1ያህዌ ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፣
2“የእስራኤል ሰዎች ተላላፊ የቆዳ በሽታ ያለበትን ሁሉ፣ በስቃይ የሚመግለውን ሁሉ፣ እና ማንኛውንም በድን በመንካት ረከሰውን ሁሉ ከሰፈር እንዲያስወጡ እዘዛቸው፡፡
3ወንዶችም ይሁኑ ሴቶች እነዚህን ከሰፈር አስወጣቸው፡፡ እኔ በውስጡ እኖራለሁና ሰፈሩን አያርክሱ፡፡”
4የእስራኤለ ሰዎችም ይህንኑ አደረጉ፡፡ ያህዌ ሙሴን እንዳዘዘው፣ ከሰፈር አስወጧቸው፡፡ የእስራኤል ሰዎች ያህዌን ታዘዙ፡፡
5ያህዌ ሙሴን እንደገና እንዲህ ሲል ተናገረው፣
6“ለእስራኤል ሰዎች እንዲህ በላቸው፡፡ አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት አንዱ በሌላው ላይ በደል ሲፈጽም፣ እና ለእኔ ታማኝ ሳይሆን ሲቀር ያ ሰው በደለኛ ነው፡፡
7በዚህን ጊዜ በዳዩ ኃጢአቱን ይናዘዝ፡፡ በዳዩ የበደሉን ዋጋ ሙሉ ለሙሉ ይክፈል፣ ደግሞም አንድ አምስተኛውን ጨምሮ ይክፈል፡፡ ይህንን ለበደለው ይስጥ፡፡
8ነገር ግን ተበዳዩ ክፍያውን ለመቀበል የቅርብ ዘመድ ባይኖረው፣ በዳዩ የበደሉን ዋጋ ከአውራ በግ ጋር ለራሱ ማስተስረያ በካህኑ በኩል ለእኔ ይክፈል፡፡
9ከተቀደሱ ነገሮች ሁሉ የሚቀርቡ መስዋዕቶች ሁሉ፣ በእስራኤል ሰዎች ለእኔ የሚለዩ ነገሮች፣ የዚያ ካህን ይሆናሉ፡፡
10የእያንዳንዱ ሰው የተቀደሱ ነገሮች የካህኑ ይሆናሉ፡፡ አንድ ሰው ለካህኑ የሚሰጣቸው ማናቸውም ነገሮች የዚያ ካህን ይሆናሉ፡፡”
11ያህዌ እንደገና ሙሴን ተናገረው፡፡ እንዲህም አለው፣
12“ለእስራኤል ሰዎች ተናገራቸው፡፡ እንዲህ በላቸው፣ “ምናልባት የአንድ ሰው ሚስት ወደ ሌላ ሰው ሄዳ በባሏ ላይ ኃጢአት ሰርታ ይሆናል፡፡
13ከባሏ ሌላ ሰው ከእርሷ ጋር ተኝቶ ይሆናል፡፡ በዚያ ሁኔታ፣ እርሷ ረክሳለች፡፡ ምንም እንኳን ባሏ ነገሩን ባያይም ወይም ስለነገሩ ባያውቅም፣ ደግሞም ድርጊቱን ስትፈጽም ማንም ባይዛትም፣ በእርሷ ላይ የሚያረጋግጥ ማንም ባይኖርም፣
14የሆነ ሆኖ፣ የቅናት መንፈስ ሚስቱ እንደ ረከሰች ለባልየው ይነግረው ይሆናል፡፡ ሆኖም፣ ሚስቱ ሳትረክስ የቅናት መንፈስ በሀሰት በሰውየው ላይ መጥቶ ይሆናል፡፡
15በዚህ ሁኔታ፣ ሰውየው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፡፡ ባልየው የመጠጥ ቁርባን ለእርሷ ያምጣ፡፡ የኢፍ አንድ አስረኛ የገብስ ዱቄት ያምጣ፡፡ ስለ ቅናት የሚቀርብ የእህል ቁርባን ነውና፣ምንም ዘይት ወይም እጣን አይጨምርበት፤ ምናልባት ተፈጽሞ ሊሆን ለሚችል ኃጢአት ጠቋሚ የእህል ቁርባን ነው፡፡
16ካህኑ ያምጣትና በያህዌ ፊት ያቁማት፡፡
17ካህኑ አንድ ገንቦ ቅዱስ ውሃና ከማደሪያ ድንኳኑ ወለል አፈር ይውሰድ፡፡ አፈሩን ውሃው ውስጥ ይጨምረው፡፡
18ካህኑ ሴትየዋን በያህዌ ፊት ያቁማት የሴትየዋን ጸጉርም ይግለጥ፡፡ ካህኑ የቅናት መስዋእት የሆነውን የእህል ቁርባን በእጇ ያስይዛታል፡፡ ካህኑ በሴትየዋ ላይ እርግማን ሊያስከትል የሚችለውን በውስጡ አቧራ ያለበትን መራራ ውሃ በእጆቹ ይያዝ፡፡
19ካህኑ ሴትየዋን ያስሞላት፤ እንደህም ይበላት፣ “ማንም ሰው ከአንቺ ጋር ተኝቶ ካልሆነ፣ እና ተሳስተሸ ካልሆነ እናም እርኩሰት ካልፈጸምሽ፣ እርግማን ከሚያጣው ከዚህ መራራ ውሃ በእርግጥ ነፃ ትሆኛለሽ፡፡
20ነገር ግን፣ አንቺ በባልሽ ስር ያለሽ ሴት፣ ተሳስተሸ ቢሆን፣ ረክሰሽ ቢሆን፣ እና ሌላ ወንድ ከአንቺ ጋር ተኝቶ ቢሆን፣
21ከዚያ፣ (ካህኑ በእርሷ ላይ ዕርግማን የሚያስከትል መሃላ ያስምላታል፣ ከዚያ በኋላ ሴትየዋን እንዲህ ማለቱን ይቀጥል) ‘ያህዌ ህን ማድረግሽን ለህዝብሽ በመርገምሽ ያሳያል፡፡ ያህዌ ጭንሽን ካሰለለና ሆድሽን ካሳበጠ ይህ ይታወቅ፡፡
22ዕርግማኑን የሚያጣው ይህ ውሃ ወደ ሆድሽ ይገባል፣ ሆድሽን ያሳብጣል፣ እንዲሁም ጭኖችሽን ያሰልላል፡፡” ሴትየዋ እንዲህ ብላ ትመልስ፣ “አሜን፣ በደለኛ ከሆንኩ ይህ በእኔ ላይ ይሁን፡፡”
23ካህኑ እነዚህን ዕርግማኖች በጥቅል ብራና ላይ ይጻፍ፣ ከዚያ የተጻፉትን እርግማኖች በመራራው ውሃ አጥቦ ያስለቅቅ፡፡
24ካህኑ ዕርግማን የሚያመጣውን መራራ ውሃ እንድትጠጣ ያድርግ፡፡ ዕርግማኑን የሚያመጣው ውሃ ወደ ውስጧ ገብቶ መራራ ይሆናል፡፡
25የቅናት መስዋዕቱን የእህል ቁርባን ከሴትየዋ እጅ ይቀበል፡፡ የእህል ቁርባኑን በያህዌ ፊት ወደ መሰዊያው ያምጣው፡፡
26ካህኑ ከእህል ቁርባኑ እፍኝ ሙሉ ዘግኖ ይውሰድና በመሰዊያው ላይ ያቃጥለው፡፡ ከዚያ ለሴትየዋ መራራውን ውሃ እንድትጠጣው ይስጣት፡፡
27ውሃውን እንድትጠጣው ሲሰጣት በባሏ ላይ በደል በመፈፀም ረክሳ ከሆነ፣ ዕርግማን የሚያስከትለው ውሃ ወደ ውስጧ ይገባና መራራ ይሆናል፡፡ ሆዷ ያብጣል ጭኗ ይመነምናል፡፡ ሴትየዋ ከህዝቧ መሃል የተረገመች ትሆናለች፡፡
28ሴትየዋ የረከሰች ካልሆነችና ንጹህ ከሆነች፣ ነጻ ትሆናለች፡፡ ልጆችን መጸነስ ትችላለች፡፡
29የቅናት ህግ ይህ ነው፡፡ ከባሏ ውጭ ለሄደች እና ለረከሰች ሴት ህጉ ይህ ነው፡፡
30የቅናት መንፈስ ለያዘውና በሚስቱ ለቀና ሰው ህጉ ይህ ነው፡፡ ሴትየዋን በያህዌ ፊት ያምጣ፣ ካህኑም ይህ የቅናት ህግ የሚገልጸውን ሁሉ በእርሷ ላይ ያድርግ፡፡
31ሰውየው ሚስቱን ወደ ካህን በማቅረቡ ከበደል ነጻ ይሆናለ፡፡ ሴትየዋ በድላ ከሆነ ማናቸውንም በደል ትሸከማለች፡፡”