1የለዘበ መልስ ቁጣን ይመልሳል፣ መጥፎ ቃል ግን ቁጣን ያስነሳል፡፡
2የጥበበኛ ሰዎች ምላስ እውቀትን የተላበሰ ነው፣ የሞኞች አፍ ግን ሞኝነትን ያንቆረቁራል፡፡
3የእግዚአብሔር ዓይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፣ ክፉውንና መልካሙን ሁሉ ነቅተው ይመለከታሉ፡፡
4ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ነው፣ አታላይ ምላስ ግን መንፈስን ይሰብራል፡፡
5ሞኝ የአባቱን ተግሳጽ ይንቃል፣ ከእርምት የሚማር ግን አስተዋይ ነው፡፡
6ጽድቅን በሚያደርጉ ሰዎች ቤት ብዙ ሀብት አለ፣ ክፉ ሰዎች የሚያገኙት ገቢ ግን መከራ ያመጣባቸዋል፡፡
7የጥበበኛ ሰዎች ከንፈሮች እውቀትን ያስፋፋሉ፣ የሞኞች ልብ ግን እንዲህ አይደለም፡፡
8እግዚአብሔር የክፉዎችን መስዋዕት ይጠላል፣ የቅኖች ጸሎት ግን ደስ ያሰኘዋል፡፡
9እግዚአብሔር የክፉዎችን መንገድ ይጠላል፣ ጽድቅን የሚከታተለውን ግን ይወደዋል፡፡
10ከመንገድ የሚወጣ ሰው ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል፣ እርምትን የሚጠላም ይሞታል፡፡
11ሲኦልና ጥፋት በእግዚአብሔር ፊት የተገለጡ ናቸው፤ የሰው ልጆች ልብማ ምንኛ የተገለጠ ይሆን?
12ፌዘኛ እርምትን ይንቃል፤ ወደ ጥበበኛም አይሄድም፡፡
13ደስተኛ ልብ ፊትን ያፈካል፣ የልብ ሐዘን ግን መንፈስን ይሰብራል፡፡
14የአስተዋይ ልብ እውቀትን ይፈልጋል፣ የሞኞች አፍ ግን ከንቱነትን ይመገባል፡፡
15የተጨቆኑ ሰዎች ቀናት በሙሉ አሰቃቂ ናቸው፣ ደስተኛ ልብ ግን የማይቋረጥ ግብዣ አለው፡፡
16እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር ያለ ጥቂት ነገር ከሁከት ጋር ካለ ትልቅ ሃብት ይሻላል፡፡
17ፍቅር ባለበት የአትክልት ምግብ መብላት ጥላቻ ባለበት የሰባ ጥጃ ከመብላት ይሻላል፡
18ቁጡ ሰው ጭቅጭቅን ያነሳሳል፣ ለቁጣ የዘገየ ሰው ግን ጠብን ጸጥ ያሰኛል፡፡
19የታካች ሰው መንገድ በእሾህ እንደ ታጠረ ስፍራ ነው፣ የቅን መንገድ ግን በሚገባ የተገነባ አውራ ጎዳና ነው፡፡
20ጥበበኛ ልጅ ለአባቱ ደስታን ያመጣለታል፣ ሞኝ ሰው ግን እናቱን ይንቃል፡፡
21ከንቱ ነገር አእምሮ ለጎደለው ሰው ደስ ያሰኛል፣ አስተዋይ ሰው ግን በቅን መንገድ ይሄዳል፡፡
22ምክር በሌለበት እቅድ ይበላሻል፣ በአማካሪዎች ብዛት ግን ይከናወናል፡፡
23ሰው ተገቢ የሆነ መልስ ሲሰጥ ደስታን ያገኛል፤ የጊዜው ቃል ምንኛ መልካም ነው!
24የሕይወት መንገድ አስተዋይ ሰዎችን ወደ ላይ ይመራቸዋል፣ በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ፡፡
25እግዚአብሔር የትዕቢተኛውን ውርስ ያፈራርሳል፣ የመበለቲቱን ንብረት ግን ይጠብቃል፡፡
26እግዚአብሔር የክፉ ሰዎችን ሐሳብ ይጠላል፣ የርኅራኄ ቃሎች ግን ንጹሐን ናቸው፡፡
27ዘራፊ ለቤተሰቡ መከራን ያመጣል፣ ጉቦን የሚጠላ ግን በሕይወት ይኖራል፡፡
28ጽድቅን የሚያደርግ ሰው ልብ መልስ ከመስጠቱ በፊት አጥብቆ ያስባል፣ የክፉ ሰዎች አፍ ግን ክፋትን ሁሉ ያጎርፋል፡፡
29እግዚአብሔር ከክፉ ሰዎች እጅግ ሩቅ ነው፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎችን ጸሎት ግን ይሰማል፡፡
30የዓይን ብርሃን ለልብ ደስታን ያመጣል፣ መልካም ወሬ ደግሞ ለሰውነት ጤና ነው፡፡
31አንድ ሰው እንዴት መኖር እንዳለብህ እርምትን ሲሰጥህ ትኩረት ሰጥተህ የምትሰማ ከሆንህ፣ በጥበበኛ ሰዎች መካከል ትቆያለህ፡፡
32ተግሳጽን የማይቀበል ራሱን ይንቃል፣ እርምትን የሚያደምጥ ግን ማስተዋልን ያገኛል፡፡
33የእግዚአብሔር ፍርሃት ጥበብን ያስተምራል፣ ትህትናም ከክብር በፊት ትመጣለች፡፡