1በጨረሻም ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ከዚህ በፊት የጻፍኩላችሁን ተመሳሳይ ነግሮች አሁንም ደግሜ ብጽፍላችሁ አይታክተኝም። እነዚህ ነገሮች እናንተን ከስሕተት ይጠብቃችኋል።
2ከውሾች ተጠንቀቁ። ከክፉ ሠራተኞች ተጠንቀቁ፤ከሐሰተኞች መገረዝም ተጠንቀቁ።
3እኛ በእግዚአብሔር መንፈስ የምናመልክ፤ በሥጋም የማንታመን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ የምንታመን የተገረዝን ነን።
4በሥጋ ትምክሕት የሚያስፈልግ ቢሆን እኔ በብዙ ነገር ልመካ እችል ነበረ። ማንም በሥጋ የሚመካበት አለኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ቢኖር እኔ ከእርሱ የበለጠ የምመካበት ብዙ አለኝ።
5እኔ በተወለድኩ በስምንተኛው ቀን ተገርዤአለሁ፤ በትውልዴም ከብንያም ነገድ የሆንኩ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከዚህም የተነሳ ጥርት ያልኩ ዕብራዊ ነኝ። የአይሁድን ሕግ ስለ መጠበቅም ቢሆን ፈሪሳዊ ነበርኩ።
6በቅንዓት ቤተ ክርስቲያን አሳድድ ነበር። ሕግን በመጠበቅ ስለ መጽደቅም ቢሆን ያለ ነቀፋ እኖር ነበር።
7ነገር ግን ከዚህ በፊት ጠቃሚዎች ናቸው ብዬ አምንባቸው የነበሩትን ነገሮች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ብዬ ዋጋ እንደሌላቸው እንደ ከንቱ ነገሮች አድርጌ ቆጥሬአቸዋለሁ።
8በርግጥ፥ ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ጌታዬ ዕውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቆጥራለሁ። ስለ እርሱም ሁሉን ነገር አጥቻለሁ። ክርስቶስንም ለማግኝትና በእርሱም ለመገኝት ስል ሁሉን ነገር እንደ ቤት ጥራጊ እቆጥራለሁ።
9እንግዲህ በሕግ ላይ የተመሠረተው የራሴ ጽድቅ የለኝም። በዚህ ፈንታ በክርስቶስ በኩል በሚገኝ እምነት የእግዚአብሔር ጽድቅ አለኝ።
10ይኸውም እርሱን የማወቅ ጽድቅ፤ የእርሱ የትንሣኤ ኃይልና የመከራው ተካፋይ የመሆንና በሞቱም ክርስቶስን ለመምሰል ነው።
11ደግሞም ከሙታን ትንሣኤን አገኝ ዘንድ ነው።
12እነዚህን ነገሮች ገና አልጨበጥኩአቸውም ፤ ፍጹም ሆኜአለሁ ማለትም አልችልም። ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘሁትን አገኝ ዘንድ ወደ ፊት ጥረቴን እቀጥላለሁ።
13ወንድሞች ሆይ፤እኔ ራሴ ገና እንደጨበጥኩ አልቆጥርም። ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ይኸውም በስተኋላዬ የነበረውን እየረሰሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እተጋለሉ።
14እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ጠርቶ ሽልማቴን ለማግኘት በፊት ወዳለው ግብ እሮጣለሁ።
15ስለዚህ እኛ ብዙዎቻችን በመንፈሳዊ ሕይወት እንዳደጉ ሰዎች ነገሮችን ሁሉ ማሳብ ይኖርብናል። ደግሞ በማንኛውም ነገር የተለያየ አስተሳሰብ ቢኖራችሁ እግዚአብሔር ሁሉንም ግልጥ ያደርግላችኋል።
16ይሁን እንጂ በደረሰንበት በዚያው ሁኔታ እንመላለስ።
17ወንድሞች ሆይ፥ የእኔን ምሳሌነት ተከተሉ፤ በእኛም ምሳሌነት የሚመላለሱትን ሁሉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ።
18ከአሁን በፊት ብዙ ጊዜ እንደ ነገርኳችሁና አሁንም እንባዬን እያፈሰስኩ እንደምነግራችሁ ሁሉ ብዙዎቹ በአካሄዳቸው የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነዋል።
19የእነርሱ አምላክ ሆዳቸው ነው፤ አሳፋሪ የሆነ ነገርም ለእነርሱ ክብራቸው ነው፤ አሳባቸውም የሚያተኩረው በምድራዊ ነገር ላይ ነው ስለዚህ የእነርሱም መጨረሻ ጥፋት ነው፤
20ነገር ግን የሚመጣውን አዳኝ ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የምንጠብቅ የሰማይ መንግሥት ዜጎች ነን።
21እርሱ ይህን የተዋረደውን ሰውነታችንን በመለወጥ የእርሱን ክቡር ሰውነት እንዲመስል ያደርገዋል። ይህንንም የሚያደርገው ሁሉን በሥልጣኑ ሥር ለማድረግ በሚያስችለው ኃይል ነው።