1በንግግሩ ጠማማ ከሆነና ከሞኝ ሰው ይልቅ በሃቀኝነት የሚራመድ ድሃ ሰው ይሻላል፡፡
2ደግሞም ያለ እውቀት አንድን ነገር መመኘት መልካም አይደለም፣ በችኮላ የሚሮጥም መንገዱን ይስታል፡፡
3የሰው ጅልነት ሕይወቱን ያበላሸዋል፣ ልቡም በእግዚአብሔር ላይ ይቆጣል፡፡
4ሐብት ብዙ ጓደኞችን ይጨምራል፣ ድሃ ሰው ግን ከወዳጆቹ የተለየ ነው፡፡
5ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይታለፍም፣ ውሸትንም የሚያሰራጭ አያመልጥም፡፡
6ብዙዎች ከቸር ሰው ውለታን ይጠይቃሉ፣ ስጦታን ለሚሰጥም ሁሉ ጓደኛ ይሆነዋል፡፡
7ድሃ ሰው ወንድሞቹ ሁሉ ይጠሉታል፤ ከእርሱ ብዙ ርቀው የሚገኙ ጓደኞቹማ ምንኛ ይጠሉት! ወደ እነርሱ ይጣራል፣ እነርሱ ግን አይገኙም፡፡
8ጥበብን የሚያገኝ ሕይወቱን ይወዳል፤ ማስተዋልንም ገንዘቡ ያደረገ መልካም ነገር ያገኛል፡፡
9ሐሰተኛ ምስክር ሳይቀጣ አይቀርም፣ ውሸትን የሚያሰራጭ ግን ይጠፋል፡፡
10ለሞኝ በቅንጦት መኖር አይገባውም፣ ባርያ መሳፍንትን ሲገዛ ደግሞ ምንኛ የከፋ ይሆን፡፡
11ጠቢብ አእምሮ ሰውን ታጋሽ ያደርገዋል፣ በደልንም መተው ክብር ይሆንለታል፡፡
12የንጉስ ቁጣ እንደ ጎረምሳ አንበሳ ግሳት ነው፣ በፊቱ ሞገስ ማግኘት ግን ሳር ላይ እንዳለ ጤዛ ነው፡፡
13ሞኝ ልጅ ለአባቱ መጥፊያ ነው፣ ጨቅጫቃ ሚስትም እንደማያቋርጥ የውኃ ነጠብጣብ ናት፡፡
14ቤትና ሐብት ከወላጆች ይወረሳል፣ ጠንቃቃ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ናት፡፡
15ስንፍና ሰውን ወደ እንቅልፍ ይጥለዋል፣ ለመስራት የማይፈቅድ ግን ይራባል፡፡
16ትእዛዛትን የሚያከብር ሕይወቱን ይጠብቃል፣ ስለ መንገዶቹ የማያስብ ሰው ግን ይሞታል፡፡
17ለድሃ ቸር የሆነ ሰው ለእግዚአብሔር ያበድራል፣ ለሰራውም ቸርነት መልሶ ይከፍለዋል፡፡
18ተስፋ ሳለ ልጅህን ስርዓት አስይዘው፣ ሞቱንም እየተመኘህ ዝም ብለህ አትየው፡፡
19ንዴቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው ቅጣቱን ማግኘት አለበት፤ ብታድነውም ለሁለተኛ ጊዜ ማድረግህ አይቀርም፡፡
20ምክርን ስማ ተግሳጽንም ተቀበል፣ በሕይወትህ መጨረሻ ጥበበኛ እንድትሆን፡፡
21በሰው ልብ ብዙ እቅዶች አሉ፣ የሚፈጸመው ግን የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው፡፡
22ሰው የሚመኘው ታማኝ ሆኖ መገኘት ነው፣ ድሃም ሰው ከውሸታም ይሻላል፡፡
23እግዚአብሔርን ማክበር ሰዎችን ወደ ሕይወት ይመራል፤ እንዲህ ያለውም ሰው ይረካል በመከራም አይጎዳም፡፡
24ሰነፍ ሰው እጁን በሳህን ውስጥ ያጠልቃል፤ ወደ አፉም እንኳ እንደገና መልሶ አያመጣውም፡፡
25ፌዘኛን ብትመታው፣ ያልተማረው ጠንቃቃ ይሆናል፤ አስተዋዩን ብታርመው እውቀትን ያገኛል፡፡
26ከአባቱ የሚሰርቅ እናቱንም የሚያሳድድ ዕፍረትና ውርደት የሚያመጣ ልጅ ነው፡፡
27ልጄ ሆይ፣ ተግሳጽን አልሰማ ብትል፣ ከእውቀት ቃሎች ትስታለህ፡፡
28ምግባረ ብልሹ ምስክር በፍትህ ላይ ያፌዛል፣ የክፉ ሰው አፍም በደልን ይውጣል፡፡
29ለፌዘኞች ፍርድ፣ ለሞኞች ጀርባም ጅራፍ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡