1ያህዌ ሙሴን በሞአብ ሜዳ ዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ እንዲህ አለው፣
2”የእስረኤል ሰዎችን ለሌዋውያን ርስታቸው ከሆነው ከድርሻቸው እንዲሰጧቸው እዘዝ፡፡ የሚኖሩባቸውን ከተሞችና በዙሪያቸውም የግጦሽ መሬት ይስጧቸው፡፡
3ሌዋውያን እነዚህን ከተሞች መኖሪያቸው ያድርጓቸው፡፡ የግጦሽ መሬቱ ለከብቶቻቸው ለመንጎቻቸው እና ለእንስሳቻቸው ይሁኑ፡፡
4ለሌዋውያኑ የምትሰጣቸው በከተሞቹ ዙሪያ የሚገኘው የግጦሽ መሬት ከከተማ ቅጥር በየአቅጣጫው ስፋቱ አንድ ሺህ ክንድ ይሆናል፡፡
5ከከተማዋ በምስራቅ አቅጣጫ ሁለት ሺህ ክንድ ለካ፣ በስተደቡብ በኩልም ሁለት ሺህ ክንድ ለካ፣ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፣ እና በሰሜን በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ለካ፡፡ ይህ በከተማቸው ዙሪያ የግጦሽ መሬት ይሆናል፡፡ ከተማይቱ በመሃል ትሆናለች፡፡
6ለሌዋውያን የምትሰጧቸው ስድስቱ ከተሞች የስደተኞች ከተሞች ሆነው ያገለግሉ፡፡ እነዚህን ከተሞች በነፍስ መግደል ለተከሰሱ መሸሻ ስፍራ እንዲሆኑ ስጣቸው፡፡ እንዲሁም ሌሎች አርባ ሁለት ከተሞችን ስጣቸው፡፡
7ለሌዋውያን የምትሰጣቸው ከተሞች በጠቅላላው አርባ ስምንት ይሆናሉ፡፡ ከከተሞቹ ጋር የግጦሽ መሬትም ትሰጣቸዋለህ፡፡
8ብዙ የሆኑ የእስራኤል ህዝብ ጎሳዎችና ብዙ መሬት ያላቸው ጎሣዎች ብዙ ከተሞች ይሰጣቸዋል፡፡ አነስተኛዎቹ ጎሣዎች ጥቂት ከተሞች ይሰጣቸዋል፡፡ እያንዳንዱ ነገድ እንደ ተቀበለው እንደ ድርሻው መጠን ለሌዋውያኑ መስጠት አለበት፡፡”
9ከዚያም ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣
10“ለእስራኤል ሰዎች እንዲህ በላቸው፣ ‘ዮርዳኖስን አቋርጣችሁ ወደ ከነዓን ስትገቡ፣
11ይሁነኝ ብሎ ሰው ያልገደለ ሰው ወደ እነዚያ ከተሞች መግባት እንዲችል የመሸሸጊየ ከተማ ሆነው የሚያገለግሉ ከተሞችን ምረጡ፡፡
12እነዚህ ከተሞች ከደመኞቻችሁ የምትሸሸጉባቸው ይሁኑ፣ ስለዚህም የተከሰሰው ሰው በቅድሚያ በማህበሩ ፊት ለፍርድ ሳይቀርብ አይገደልም፡፡
13የመሸሸጊያ ከተማ አድርጋችሁ ስድስት ከተሞችን ምረጡ፡፡
14ከዮርዳኖስ ወዲያ ሶስት ከተሞችን፣ በከነዓን ምድር ደግሞ ሶስት ከተሞችን ስጡ፡፡ እነዚህ የመሸሸጊያ ከተሞች ይሆናሉ፡፡
15እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ሰዎች፣ ለመጻተኞች፣ እና ለማናቸውም በመሀላቸው ለሚኖር ሳያውቅ ሰውን ለገደለ መሸሸጊያ ሆነው ያገለግላሉ፡፡
16ነገር ግን የተከሰሰው ሰው ተበዳዩን በብረት መሳሪያ ቢመታውና ተጠቂው ቢሞት፣ ተከሰሹ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ እርሱ በእርግጥ ይገደል፡፡
17የተከሰሰው ሰው በእጁ በያዘው ድንጋይ ተበዳዩን ቢመታና ተበዳዩ ቢሞት ተከሳሹ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ በእርግጥ ይገደል፡፡
18የተከሰሰው ሰው ተበዳዩን ሊገድል በሚችል የእንጨት መሳሪያ ቢመታውና ተበዳዩ ቢሞት ተከሳሹ በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ ሊገደል ይገባዋል፡፡
19ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው፡፡ ሲያገኘው፣ ሊገድለው ይችላል፡፡
20ተከሳሹ አንድን እየተደበቀ ወይም እየተሸሸገ ያለ ሰው በጥላቻ ቢገፈትረው ወይም አንዳች ነገር ቢወረውርበትና ከዚህም የተነሳ ተበዳዩ ቢሞት፣
21ወይም በጥላቻ መትቶ ቢጥለውና ከዚህም የተነሳ ተበዳዩ ቢሞት መትቶ የገደለው በእርግጥ ይገደል፡፡ ነብስ ገዳይ ነው፡፡ ደም ተበቃዩ ነብሰ ገዳዩን ሲያገኘው ይግደለው፡፡
22ነገር ግን ተከሳሹ ሰው ቀድሞ ባልታሰበበት ጥላቻ ተበዳዩን ቢመታው ወይም ሳያስበው አንዳች ነገር ወርውሮ ቢመታው፣
23ተበዳዩን ሳይመለከት ሊገድለው የሚችል ድንጋይ ቢወረውርበት፣ ተከሳሹ የተበዳዩ ጠላት አይደለም፤ ተበዳዩን ለመጉዳት እየሞከረ አልነበረም፡፡ የሆነ ሆኖ ተበዳዩ ቢሞት፣
24በዚህ ሁኔታ፣ ማህበረሰቡ በተከሳሹና በደም ተበቃዩ መሀል በእነዚህ ህጎች መሠረት ይዳኝ
25ማህበረሰቡ ተከሳሹን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነው፡፡ ማህበረሰቡ ተከሳሹን በመጀመሪያ ወዳሸሸበት መሸሸጊያ ከተማ ይመልሰው፡፡ ተከሳሹ፣ በቅዱሱ ዘይት የተቀባው በወቅቱ ያለው ሊቀካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይኑር፡፡
26ነገር ግን የተከሰሰው ሰው በማንኛውም ጊዜ ከሸሸበት ከተማ ድንበር አልፎ ቢሄድ፣
27እና ደም ተበቃዩ ከመሸሸጊያ ከተማው ድንበር ውጭ ቢያገኘውና ቢገድለው፣ ደም ተበቃዩ በነብሰ ገዳይነት ጥፋተኛ አይሆንም፡፡
28ለዚህም ምክንያቱ ተከሳሹ ሰው እስከ ሊቀ ካህኑ ሞት ድረስ በመሸሸጊያ ከተማው መቆየት ስለነበረበት ነው፡፡
29እነዚህ ህጎች፤ በምትኖባቸው ቦታዎች ሁሉ፣ በትውልዳቸው ሁሉ ለእናንተ የጸኑ ናቸው፡፡
30ሰውን የገደለ ማንኛውም ሰው፣ በምስክሮች ቃል እየረጋገጠ መገደል አለበት፡፡ ነገር ግን የአንድ ምስክር ቃል ብቻውን ማንንም ሰው ለመግደል በቂ አይደለም፡፡
31ደግሞም፣ በነብስ ገዳይነት ጥፋተኛ ለሆነ ሰው ሕይወት የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፡፡ ያ ሰው በእርግጥ ይገደል፡፡
32ወደ መሸሸጊያ ከተማ ለሄደ የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፡፡ ሊቀ ካህኑ እስኪሞት ድረስ የነፍስ ዋጋ በመቀበል ወደ ራሱ ርስት ተመልሶ እንዲገባ አትፍቀዱለት፡፡
33በዚህ መንገድ የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱ፣ ምክንቱም በነፍስ ግድያ የሚፈስ ደም ምድሪቱን ያረክሳል፡፡ ምድር በላይዋ ደም ሲፈስ፣ ደም ካፈሰሰው ሰው ደም በስተቀር ሌላ ምንም ማስተስረያ ማድረግ አይቻልም፡፡
34ስለዚህ የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱ ምክንያቱም እኔ በውስጧ እኖራለሁ፡፡ እኔ፣ ያህዌ፣ በእስራኤል ሰዎች መሃል እኖራለሁ፡፡”