1ተግሳጽን የሚወድ እውቀትን ይወዳል፣ እርምትን የሚጠላ ግን ደነዝ ነው፡፡
2እግዚአብሔር ለመልካም ሰው ሞገስን ይሰጠዋል፣ ክፉ እቅድ ለሚያወጣ ሰው ግን ይፈርድበታል፡፡
3ሰው በክፋት ላይ ተመስርቶ ጸንቶ ሊቆም አይችልም፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ግን ከመሰረታቸው አይነቀሉም፡፡
4መልካም ሴት ለበሏ ዘውድ ናት፣ አሳፋሪ ሴት ግን አጥንቱን እንደሚያበሰብስ በሽታ ናት፡፡
5ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎች እቅድ ጽድቅ ነው፣ የክፉዎች ምክር ግን ተንኮል ነው፡፡
6የክፉ ሰዎች ቃል ድንገት ለመግደል አድፍጦ ያደባል፣ የቅኖች ቃል ግን ይታደጋቸዋል፡፡
7ክፉ ሰዎች ይገለበጣሉ፣ አይገኙምም፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎች ቤት ግን ጸንቶ ይቆማል፡፡
8ሰው በጥበቡ ብዛት ይመሰገናል፣ ጠማማ ምርጫዎች የሚያደርግ ግን ይናቃል፡፡
9የሚበላው ምግብ ሳይኖረው ከሚኩራራ ሰው ይልቅ ራሱን ዝቅ አድርጎ አገልጋይ መሆን ይሻላል፡፡
10ጽድቅን የሚያደርግ ሰው እንስሳቱ ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ግድ ይለዋል፣ ክፉ ሰው ግን ርህራሄ አደረገ ቢባል እንኳ ስራው ጭካኔ የተሞላ ነው፡፡
11መሬቱን በሚገባ የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፣ ዋጋ ቢስ ስራዎችን የሚያሳድድ ሰው ግን አእምሮ አልባ ነው፡፡
12ኃጢአተኞች ክፉ ሰዎች ከሌሎች የሰረቁትን ይመኛሉ፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎች ፍሬ ግን ከገዛ ራሳቸው ይመጣል፡፡
13ክፉ ሰው በክፉ ንግግሩ ይጠመዳል፣ ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎች ግን ከመከራ ያመልጣሉ፡፡
14ሰው ከቃሎቹ ፍሬ የተነሳ መልካም ነገርን ይጠግባል፣ እንደ እጁ ስራም ዋጋውን ይቀበላል፡፡
15የሞኝ መንገድ ለራሱ ትክክል መስሎ ይታየዋል፣ ጥበበኛ ሰው ግን ምክርን ይሰማል፡፡
16ሞኝ ቁጣውን በቶሎ ይገልጣል፣ ስድብን ንቆ የሚተው ግን አስተዋይ ነው፡፡
17እወነትን የሚናገር ትክክለኛውን ነገር ይናራል፣ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይናገራል፡፡
18የለፍላፊ ሰው ቃሎች እንደሚዋጋ ሰይፍ ነው፣ የጥበበኛ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል፡፡
19እውነተኛ ከንፈሮች ለዘላለም ይኖራሉ፣ ሀሰተኛ ከንፈር ግን ለቅጽበት ብቻ ነው፡፡
20ክፋትን ለማድረግ በሚያቅዱ ሰዎች ልብ ውስጥ ተንኮል አለ፣ ሰላምን ለሚመክሩ ሰዎች ግን ደስታ ይመጣል፡፡
21ጽድቅን የሚያደርጉ ሰዎች በሽታ አያገኛቸውም፣ ክፉ ሰዎች ግን በመከራ የተሞሉ ናቸው፡፡
22እግዚአብሔር ሀሰተኛ ከንፈሮችን ይጠላል፣ በእውነተኛነት በሚኖሩ ሰዎች ግን ደስ ይለዋል፡፡
23አስተዋይ ሰው እወቀቱን ይሰውራል፣ የሞኞች ልብ ግን ከንቱነትን ያወራል፡፡
24የትጉ ሰዎች እጅ ይገዛል፣ ሰነፍ ሰዎች ግን ለጉልበት ስራተኝነት ታልፈው ይሰጣሉ፡፡
25በሰው ልብ ውስጥ የሚገኝ ጭንቀት ያዋርደዋል፣ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል፡፡
26ጽድቅን የሚያደርግ ሰው ለጓደኛው መንገድን ያሳያል፣ የክፉ መንገድ ግን ታስታቸዋለች፡፡
27ሰነፍ ሰዎች አድነው ያመጡትን እንስሳ እንኳ አይጠብሱም፣ ትጉ ሰው ግን የከበረ ሀብት ያገኛል፡፡
28በጽድቅ መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ሕይወትን ያገኛሉ፣ በጎዳናዋም ሞት የለም፡፡