1በለዓምም ያህዌ እስራኤልን መባረክ እንደፈቀደ ባየ ጊዜ፣ በሌላ ጊዜ እንደሚያደርገው አስማት ለማድረግ አልወጣም፡፡ ይልቁንም፣ ወደ ምድረበዳው ቁልቁል ተመለከተ፡፡
2ዐይኖቹን አቅንቶ እስራኤልን በየነገዱ ሰፍሮ አየ፣ የእግዚአብሔር መንፈስም በእርሱ ላይ መጣ፡፡
3ይህን ትንቢት ተቀብሎ እንዲህ ሲል ተናገረ፣ “ዐይኖቹ እጅግ የተከፈቱለት የቢዖር ልጅ በለዓም እዲህ ይላል፡፡
4እርሱ የእግዚአብሔርን ቃላት ይናገራል ይሰማልም፡፡ እርሱ ሁሉን ቻይ ከሆነው ዘንድ ዐይኖቹ ተከፍተውለት በፊቱ ከሚሰግድለት ዘንድ የሆነውን ራእይን ይመለከታል፡፡
5ያዕቆብ ሆይ ድንኳኖችህ ምንኛ ያማሩ ናቸው፣ እስራኤል ሆይ መኖሪያዎችህ እንዴት ያምራሉ!
6እንደ ሸለቆዎች ተዘርግተዋል፣ በወንዝ ዳር እንዳሉ መናፈሻ ስፍራዎች፣ በያህዌ እንደተተከሉ ሬቶች፣ በውሃ ዳርቻ እንዳሉ ዝግባዎች ናቸው፡፡
7ማድጋዎቻቸው በውሃ የተትረፈረፉ ናቸው፣ ሰብላቸው ውሃ አይታጣውም፡፡ ንጉሳቸው ከአጋግ ይበልጣል፣ መንግስታቸው የከበረ ነው፡፡
8እግዚአብሔር እርሱን ከግብጽ አውጥቶታል፡፡ እንደ ጎሽ ብርታት አለው፡፡ የሚዋጉትን መንግስታት ይፈጃቸዋል፡፡ አጥንቶቻቸውን ይሰባብራል፡፡ በቀስቶቹ ይወጋቸዋል፡፡
9እንደ አንበሳ ይሰባብራቸዋል፣ እንደ ሴት አንበሳ ያደቃቸዋል፡፡ ማን ሊቋቋመው ይችላል? የሚባርኩት ሁሉ ይባረኩ፤ የሚረግሙት ሁሉ የተረገሙ ይሁኑ፡፡”
10የባላቅ ቁጣ በበለዓም ላይ ነደደ፣ እጆቹን አጣፍቶ በለዓምን እንዲህ አለው፣ “እኔ ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፣ ነገር ግን አንተ ሶስት ጊዜም ባረካቸው፡፡
11ስለዚህ አሁኑኑ ከእኔ ተለይተህ ወደ ቤትህ ሂድልኝ፡፡ እጅግ አድርጌ አከብርሃለሁ ብዬ ነበር፣ ነገር ግን አንዳች ሽልማት እንዳታገኝ ያህዌ ከለከለህ፡፡”
12ከዚያ በለዓም ለባላቅ እንዲህ ሲል መለሰለት፣ “ወደ እኔ ለላካቸው መልዕክተኞች እንዲህ ብያቸው ነበር፣
13‘ባላቅ በብርና ወርቅ የተሞላውን ቤተ መንግስቱን ቢሰጠኝ እንኳን፣ ያህዌ ከተናገረው ውጭ አንዳች መጥፎ ወይም መልካም፣ ወይም አንዳች እኔ ላደርግ የምፈልገውን አልናገርም፡፡ መናገር የምችለው ያህዌ ተናገር ያለንን ብቻ ነው፡፡’ ይህን ለእነርሱ አልተናገርኩምን?
14ስለዚህ እነሆ አሁን ወደ ህዝቤ እመለሳለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን በቅድሚያ ይህ ህዝብ በሚመጡት ቀናት በአንተ ህዝብ ላይ ሊያደርግ ያለውን ላስጠንቅህ፡፡”
15በለዓም ይህን ትንቢት መናገር ጀመረ፣ “ዐይኖቹ እጅግ የተከፈቱለት የቢዖር ልጅ በልዓም ይህን ናገራል፡፡
16ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ቃል የሚሰማ ሰው ትንቢት ነው፣ ከልዑል ዘንድ ዕውቀት ከተሰጠው፣ ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ራዕይ ከተቀበለው፣ በተከፈተ ዐይን በፊቱ ከሚሰግደው፣ ሰው የተነገረ ትንቢት ነው፡፡
17እኔ እርሱን አያለሁ፣ ነገር ግን እርሱ አሁን እዚህ አይደለም፡፡ እኔ እርሱን እመለከታለሁ፣ ነገር ግን እርሱ በቅርብ አይደለም፡፡ ኮከብ ከያዕቆብ ይወጣል፣ በትረ መንግስት ከእስራኤል ይነሳል፡፡ እርሱ የሞአብን መሪዎችን ይበታትናል፣ የሴትንም ትውልዶች ያጠፋል፡፡
18ከዚያ እስራኤል በሃይል ድል የሚነሳው ኤዶም፤ የእስራኤል ርስት ይሆናል፣ ደግሞም የእስራኤል ጠላት የሆነው ሴይር፣ የእነርሱ ርስት ይሆናል፣
19ከያዕቆብ ግዛት ያለው ንጉስ ይወጣል፣ እርሱም ከከተማቸው የተረፉትን ቅሬታዎች ያጠፋል፡፡”
20ከዚያ በለዓም አማሌቅን ተመልክቶ ትንቢት መናገር ጀመረ፡፡ እንዲህም አለ፣ “አማሌቅ ታላቅ ህዝብ ነበር፣ነገር ግን መጨረሻው ጥፋት ይሆናል፡፡”
21ከዚያ በለዓም ወደ ቄናውያን ተመልክቶ ትንቢቱን ጀመረ፡፡ እንዲህም አለ፣ “የምትኖርበት ስፍራ አስተማማኝ ነው፣ ጎጆችህም በአለቶች መሀል ነው፡፡
22ሆኖም ግን እናንተ ቄናውያን አሶር ምርኮ አድርጎ ሲወስዳችሁ ትደመሰሳላችሁ፡፡”
23ከዚያ በለዓም የመጨረሻውን ትንቢቱን መናገር ጀመረ፡፡ እንዲህም አለ፣ “አወይ! እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግ ማን ይተርፋል?
24መርከቦች ከኪቲም ዳርቻዎች ይመጣሉ፤ አሶርን ያጠቃሉ ዔቦርን ይይዛሉ፣ ነገር ግን እነርሱም ደግሞ መጨረሻቸው መደምሰስ ነው፡፡
25ከዚያ በለዓም ተነስቶ ሄደ፡፡ ወደ ቤቱ ተመለሰ፣ ባላቅም ተነስቶ ሄደ፡፡