1ወይን ጠጅ ፌዘኛ፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በመጠጥ የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም፡፡
2የንጉስ ቁጣ እንደሚያገሳ ደቦል አንበሳ ቁጣ ነው፤ የሚያስቆጣውም ሰው ሕይወቱን ይከፍላል፡፡
3ጥልን መራቅ ለማንም ሰው ቢሆን ክብር ነው፣ ሞኝ ሰው ግን ወደ ጭቅጭቅ ይገባል፡፡
4ሰነፍ ሰው በመከር ወቅት አያርስም፤ በምርት ጊዜ እህል ይለምናል ነገር ግን ምንም አያገኝም፡፡
5በሰው ልብ ውስጥ ያለ አሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፣ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል፡፡
6ብዙ ሰው ታማኝ እንደሆነ ይናገራል፣ ታማኝ የሆነውን ግን ማን ሊያገኘው ይችላል?
7ጽድቅን የሚያደርግ ሰው በሐቀኝነቱ ይራመዳል፣ ፍለጋውን የሚከተሉ ልጆቹም ደስተኞች ናቸው፡፡
8የዳኛን ተግባር በማከናወን በዙፋኑ ላይ የተቀመጠ ንጉስ በፊቱ ያለውን ክፋት ሁሉ በዓይኖቹ አበጥሮ ይለያል፡፡
9“ልቤን በንጽህና ጠብቄያለሁ፤ ከኃጢአቴ ንጹህ ነኝ” ብሎ መናገር የሚችል ማን ነው?
101የተለያዩ ሚዛኖችና እኩል ያልሆኑ መስፈሪያዎች፣ ሁለቱንም እግዚአብሔር ይጠላቸዋል፡፡
11ወጣት እንኳ ባህርዩ ንጹህና ቅን መሆኑ በስራው ይታወቃል፡፡
12የሚሰሙ ጆሮዎችና የሚያዩ ዓይኖች፣ ሁለቱንም እግዚአብሔር ሰራቸው፡፡
13እንቅልፍን አትውደድ ወደ ድህነት ትመጣለህና፤ ዓይኖችህን ክፈት፣ የተትረፈረፈ መብል ይኖርሃል፡፡
14ዕቃ የሚገዛ ሰው “መጥፎ ነው! መጥፎ ነው!” ይላል፣ በሄደ ጊዜ ግን ይኩራራል፡፡
15ወርቅና ብዙ ውድ ድንጋዮች አሉ፣ የእውቀት ከንፈሮች ግን የከበረ ጌጥ ናቸው፡፡
16ለማይታወቅ ሰው ብድር በዋስትና ገንዘብ ያስያዘውን ሰው ልብስ ውሰድበት፣ ዝሙት ለምትፈጽም ሴት ዋስትና አስይዞ ከሆነ ውሰድበት፡፡
17በማጭበርበር የተገኘ ዳቦ ይጣፍጣል፣ ከዚያ በኋላ ግን አፉ ጠጠር ይሞላል፡፡
18እቅዶች በምክር ይጸናሉ፣ በጠቢብ ምክርም ብቻ ጦርነት አድርግ፡፡
19ሐሜት ሚስጥርን ያባክናል፣ ስለዚህ ወሬን ከሚያበዙ ሰዎች ጋር አንድነት አትፍጠር፡፡
20አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን ከሰደበ፣ መብራቱ በድቅድቅ ጨለማ መካከል ይጠፋል፡፡
21በመጀመርያ በጥድፊያ የተገኘ ሀብት በመጨረሻ ላይ በረከት አይኖረውም፡፡
22“ለፈጸምክብኝ በደል ብድራትህን እመልስልሃለሁ” አትበል! እግዚአብሔርን ጠብቅ እርሱም ያድንሃል፡፡
23እኩል ያልሆኑ ሚዛኖችን እግዚአብሔር ይጠላል፣ ሐሰተኛ መስፈሪያም መልካም አይደለም፡፡
24የሰው አካሄድ በእግዚአብሔር ይመራል፤ ታዲያ ሰው የራሱን መንገድ እንዴት ሊያስተውል ይችላል?
25ሰው በችኮላ “ይህ ነገር የተቀደሰ ነው” ቢሎ ስእለት ቢሳል፣ ከተሳለም በኋላ ስለ ነገሩ ምንነት ማሰላሰል ቢጀምርና ቢጸጸት ወጥመድ ይሆንበታል፡፡
26ጥበበኛ ንጉስ ክፉውን አበጥሮ ያወጣል፣ ከዚያም የመውቂያ ጋሪውን በላያቸው ላይ ይነዳል፡፡
27የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው፣ ውስጣዊ ማንነቱንም ይመረምራል፡፡
28በኪዳን የተመሰረተ ታማኝነትና እውነተኛነት ንጉስን ይጠብቁታል፤ ዙፋኑም በፍቅር ይጸናል፡፡
29የወጣት ወንዶች ክብር ጥንካሬያቸው ነው፣ የሽማግሌዎችም ውበት ሽበታቸው ነው፡፡
30የሚያቆስል ምት ክፋትን ያስወግዳል፣ ግርፋትም ውስጣዊ የሰውነት ክፍሎችን ያነጻል፡፡