1ሙሴ ለእስራኤል ህዝብ የጎሳ መሪዎች እንዲህ አላቸው፣ “ያህዌ ያዘዘው ይህን ነው፡፡
2ማንም ሰው ለያህዌ ስዕለት ሲሳል፣ ወይም በቃል ኪዳን ራሱን በመሀላ ሲያስር፣ ቃሉን ማፍረስ የለበትም፡፡ ከአፉ የወጣውን ማናቸውንም ነገር ለማድረግ ቃልኪዳኑን መጠበቅ አለበት፡፡
3አንዲት ወጣት ሴት በአባቷ ቤት እያለች ለያህዌ ብትሳልና በመሀላ ራሷን ብታስር፣
4አባቷም ስዕለቷንና ራሷን ያሰረችበትን መሀላ ቢሰማ፣ እርሱም እርሷን ለመመለስ አንዳች ነገር ባይናገር መሀላዎቿ ሁሉ መፈፀም አለባቸው፡፡ ራሷን ያሰረችባቸው ቃልኪዳኖች ሁሉ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡
5ነገር ግን አባቷ ስለ ስዕለቷና ስለገባችው ቃል ኪዳን ሰምቶ ምንም ነገር ባይነግራት በራሷ ላይ የወሰደቻቸው የገባቻቸው መሀላዎችና ቃል ኪዳኖች መፈጸም አለባቸው፡፡
6ሆኖም ግን፣ አባቷ የገባቻቸውን መሀላዎች ሁሉና የከበሩ ቃል ኪዳኖቿን ራሷን ግዴታ ውስጥ ያስገባችበትን ነገር ቢሰማ፣ ደግሞም በዚያው ቀን ማድረግ ያለበትን ቢነግራት መሀላዋን ለመፈጸም አትገደድም፡፡ ያህዌ ይቅር ይላታል ምክንያቱም አባቷ ማድረግ ያለባትን ነግሯታል፡፡
7እነዚያ መሀላዎች እያሉባት ባል ብታገባ ወይም በችኮላ መሀላ ብታደርግና ራሷን ግዴታ ውስጥ ብታስገባ እነዚያ ግዴታዎች መፈጸም አለባቸው፡፡
8ነገር ግን ባሏ በዚያው ቀን ሰምቶ ቢከለክላት የገባቸውን መሀላና በችኮላ ራሷን ያሰረችበትን መሀላዋን ያስቀራል፡፡ ያህዌ ከዚህ ነጻ ያደርጋታል፡፡
9ባሏ የሞተባት ወይም ከባሏ የተፋታች ሴት ግን ራሷን የሰራችባቸው ነገሮች ሁሉ ተፈፃሚ ይሆኑባታል፡፡
10ከባሏ ቤተሰቦች ጋር ያለች ሴት ብትሳል ራሷን በቃል ኪዳን መሀላ ብታስር፣
11እና ባልዋ ሰምቶ ምንም ነገር ባይነግራት ስእለቷን ባያስቀር፣ ስዕለቶቿ ሁሉ መፈጸም አለባቸው፡፡ ራሷን ያሰረችባቸው ቃልኪዳኖች ሁሉ መፈጸም አለባቸው፡፡
12ነገር ግን ባሏ ስለ ስዕለቶቿ በሰማ ቀን እንዲቀሩ ካደረገ፣ ስለ ስዕለቶቿ ወይም ቃልኪዳኖቿ ከከንፈሯ የወጡ ነገሮች ሁሉ የግዴታ መፈጸም አይኖርባቸውም፡፡ ባልዋ አስቀርቷቸዋል፡፡ ያህዌ ነጻ ያደርጋታል፡፤
13አንዲት ሴት የገባችውን እያንዳንዱን መሀላ ወይም ስእለት እንድታጥፍ የሚያደርጋትን አንዳች ነገር በባሏ ሊጸና ወይም ሊሻር ይችላል፡፡
14ነገር ግን ቀናት ሲያልፉ ባሏ አንዳች ካልነገራት፣ ስዕቶቿን ሁሉ እና ቃል የገባቻቸውን ነገሮች ያፀናባታል፡፡ ስዕቶቿንና መሀላዎቿን የሚያፀናባት ስለእነዚህ በሰማበት ጊዜ ምንም ስላልነገራት ነው፡፡
15ባሏ የሚስቱን ስዕለት ከሰማ ከረጅም ጊዜ በኋላ ሊሽር ቢሞክር፣ ስለእርሷ ኃጢአት ሀላፊነቱን ይወስዳል፡፡”
16ያህዌ ሙሴ እንዲያውጃቸው የሰጠው ቋሚ መመሪያዎች እነዚህ ናቸው፡፡ በአንድ ወንድና በሚስቱ መሀል፣ እንዲሁም በአባትና በወጣትነቷ በአባቷ ቤት ስለምትኖር ሴት ልጁ ያህዌ የሰጠው ቋሚ መመሪያ ይህ ነው፡፡