1የልብ እቅድ የሰው ነው፣ መልስ ግን ከእግዚአብሔር አንደበት ይመጣል፡፡
2የአንድ ሰው መንገዶች ሁሉ ለእርሱ ንጹህ ሆኖ ይታየዋል፣ እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል፡፡
3ስራህን ለእግዚአብሔር አስረክብ፣ እቅድህም ይሳካልሃል፡፡
4እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ለራሱ ዓላማ ፈጠረ፣ ሃጢአተኛውንም እንኳ ለክፉ ቀን፡፡
5እግዚአብሔር እምቢተኛ ልብ ያለውን ሁሉ ይጠላል፣ ተባብረው ቢቆሙም ከቅጣት አያመልጡም፡፡
6በኪዳን በተመሰረተ ታማኝነትና እውነተኛነት ኃጢአት ስርየት ያገኛል፣ እግዚአብሔርን በመፍራትም ሰዎች ከክፋት ይርቃሉ፡፡
7የሰው መንገዶቹ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙ ሲሆኑ፣ እግዚአብሔር የዚያን ሰው ጠላቶች እንኳ ከእርሱ ጋር በሰላም እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡
8ፍትህ በጎደለው መንገድ ከተገኘ በርካታ ገቢ ይልቅ፣ በጽድቅ የተገኘ ጥቂት ገቢ ይሻላል፡፡
9ሰው በልቡ መንገዱን ያቅዳል፣ እግዚአብሔር ግን እርምጃውን ያቀናለታል፡፡
10ውሳኔ በንጉስ ከንፈሮች ላይ አለ፣ በፍርድም ጊዜ አፉ በማታለል አይናገርም፡፡
11እውነተኛ ሚዛን ከእግዚአብሔር ይመጣል፤ በከረጢትም ውስጥ ያሉት መመዘኛዎች ሁሉ የእርሱ ስራዎች ናቸው፡፡
12ነገስታት ክፋትን ሲሰሩ፣ እርሱ አጸያፊ ነገር ነው፣ ዙፋን የሚጸናው ጽድቅን በማድረግ ነውና፡፡
13ንጉስ እውነትን በሚናገሩ ከንፈሮች ደስ ይለዋል፣ በግልጽነት የሚናገረውንም ሰው ይወደዋል፡፡
14የንጉስ ቁጣ የሞት መልእክተኛ ነው፣ ጥበበኛ ሰው ግን የንጉሱን ቁጣ ያበርዳል፡፡
15የንጉስ ፊት ሲያበራ ሕይወት አለ፣ መልካም ፈቃዱም የጸደይን ዝናብ እንደሚያመጣ ደመና ነው፡፡
16ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት ምንኛ ይበልጣል፡፡ ከብርም ይልቅ ማስተዋል ይመረጣል፡፡
17የጻድቃን መንገድ ከክፋት ትርቃለች፤ ሕይወቱን የሚጠብቅም መንገዱን ይጠብቃል፡፡
18ትዕቢት ከጥፋት በፊት ትመጣለች፣ ኩሩ መንፈስም ከውድቀት በፊት፡፡
19ከትዕቢተኞች ጋር ዝርፊያን ከመካፈል ይልቅ ከድሆች ጋር ራስን ዝቅ ማድረግ ይሻላል፡፡
20የተማሩትን የሚያሰላስሉ ሰዎች መልካምን ነገር ያገኛሉ፣ በእግዚአብሔር የሚታመኑም ደስተኛ ይሆናሉ፡፡
21በልቡ ጥበበኛ የሆነ ሰው አስተዋይ ይባላል፣ ጣፋጭ ንግግርም የማስተማር ችሎታን ያዳብራል፡፡
22ገንዘብ ላደረገው ማስተዋል የሕይወት ምንጭ ነው፣ የሞኞች ቅጣት ግን ሞኝነታቸው ነው፡፡
23የጥበበኛ ሰው ልብ ለአፉ ትምህርትን ይሰጠዋል፣ ለከንፈሮቹም ትምህርትን ይጨምራል፡፡
24ደስ የሚያሰኙ ቃላት የማር ወለላ ናቸው፣ ለነፍስ የሚጣፍጡ አጥንትንም የሚፈውሱ ናቸው፡፡
25ለሰው ትክክል የሚመስል መንገድ አለ፣ ፍጻሜው ግን ወደ ሞት የሚወስድ ነው፡፡
26የሰራተኛ ረሃብ ለእርሱ ይሰራል፤ ረሃቡም ያነሳሳዋል፡፡
27የማይረባ ሰው ክፋትን ይቆፍራል፣ ንግግሩም እንደሚያቃጥል እሳት ነው፡፡
28ጠማማ ሰው ጥልን ያነሳሳል፣ ሐሜትም የቅርብ ወዳጆችን ያለያያል፡፡
29በጥባጭ ሰው ጎረቤቱን ይዋሻል፣ መልካም ወዳልሆነ መንገድም ይመራዋል፡፡
30በዓይኑ የሚጠቅስ ሰው ጠማማ ነገሮችን ያስባል፤ ከንፈሮቻቸውን የሚነክሱም ክፋትን ይጎትታሉ፡፡
31ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ በጽድቅ መንገድ በመኖር ይገኛል፡፡
32ጦረኛ ከመሆን ይልቅ ትዕግስተኛ መሆን ይሻላል፣ መንፈሱን የሚገዛም ከተማን ከሚቆጣጠር ይልቅ ይበረታል፡፡
33እጣ በጉያ ይጣላል፣ ውሳኔው ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡