መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ምሳሌ 17

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ጥል ባለበት ግብዛ ከሞላበት ቤት ይልቅ ሰላም ባለበት ደረቅ ቁራሽ ዳቦ ይሻላል፡፡
2ጥበበኛ ባርያ አስነዋሪ ስራ የሚሰራውን ልጅ ይገዛል፣ ከወንድማማቾችም መካከል እንደ አንዱ ውርስን ይካፈላል፡፡
3ማቅለጫ ለብር ነው እቶንም ለወርቅ ነው፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያነጥራል፡፡
4ክፋትን የሚያደርግ ሰው ክፋትን የሚናገሩ ሰዎች ምክር ይሰማል፤ ውሸታምም ክፉ ነገሮች የሚያወሩ ሰዎችን ያዳምጣል፡፡
5በድሃ የሚቀልድ ሰው ፈጣሪውን ይሰድባል፣ በጥፋትም የሚደሰት ከቅጣት አያመልጥም፡፡
6የልጅ ልጆች ለሽማግሌዎች ዘውድ ናቸው፣ ወላጆችም ለልጆቻቸው ክብር ናቸው፡፡
7መልካም ንግግር ለሞኝ ሰው አይስማማውም፤ ውሸታም ከንፈሮችም ለንጉሳውያን አይመቹም፡፡
8ጉቦ ለሰጪው እንደ አስማት ድንጋይ ነው፤ በሄደበት ስፍራ ሁሉ ስኬትን ያገኛል፡፡
9በደልን የሚሸፍን ፍቅርን ይፈልጋል፣ ነገርን የሚደጋግም ግን የቅርብ ወዳጆችን ይለያያል፡፡
10መቶ ግርፋት ወደ ሞኝ ጠልቆ ከሚገባ ይልቅ ተግሳጽ ወደ አስተዋይ ሰው ጠልቆ ይገባል፡፡
11ክፉ ሰው አመጽን ይፈልጋል፣ ጨካኝ መልዕክተኛም ወደ እርሱ ይላክበታል፡፡
12ሞኝን በሞኝነቱ ከመገናኘት ይልቅ ግልገሎቿ የተነጠቀችን ድብ መገናኘት ይሻላል፡፡
13አንድ ሰው በበጎ ፈንታ ክፋትን ሲመልስ፣ ክፋት ከቤቱ ፈጽሞ አይርቅም፡፡
14የጠብ መጀመርያ በሁሉም ስፍራ ውኃ እንደሚለቅ ሰው ነው፣ ስለዚህ ከመበርታቱ በፊት ከግጭት ራቅ፡፡
15ክፉ ሰዎችን ነጻ የሚለቅም ሆነ ጽድቅን የሚያደርጉትን ደግሞ የሚኮንን ማንኛውም ሰው፣ ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠሉ ናቸው፡፡
16ሞኝ ጥበብን ለመማር የማይችል ሆኖ ሳለ፣ ጥበብን ለመማር ለምን ገንዘብ ይከፍላል?
17ጓደኛ በዘመኑ ሁሉ ወዳጅ ነው፣ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል፡፡
18አእምሮ የጎደለው ሰው ቃል በመግባት ግዴታ ውስጥ ይገባል፣ ለጎረቤቱም ብድር ዋስ ይሆናል፡፡
19ጠብ የሚወድ ኃጢአትን ይወዳል፤ መግቢያ በሩን እጅግ ከፍ አድርጎ የሚሰራ አጥንቶች እንዲሰበሩ ያደርጋል፡፡
20ጠማማ ልብ ያለው ሰው አንዳችም መልካም ነገር አያገኝም፤ ጠማማ ምላስ ያለውም ወደ መከራ ይወድቃል፡፡
21ሞኝን የወለደ ሐዘንን ወደራሱ ያመጣል፣ የሞኝም አባት ደስታን አያገኝም፡፡
22ደስተኛ ልብ ጥሩ መድሃኒት ነው፣ የተሰበረ መንፈስ ግን አጥንትን ያደርቃል፡፡
23ክፉ ሰው የፍትህን መንገድ ለማጣመም በሚስጥር ጉቦን ይቀበላል፡፡
24አስተዋይ ሰው ፊቱን ወደ ጥበብ ያዘነብላል፣ የሞኝ አይኖች ግን ወደ ምድር ዳርቻ ያዘነብላሉ፡፡
25ሞኝ ልጅ ለአባቱ ሐዘን ነው፣ ለወለደችውም እናቱ ምሬትን ያመጣል፡፡
26ጽድቅ የሚያደርግን ሰው መቅጣት በፍጹም መልካም አይደለም፤ በሐቀኝነት የሚሄዱትን የተከበሩ ሰዎችን መግረፍም መልካም አይደለም፡፡
27እውቀት ያለው ሰው ጥቂት ቃላትን ይናገራል፣ አስተዋይ ሰውም ለቁጣ የዘገየ ነው፡፡
28ሞኝ እንኳ ዝም ሲል ጥበበኛ እንደሆነ ይታሰባል፤ አፉንም ዘግቶ ዝም ሲል፣ እንደ ምሁር ይቆጠራል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።