ ይገኛሉ፤ ሕይወቱን የሚጠብቅም ከእነርሱ ይርቃል፡፡
6ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፣ በሸመገለም ጊዜ ከነገርከው መንገድ ፈቀቅ አይልም፡፡
7ባለጠጎች ድሆችን ይገዛሉ፣ ተበዳሪም ለአበዳሪው ባርያ ነው፡፡
8ክፋትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፣ የቁጣውም በትር አይጠቅመውም፡፡
9ቸር አይኖች ያሉት ሰው ይባረካል፣ እንጀራውን ከድሆች ጋር ይካፈላልና፡፡
10ፌዘኛን ከአንተ አርቀው፣ ጠብም ከአንተ ይርቃል፤ ግጭትና ስድብም ይቆማሉ፡፡
11ንጹህ ልብ የሚወድድና ንግግሩም ሞገስ ያለው ሰው፣ ንጉስ ጓደኛው ይሆናል፡፡
12የእግዚአብሔር ዓይኖች እውቀትን ይከታተላሉ፣ የከዳተኞችን ቃሎች ግን ይገለብጣል፡፡
13ሰነፍ ሰው “አንበሳ በመንገድ ላይ አለ! በውጪ ላይ እገደላለሁ” ይላል፡፡
14የአመንዝራ ሴት አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው፤ ወደ እርሱም በሚወድቅ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይሆናል፡፡
15ሞኝነት በሕጻን ልብ ላይ ታስሯል፣ የስርዓት በትር ግን ከእርሱ ያርቀዋል፡፡
16ሀብቱን ለማካበት ወይም ለሀብታሞች ለመስጠት ሲል ድሆችን የሚያስጨንቅ፣ ወደ ድህነት ይመጣል፡፡
17የጠቢብን ቃላት ልብ በል አስተውለህም ስማ፣ ልብህንም ወደ ከእውቀቴ አዘንብል፣
18በውስጥህ ብትጠብቃቸውና ሁሉም በከንፈሮችህ ላይ ዝግጁ ቢሆኑ ለአንተ ደስ ያሰኙሃልና፡፡
19እምነትህ በእግዚአብሔር ላይ ይሆን ዘንድ፣ እነዚህን ለአንተ ዛሬ አስተምርሃለሁ፣ ለአንተም ቢሆን አስተምርሃለሁ፡፡
20ሰላሳ የተግሳጽና የእውቀት ቃሎችን ለአንተ አልጻፍኩልህምን፣
21በእነዚህ ታማኝ ቃሎች እውነትን አስተምርህ ዘንድ፣ አንተም ለላኩህ ታማኝ መልስ ትሰጥ ዘንድ?
22ድሃ በመሆኑ ምክንያት ድሃ ሰው አትዝረፍ፣ ችግረኛውንም በበር ላይ አትግፋው፣
23እግዚአብሔር ለእነርሱ ይፈርድላቸዋልና፣ የዘረፏቸውንም ሰዎች ሕይወት እርሱ ይነጥቃል፡፡
24ግልፍተኛ ሰውን ጓደኛ አታድርግ፣ ቁጣም ካለበት ሰው ጋር አብረህ አትሂድ፣
25አለበለዚያ መንገዱን ትማራለህ፣ ራስህንም በወጥመድ ታጠላልፋለህ፡፡
26ገንዘብን በተመለከተ ግዴታ የሚያስገባ ውል የምትሰጥ አትሁን፣ ለሌሎችም ብድር ዋስ አትሁን፡፡
27መክፈል ካልቻልህ፣ ያንን ሰው አልጋህን ከስርህ ከመውሰድ ሊያቆመው የሚችል ምን ነገር አለ?
28አባቶችህ ያስቀመጡትን የጥንቱን የድንበር የምልክት ድንጋይ አታንሳ፡፡
29በስራው ስልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን? በነገስታት ፊት ይቆማል፤ በተራ ሰዎች ፊትም አይቆምም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።