1የንጉስ ልብ በእግዚአብሔር እጅ እንዳለ የውኃ ፈሳሽ ነው፤ እርሱ ደስ ወዳሰኘው ይመራዋል፡፡
2ለሰው መንገዱ በራሱ ዓይን ፊት ቀና ሊመስለው ይችላል፣ ልብን የሚመዝን ግን እግዚአብሔር ነው፡፡
3ከመስዋዕት ይልቅ ጽድቅንና ፍትሕን ማድረግ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አለው፡፡
4ትቢተኛ ዓይንና ኩሩ ልብ፣ የክፉ ሰውም መብራት፣ ኃጢአት ናቸው፡፡
5የትጉ ሰው እቅዶች ወደ ብልጽግና ይመራሉ፣ በችኮላ የሚያደርግ ሰው ሁሉ ግን ወደ ድህነት ይመጣል፡፡
6በሐሰተኛ ምላስ ሀብትን ማግኘት በኖ የሚጠፋ ተን፣ የሚገድልም ወጥመድ ነው፡፡
7የክፉዎች አመጽ ራሳቸውን ይጠራርጋቸዋል፣ ፍትሕን ማድረግ አይፈቅዱምና፡፡
8የበደለኛ ሰው መንገድ ጠማማ ነው፣ ንጹሕ ሰው ግን ጽድቅን ያደርጋል፡፡
9ከጠበኛ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር በጣራ ማእዘን ላይ ተጠግቶ መኖር ይሻላል፡፡
10የክፉ ሰው ምኞት ክፋትን አጥብቆ ይመኛል፤ ጎረቤቱም በዓይኖቹ ውስጥ ምንም ደግነት አያይም፡፡
11ፌዘኛ ሲቀጣ ፣ እውቀት አልባ ሰው ጥበበኛ ይሆናል፣ ጥበበኛ ሰው ሲገሰጽ፣ እውቀትን ይጨምራል፡፡
12ጽድቅን የሚያደርግ ሰው የክፉውን ቤት ልብ ብሎ ይመለከታል፤ እርሱ ክፉውን ወደ ጥፋት ያወርደዋል፡፡
13የድሆችን ጩኸት የማይሰማ ሰው፣ እርሱም ሲጮህ ማንም አይሰማውም፡፡
14በምስጢር የተደረገ ስጦታ ቁጣን ያበርዳል፣ የተሸሸገ ስጦታም ታላቅ ቁጣን ያጠፋል፡፡
15ፍትሕ በተደረገ ጊዜ ጽድቅን ላደረገው ሰው ደስታን ያመጣለታል፣ ለክፉ አድራጊዎች ግን ሽብር ያመጣባቸዋል፡፡
16ከማስተዋል መንገድ የሳተ ሰው፣ በሙታን ጉባኤ ውስጥ ያርፋል፡፡
17ቅንጦት የሚወድ ሰው ድሃ ይሆናል፤ የወይን ጠጅና ዘይት የሚወድ ደግሞ ባለጠጋ አይሆንም፡፡
18ክፉ ሰው ጽድቅን ለሚያደርግ ሰው ቤዛ ይሆናል፣ ከዳተኛ ሰው ደግሞ ለጻድቅ ቤዛ ነው፡፡
19ጠብ ከምታነሳሳና ያለማቋረጥ ከምታማርር ሴት ጋር ከመኖር በምድረ በዳ መኖር ይሻላል፡፡
20የከበረ ሀብትና ዘይት በጥበበኛ ቤት ይገኛሉ፣ ሞኝ ሰው ግን ያባክናቸዋል፡፡
21ጽድቅን የሚያደርግና ደግ ሰው፣ ይህ ሰው ሕይወትን፣ ጽድቅንና ክብርን ያገኛል፡፡
22ጥበበኛ ሰው ወደ ኃያላን ከተማ ይገባል፣ የምትታመንበት ምሽጓንም ያፈርሳል፡፡
23አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ ሰው ራሱን ከመከራ ይጠብቃል፡፡
24ኩሩና ትዕቢተኛ ሰው ስሙ “ሞኝ” ይባላል፣ እርሱም በእብሪትና በትዕቢት ያደርጋል፡፡
25የሰነፍ ምኞት ራሱን ይገድለዋል፣ እጆቹ ለመስራት አይፈቅዱምና፡፡
26እርሱ ቀኑን በሙሉ ይመኛል፣ ተጨማሪ ይመኛል፣ ጽድቅን የሚያደርግ ግን ይሰጣል፣ አይሰስትምም፡፡
27የክፉዎች መስዋዕት አስጸያፊ ነው፤ በክፉ ሃሳብ ሲያቀርበው ደግሞ የበለጠ አስጸያፊ ነው፡፡
28ሐሰተኛ ምስክር ይጠፋል፣ የሚያዳምጥ ሰው ግን ለሁልጊዜ የሚሆን ይናገራል፡፡
29ክፉ ሰው ራሱን ጠንካራ አስመስሎ ያቀርባል፣ ጻድቅ ሰው ግን ስለ ድርጊቶቹ ይጠነቀቃል፡፡
30እግዚአብሔርን ሊቋቋም የሚችል ጥበብ፣ ማስተዋል ወይም ምክር የለም፡፡
31ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፣ ድል ግን የእግዚአብሔር ነው፡፡