1ጥበበኛ ልጅ የአባቱን ምክር ይሰማል፣ ፌዘኛ ግን ተግሳጽን አያዳምጥም፡፡
2ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ነገር ይጠግባል፣ ጠማማ ሰው ግን ዓመጽን ይመኛል፡፡
3አፉን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል፣ ከንፈሮቹን ያለ ልክ የሚከፍት ግን ይጠፋል፡፡
4ሰነፍ ሰው ይመኛል ነገር ግን አንዳችም አያገኝም፣ የትጉ ሰው ምኞት ግን በሙላት ይረካል፡፡
5ጽድቅን የሚያደርግ ሰው ውሸትን ይጠላል፣ ክፉ ሰው ግን ራሱ ጥላቻን ይፈጥራል፣ አሳፋሪ ተግባርንም ይፈጽማል፡፡
6በመንገዳቸው ያለ ነቀፋ የሚሄዱትን ጽድቅ ትጠብቃቸዋለች፣ ክፋት ግን ኃጢአተኞችን ትጥላቸዋለች፡፡
7ራሱን ባለጠጋ የሚያስመስል ሰው አለ፣ ነገር ግን አንዳች የለውም፣ ምንም እንደሌለው መስሎ የሚታይ ሰው ደግሞ አለ፣ ይሁን እንጂ እጅግ ባለጠጋ ነው፡፡
8ባለጠጋ ሰው ሀብቱን ለሕይወቱ ቤዛ አድርጎ ያቀርብ ይሆናል፣ ድሀ ግን እንዲህ ዓይነት ሥጋት በፍጹም የለበትም፡፡
9ጽድቅን የሚያደርግ ሰው ብርሃን ደምቆ ይበራል፣ የክፉዎች መብራት ግን ይጠፋል፡፡
10ትዕቢት ጠብን ብቻ ያስፋፋል፣ መልካም ምክርን ለሚያደምጡ ግን ጥበብ አለ፡፡
11ብዙ ከንቱነት ሲኖር ሀብት እየመነመነ ያልቃል፣ በእጁ እየሰራ ገንዘብ የሚያከማች ሰው ግን ገንዘቡ እየጨመረ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡
12ተስፋ ሲዘገይ ልብን ይሰብራል፣ የተሳካ ምኞት ግን የሕይወት ዛፍ ነው፡፡
13ትእዛዝን የሚንቅ በትእዛዝ ይቀጣል፣ ትእዛዝን የሚያከብር ግን ወሮታን ያገኛል፡፡
14የጥበበኛ ሰው ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው፣ ከሞት ወጥመድ እንድታመልጥ ያደርግሃል፡፡
15መልካም እውቀት ሞገስ ያስገኛል፣ የከዳተኛ ሰው መንገድ ግን አያልቅም፡፡
16ጥንቃቄ የተሞሉ ሰዎች ማንኛውንም ውሳኔ የሚያደርጉት በጥበብ ነው፣ ሞኝ ግን ከንቱነቱን ይገልጣል፡፡
17ክፉ መልእክተኛ መከራ ውስጥ ይገባል፣ ታማኝ መልእክተኛ ግን እርቅን ያመጣል፡፡
18ተግሳጽን የሚንቅ ድህነትና ኃፍረት ይመጣበታል፣ ከእርምት የሚማር ግን ክብር ወደ እርሱ ይመጣል፡፡
19ምኞት ሲፈጸም የውስጥ ፍላጎትን ደስ ያሰኛል፣ ሞኞች ግን ከክፋት መመለስን ይጠላሉ፡፡
20ከጥበበኞች ጋር ሂድ አንተም ጥበበኛ ትሆናለህ፣ የሞኞች ባልንጀራ ግን እጅግ ይጎዳል፡፡
21መቅሰፍት ኃጢአተኞችን ይከታተላቸዋል፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ግን መልካምን ነገር ይቀበላሉ፡፡
22መልካም ሰው ለልጅ ልጆቹ የሚያወርሰውን ይተዋል፣ የኃጢአተኛ ሀብት ግን ጽድቅን ለሚያደርጉ ይከማቻል፡፡
23የድሆች እርሻ ያልታረሰም ቢሆን ብዙ ምግብ ሊያመርት ይችላል፣ ነገር ግን በፍትህ መጓደል ምክንያት ተጠራርጎ ይወሰዳል፡፡
24ልጁን የማይቀጣ ይጠላዋል፣ ልጁን የሚወድ ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል፡፡
25ጽድቅን የሚያደርግ ሰው ፍላጎቱን እስከሚያረካ ድረስ ጠግቦ ይበላል፣ የክፉዎች ሆድ ግን ሁልጊዜ እንደተራበ ነው፡፡