1ጥበበኛ ሴት ቤቷን ትሰራለች፣ ሞኝ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች፡፡
2በጽድቅ የሚሄድ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፣ በመንገዱ ታማኝ ያልሆነ ግን ይንቀዋል፡፡
3ከሞኝ አፍ የትዕቢት በትር ይወጣል፣ የጥበበኛ ከንፈሮች ግን ይጠብቋቸዋል፡፡
4ከብቶች በሌሉበት የመመገቢያ ገንዳ ባዶ ይሆናል፣ በበሬ ጉልበት ግን ብዙ ምርት ይገኛል፡፡
5እውነተኛ ምስክር አይዋሽም፣ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይለፈልፋል፡፡
6ፌዘኛ ጥበብን ይፈልጋል ሆኖም አያገኛትም፣ እውቀት ግን ወደ አስተዋይ ሰው በቀላሉ ትመጣለች፡፡
7ከሞኝ ሰው ራቅ፣ ከከንፈሮቹ እውቀትን አታገኝምና፡፡
8የጠንቃቃ ሰው ጥበብ መንገዱን ማስተዋል ነው፣ የሞኞች ከንቱነት ግን ማታለል ነው፡፡
9ሞኞች የኃጢአት መስዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ ያፌዛሉ፣ በጻድቃን መካከል ግን ቸርነት ይገኛል፡፡
10ልብ የራሱን ምሬት ያውቃል፣ ደስታውንም ሌላ ሰው አይጋራውም፡፡
11የክፉ ሰዎች ቤት ይጠፋል፣ የጻድቃን ድንኳን ግን ይስፋፋል፡፡
12ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፣ ፍጻሜዋ ግን ወደ ሞት ይመራል፡፡
13ልብ በሐዘን ውስጥ ሆኖ ሊስቅ ይችላል፣ የደስታም ፍጻሜ ሐዘን ሊሆን ይችላል፡፡
14ታማኝ ያልሆነ ሰው ለመንገዱ የሚገባውን ዋጋ ያገኛል፣ መልካም ሰው ግን የራሱ የሆነውን ያገኛል፡፡
15እውቀት አልባ ሰው ሁሉንም ነገር ያምናል፣ አስተዋይ ሰው ግን አካሄዱን ያስተውላል፡፡
16ጥበበኛ ሰው ይፈራል ከክፉም ይርቃል፣ ሞኝ ግን ራሱን ታምኖ ማስጠንቀቂያን ችላ ይላል፡፡
17ለቁጣ የሚቸኩል ሰው ከንቱ ነገሮችን ይፈጽማል፣ ክፋትን የሚያሴር ሰው ደግሞ ይጠላል፡፡
18እውቀት አልባ ሰዎች ሞኝነትን ይወርሳሉ፣ አስተዋይ ሰዎች ግን በእውቀት ይከበባሉ፡፡
19ክፉዎች በመልካም ሰዎች ፊት ይሰግዳሉ፣ ኃጢአተኞች ደግሞ በጻድቃን ደጅ ይሰግዳሉ፡፡
20ድሃ ሰው በራሱ ባልንጀሮችም ጭምር ይጠላል፣ ባለጠጋ ሰዎች ግን ብዙ ወዳጆች አሏቸው፡፡
21ለጎረቤቱ ንቀትን የሚያሳይ ኃጢአትን ያደርጋል፣ ለድሃ በጎነትን የሚያሳይ ግን ደስተኛ ነው፡፡
22ክፋትን የሚያሴሩ አይስቱምን? መልካምን ለማድረግ የሚያቅዱ ግን በኪዳን የተመሰረተ ታማኝነትና እውነተኛነት ይቀበላሉ፡፡
23በብዙ ድካም ትርፍ ይገኛል፣ ወሬ ግን ወደ ድህነት ይመራል፡፡
24የጥበበኞች ዘውድ ባለጠግነታቸው ነው፣ የሞኞች ሞኝነት ግን ተጨማሪ ከንቱነትን ያመጣባቸዋል፡፡
25እውነተኛ ምስክር ሕይወት ያድናል፣ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይለፈልፋል፡፡
26ሰው እግዚአብሔርን ሲፈራ፣ በእርሱ ይታመናል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ለልጆቹ እንደ ብርቱ መጠጊያ ስፍራ ይሆኗቸዋል፡፡
27እግዚአብሔርን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፣ ሰውን ከሞት ወጥመድ እንዲያመልጥ ያደርገዋል፡፡
28የንጉስ ክብር የሚገኘው ከሕዝቡ ብዛት ነው፣ ሕዝብ በሌለበት ግን ልዑል ይጠፋል፡፡
29ትዕግስተኛ ሰው ታላቅ ማስተዋል አለው፣ ለቁጣ የሚቸኩል ሰው ግን ሞኝነትን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡
30በሰላም የተሞላ ልብ ለሰውነት ሕይወት ነው፣ ቅናት ግን አጥንትን ያበሰብሳል፡፡
31ድሀን የሚያስጨንቅ ሰው ፈጣሪውን ይሰድባል፣ ለድሀ ቸርነትን የሚያሳይ ግን ፈጣሪውን ያከብራል፡፡
32ክፉ ሰው በክፉ ስራው ይወድቃል፣ ጻድቅ ግን በሞት ጊዜ እንኳ መጠጊያ አለው፡፡
33ጥበብ በአስተዋይ ሰው ዘንድ ትኖራለች፣ በሞኞች መካከል እንኳ ራሷን ታሳውቃለች፡፡
34ጽድቅን ማድረግ ህዝብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፣ ኃጢአት ግን ለማንኛውም ሕዝብ ውርደት ነው፡፡
35የንጉስ ሞገስ ተግተው በሚሰሩ አገልጋዮቹ ላይ ነው፣ ቁጣው ግን በአሳፋሪ አገልጋይ ላይ ነው፡፡