1ያህዌ በሲና ተራራ ከሙሴ ጋር በተነጋገረበት ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልዶች ታሪክ ይህ ነበር፡፡
2የአሮን ልጆች ስሞቻቸው የበኩር ልጁ ናዳብ፣ እንዲሁም አብዩድ፣ አልዓዛር እና ኢታምር ነበሩ፡፡
3የአሮን ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፣ እነዚህ የተቀቡ ካህናትና እንደ ካህናት ሊያገለግሉ የተሾሙ ነበሩ፡፡
4ነገር ግን ናዳብ እና አብዩድ በሲና ምድረበዳ ተቀባይነት የሌለው እሳት ለእርሱ ሲሰዉ በያህዌ ፊት ወድቀው ሞቱ፡፡ ናዳብና አብዩድ ልጅ አልነበራቸውም፣ ስለዚህም አልዓዛርና ኢታምር ብቻ ከአባታቸው ከአሮን ጋር ካህናት ሆነው አገለገሉ፡፡
5ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣
6“የሌዊን ጎሳ ይረዱት ዘንድ ወደ ካህኑ ወደ አሮን አምጣቸው፡፡
7በአሮንና በመላው ማህበሩ ስም በመገናኛው ድንኳን ፊት አገልግሎት ይስጡ፡፡ በቤተመቅደሱ ውስጥ ያገልግሉ፡፡
8በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ላሉ ነገሮች ሁሉ ጥንቃቄ ያድርጉ፣ እንዲሁም የእስራኤል ጎሳዎች የቤተ መቅደሱን አገልግሎት እንድፈጽም ይርዱ፡፡
9ሌዋውያኑን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ፡፡ እነርሱ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲያገለግል ሙሉ ለሙሉ የተሰጡ ናቸው፡፡
10አሮንንና ልጆቹን ካህን አድርገህ ሹማቸው፣ ነገር ግን ማናቸውም ባዕድ ወደ ቤተ መቅደሱ ቢቀርብ ይገደል፡፡”
11ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣
12“እነሆ፣ እኔ ከእስራኤል ህዝብ መሃል ሌዋውያንን መረጥኩ፡፡ ከእስራኤል ሕዝብ መሃል በኩር የሆነውን ወንድ ሁሉ ከመውሰድ ፈንታ ይህን አድርጌያለሁ፡፡ ሌዋዊያን የእኔ ናቸው፡፡
13ማናቸውም በኩር የእኔ ነው፡፡ በግብጽ ምድር በኩሩን ሁሉ በመታሁ ዕለት፣ በእስራኤል በኩር ሆኖ የተወለደውን የሰውንም ሆነ የእንስሳትን በኩር ሁሉ ለራሴ ለየሁ፡፡ እነርሱ የእኔ ናቸው፡፡ እኔ ያህዌ ነኝ፡፡”
14በሲና ምድረበዳ ያህዌ ሙሴን ተናገረው፡፡ እንዲህም አለው፣
15“በእያንዳንዱ ቤተሰብ፣ በአባቶቻቸው ቤቶች የሌዊን ትውልዶች ቁጠር፡፡ አንድ ወር እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያለውን ወንድ ሁሉ ቁጠር፡፡”
16ሙሴ እንዲያደርግ በታዘዘው መሠረት የያህዌን ቃል ሰምቶ ቆጠራቸው፡፡
17የሌዊ ልጆች ስም፣ ጌድሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ናቸው፡፡
18ከጌድሶን ልጆች የመጡ ነገዶች ሎቢኒ እና ሰሜኢ ናቸው፡፡
19ከቀዓት ልጆች የመጡ ነገዶች፣ አንበረም፣ ይስዓር፣ኬብሮን እና ዑዝኤል ናቸው፡፡
20ከሜራሪ ልጆች የመጡ ነገዶች፣ ሞሖሊና ሙሴ ናቸው፡፡ በነገድ የተዘረዘሩ የሌዋውያን ነገዶች እነዚህ ናቸው፡፡
21የሊቤናና የሰሜአ ነገዶች የመጡት ከጌርሶን ነው፡፡ እነዚህ የጌርሶን ነገዶች ናቸው፡፡
22አንድ ወር ከሞላው አንስቶ ከዚያ በላይ ዕድሜ ያለው ወንድ ሁሉ ተቆጥሮ ነበር፣ በጠቅላላው 7500 ነበሩ፡፡
23የጌርሶን ነገዶች ከቤተመቅደሱ ምዕራብ አቅጣጫ ይስፈሩ፡፡
24የጌርሶንን ትውልዶች የላኤለ ልጅ ኤሊሳፍ ይምራ፡፡
25የጌርሶን ቤተሰብ የመገናኛው ድንኳን ጨምሮ የማደሪያውን ድንኳን ኃላፊነት ይውሰድ፡፡ እነርሱ ለድንኳኑ፣ ለመደረቢያዎቹና ለመገናኛው ድንኳን መግቢያ ሆኖ ለሚያገለግለው መጋረጃ ጥንቃቄ ያደርጉ፡፡
26ለአደባባዩ ጌጦች ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፣ በአደባባይ መግቢያ ላይ ለሚገኘው መጋረጃ፣ ቅዱሱን ስፍራና መሰዊያውን የሚከበውን አደባባይ ይጠብቁ፡፡ የመገናኛው ድንኳን ገመዶች እና በውስጡ የሚገኘውን ነገር ሁሉ ይጠብቁ፡፡
27ከቀዓት የመጡት ነገዶች እነዚህ ናቸው የአንበረማውያን ነገድ የይሰዓራውያን ነገድ፣ የኬብሮናውያን ነገድ፣ እና የዑዝኤላውያን ነገድ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገዶች የቀዓት ወገኖች ናቸው፡፡
28አንድ ወር እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው 8600 ወንዶች የያህዌ የሆኑ ነገሮችን ለመጠበቅ ተቆጠሩ፡፡
29የቀዓት ቤተሰብ ትውልዶች ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ አቅጣጫ ይስፈሩ፡፡
30የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን የቀዓታዊያንን ነገድ ይምራ፡፡
31እነርሱ ታቦቱን፣ ጠረጴዛውን፣ የመቅረዝ ማስቀመጫውን፣ መሰዊያዎቹን፣ ለአገልግሎታቸው የሚጠቀሙባቸውን ቅዱሳን ዕቃዎች፣ መጋረጃውን፣ እና በዚያ ዙሪያ ያለውን ስራ ሁሉ ይንከባከቡ፡፡
32የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ሌዋውያንን የሚመሩትን ሰዎች ይምሩ፡፡ እርሱ ቅዱሱን ስፍራ የሚንከባከቡትን ሰዎች ይቆጣጠር፡፡
33ሁለቱ ነገዶች ኮሜራሪ ነገድ የመጡ ናቸው፡ እነዚህም የሞሖላውያን ነገድ እና የሙሳያውያን ነገድ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገዶች የመጡት ከሜራሪ ነው፡፡
34አንድ ወርና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው 6200 ወንዶች ተቆጠሩ፡፡
35የሜራሪን ነገድ የአቢካኤል ልጅ ሲሪኤል ይምራ፡፡
36እነርሱ የቤተመቅደሱን ጣውላዎች፣ መቀርቀሪያዎች፣ ምሰሶዎች፣ መሰረቶች፣ ሁሉንም መገልገያዎች፣ እና ከእነርሱ ጋር የተያያዙ ነገሮች ሁሉ፣
37መቅደሱ ዙሪያ የሚገኙ ምሰሶዎችና ቋሚዎችን ጨምሮ፣ ከማስገቢያዎቻቸው፣ ችካሎችና ገመዶች ጋር ይጠብቁ፡፡
38ሙሴ፣ አሮን እና ልጆቹ ከመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት፣ በፀሀይ ማውጫ ከቤተ መቅደሱ በስተ ምስራቅ ይስፈሩ፡፡ እነርሱ በቅድስተ ቅዱሳን ለሚከናወኑ ተግባራት እና ለእስራኤል ህዝብ ግዴታዎች ሀላፊነት አለባቸው፡፡ ማንኛውም ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ የሚቀርብ ባዕድ ይገደል፡፡
39ሙሴና አሮን ያህዌ እንዳዘዘው በሌዊ ነገዶች ውስጥ የሚገኙትን አንድ ወርና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸውን ወንዶች ሁሉ ቆጠሩ፡፡ ሃያ ሁለት ሺህ ወንዶችን ቆጠሩ፡፡
40ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣ “አንድ ወር ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸውን በኩር የሆኑ የእስራኤል ወንዶች ቁጠር፡፡ ስሞቻቸውን ጻፍ፡፡
41በእስራኤል ህዝብ በኩር ምትክ ሌዋውያንን ለእኔ ውሰድ፡፡ እኔ ያህዌ ነኝ፡፡ እንደዚሁም የሌዋውያንን ቀንድ ከብቶች፣ በመጀመሪያ በሚወለዱ የእስራኤላውያን የቀንድ ከብቶች ምትክ ውሰድ፡፡”
42ያህዌ እንዳዘዘው ሙሴ የእስራኤልን ሰዎች በኩር በሙሉ ቆጠረ፡፡
43ዕድሜያቸው አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆኑትን በኩር ወንዶች ሁሉ በስም ቆጠረ፡፡ 22273 ወንዶችን ቆጠረ፡፡
44እንደገና፣ ያህዌ ሙሴን ተናገረው፡፡ እንዲህም አለው፣
45“በእስራኤል ህዝብ በኩር ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን ውሰድ፡፡ በህዝቡ የቀንድ ከብት ምትክ የሌዋውያንን ቀንድ ከብት ውሰድ፡፡ ሌዋውያን የእኔ ናቸው፡፡ እኔ ያህዌ ነኝ፡፡
46ከሌዋውያን ቁጥር በላይ የሆኑትን 273 የእስራኤል በኩሮች ለመዋጀት ለእያንዳንዳቸው አምስት ሰቅሎች ተቀበል፡፡
47የቅድስተ ቅዱሳኑን ሰቅል እንደ መደበኛ ክብደት ተጠቀም፡፡ (አንድ ሰቅል አምሳ አምስት ግራም ነው)
48ያገኘኸውን የመዋጆ ዋጋ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ፡፡”
49ስለዚህም ሙሴ በሌዋውያን ከተዋጁት በላይ ቁጥራቸው ያለፈውን መዋጃ ክፍያ ሰበሰበ፡፡
50ሙሴ ከእስራኤል ሕዝብ በኩሮች ገንዘብ ሰበሰበ፡፡ በቤተ መቅደሱ ሚዛን መዝኖ 1365 ሰቅሎች ሰበሰበ፡፡
51ሙሴ ለአሮንና ለልጆቹ የመዋጃውን ገንዘብ ሰጣቸው፡፡ ሙሴ ያህዌ እንዲያደርግ የተናገረውን ሁሉ አደረገ፣ ያህዌ እንዳዘዘው አደረገ፡፡