1ከግብጽ ምድር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው አመት በመጀመሪያው ወር፣ በሲና ምድረ በዳ ያህዌ ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፣
2“የእስራኤል ሰዎች በተወሰነው የአመቱ ወቅት ፋሲካን ያድርጉ፡፡
3በዚህ ወር በእስራ አራተኛው ቀን፣ ምሽት ላይ፣ በተወሰነው በአመቱ ወቅት ፋሲካን አድርጉ፡፡ ፋሲካን አድርጉ፣ ደንቦቹን ጠብቁ፣ ከዚህ ጋር የተያያዙ ደንቦችን ሁሉ ታዘዙ፡፡”
4ስለዚህ፣ ሙሴ የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ ነገራቸው፡፡
5ስለዚህ በመጀመሪያው ወር በወሩ በአስራ አራተኛው ቀን፣ ምሽት ላይ፣ በሲና ምድረ በዳ ፋሲካን አከበሩ፡፡ የእስራኤል ሰዎች ያህዌ ለሙሴ እንዲያደርግ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፡፡
6በሞተ ሰው በድን የረከሱ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነርሱ በዕለቱ ፋሲካን አላከበሩም፡፡ በዚያ ቀን እነዚህ ሰዎች ሙሴና አሮን ፊት ቀረቡ፡፡
7እነዚያ ሰዎች ሙሴን እንዲህ አሉት፣ “እኛ በሰው በድን አካል ምክንያት ንጹህ አይደለንም፡፡ ሆኖም በእስራኤል ሰዎች መሃል በተወሰነው የአመቱ ወቅት ለያህዌ መስዋዕት ከማቅረብ ለምን ትከለክለናለህ”
8ሙሴ እንዲህ አላቸው፣ “ያህዌ ስለ እናንተ ምን ትዕዛዝ እንደሚሰጥ እስከምሰማ ጠብቁኝ፡፡”
9ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣
10”ለእስራኤል ሰዎች እንዲህ በላቸው፣ ‘ከእናንተ ማናችሁም ወይም ከትውልዳችሁ ማንም በበድን አካል ምክንያት እርኩስ ቢሆን፣ ወይም ሩቅ መንገድ ሄዶ ቢሆን፣ ለያህዌ ፋሲካን ማክበር ይችላል፡፡’
11እነርሱ በሁለተኛው ወር በአስራ አራተኛው ቀን ፋሲካን ያክብሩ፡፡ እነርሱ ፋሲካን እርሾ ባስገባበት እንጀራ ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉ፡፡
12እስከ ማለዳ አንዳች አያስተርፉለት፣ አሊያም ከእንስሳቱ አጥንት አይስበሩ፡፡ የፋሲካን ህግጋት ሁሉ ይጠብቁ፡፡
13ነገር ግን ማናቸውም ንጹህ የሆነና ሩቅ መንገድ ያልሄደ ሰው፣ ነገር ግን ፋሲካን ሳያከብር የቀረ ሰው፣ ከህዝቡ ተለይቶ ይጥፋ፤ ምክንያቱም እርሱ በተወሰነው የአመቱ ወቅት የሚቀርበውን ያህዌ የሚጠይቀውን መስዋዕት አላቀረበም፡፡ ያሰው ኃጢአቱን ይሸከም፡፡
14እንግዳ በመሀላችሁ ቢኖርና ፋሲካን ለያህዌ ክብር ቢያብር፣ ፋሲካን መጠበቅና እርሱ ያዘዘውን ሁሉ ማድረግ አለበት፣ የፋሲካን ህግጋት ሁሉ መጠበቅ እንዲሁም የፋሲካን ህግነት መጠበቅ አለበት፡፡ ለመጻተኞች እና በምድሪቱ ለተወለዱ ሁሉ ተመሳሳይ ህግ ይኑርህ፡፡”
15የማደሪያው ድንኳን በተተከለበት ቀን፣ ደመና የማደሪያውን ድንኳን ፣ የቃል ኪዳኑን ምስክር ድንኳን ሸፈነው፡፡ በምሽት ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ነበር፡፡ እስከ ንጋት እሳት ይመስል ነበር፡፡
16በዚያ መልክ ቀጠለ፡፡ ደመናው የማደሪያ ድንኳኑን ሸፍኖ በምሽት እሳት ይመስል ነበር፡፡
17ደመናው ከድንኳኑ ላይ በተወሰደ ጊዜ ሁሉ፣ የእስራኤል ሰዎች ከመጓዝ ያቋርጡ ነበር፡፡ ደመናው በቆመ ጊዜ ሁሉ፣ ህዝቡ አንድ ቦታ ይሰፍራል፡፡
18የእስራኤል ሰዎች በያህዌ ትዕዛዝ ይጓዛሉ፣ በእርሱም ትእዛዝ በሰፈራቸው ይቆያሉ፡፡ ደመናው በማደሪያው ድንኳን ላይ ሲቆም፣ በሰፈራቸው ይቆያሉ፡፡
19ደመናው በማደሪያው ድንኳን ለብዙ ቀናት ሲቆይ፣ የእስራኤል ሰዎች የያህዌን ትዕዛዝ ተከትለው መጓዝ ያቆማሉ፡፡
20አንዳንድ ጊዜ ደመናው በማደሪያው ድንኳን ላይ ለጥቂት ቀናት ይቆያል፡፡ በዚህ ሁኔታ የያዌን ትእዛዝ ተከትለው በአንድ ቦታ ይሰፍራሉ፣ ከዚያ በእርሱ ትእዛዝ እንደገና ይጓዛሉ፡፡
21አንዳንድ ጊዜ ደመናው ከምሽት እስከ ማለዳ በሰፈር ይገኛል፡፡ ማለዳ ደመናው ሲነሳ፣ እነርሱ ይጓዛሉ፡፡ ቀንም ይሁን ሌሊት ጉዟቸውን የሚቀጥሉት ደመናው ከተነሳ ብቻ ነው፡፡
22ደመናው በማደሪያ ድንኳኑ ላይ ለሁለት ቀናት፣ ለወር ወይም ለአመት ቢቆይ በዚያ ስፍራ እስከ ቆየ ድረስ የእስራኤል ሰዎች በሰፈሮቻቸው ይቆያሉ አይጓዙም፡፡ ነገር ግን ደመናው ሲንቀሳቀስ እነርሱም ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡
23በያህዌ ትዕዛዝ ይሰፍራሉ፣ በእርሱ ትዕዛዝ ይጓዛሉ በሙሴ በኩል የተሰጣቸውን የያህዌን ትዕዛዝ ይፈጽማሉ፡፡