መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ዘኁልቁ 23

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1በለዓም ባላቅን እንዲህ አለው፣ “በዚህ ሰባት መሰዊያዎችንና ሰባት በሬዎችን እንዲሁም ሰባት አውራ በጎችን አዘጋጅልኝ፡፡”
2ስለዚህም ባላቅ በለዓም እንደጠየቀው አደረገ፡፡ ከዚያም ባላቅና በለዓም በእያንዳንዱ መሰዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቀረቡ፡፡
3ከዚያ በለዓም ባላቅን እንዲህ አለው፣ “አንተ በሚቃጠል መስዋዕትህ አጠገብ ቁም እኔ እሄዳለሁ፡፡ ምናልባት ያህዌ ሊገናኘኝ ይመጣ ይሆናል፡፡ እርሱ የሚያሳየኝን ሁሉ እነግርሀለሁ፡፡” ስለዚህም በለዓም ዛፎች ወደ ሌሉበት የተራራ ጫፍ ሄደ፡፡
4እግዚአብሔር እርሱን ተገናኘው፣ በለዓምም ለእግዚአብሔር እንዲህ አለ፣ “እኔ ሰባት መሰዊያዎችን አበጅቻለሁ፣ ደግሞም በእያንዳንዱ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ አቅርቤያለሁ፡፡”
5ያህዌ በበለዓም አፍ ላይ መልዕክት አኑሮ እንዲህ አለ፣ “ወደ ባላቅ ተመለስና እንዲህ በለው፡፡”
6ስለዚህ በለዓም በሚቃጠል መስዋዕቱ አጠገብ ወደቆመው ወደ ባላቅ ከእነርሱ ጋር ወደ ነበሩት የሞአብ መሪዎች ሁሉ ተመለሰ፡፡
7ከዚያ በለዓም ትንቢቱን መናገር ጀመረ እንዲህም አለ፣ “ባላቅ እኔን ከአራም አመጣኝ፣ የሞአብ ንጉስ ከምስራቅ ተራሮች አመጣኝ፡፡ ‘ና፣ ያዕቆብን ዕርገምልኝ’ አለኝ፡፡ ‘ና፣ እስራኤልን ተፈታተንልኝ’ አለኝ፡፡
8እግዚአብሔር ያልረገመውን እኔ እንዴት መርገም እችላለሁ? ያህዌ ያልተቃወማቸውን እኔ እንዴት መቃወም እችላለሁ?
9ከአለቶች በላይ ሆኜ አየዋለሁ፣ ከተራሮች ላይ ሆኜ ወደ እርሱ አያለሁ፡፡ ተመልከት፣ ብቻውን የሚኖር ራሱን እንደ ተራ ህዝብ አድርጎ የማይቆጥር ህዝብ አለ፡፡
10የያዕቆብን ትቢያ ማን መቁጠር ይችላል ወይም ከእስራኤል ሩቡን እንኳን ማን ይቆጥራል? የጻድቁነ ሞት እኔ ልሙት፣ ደግሞም የህይወቴ መጨረሻ እንደ እርሱ ይሁን!”
11ባላቅ በለዓምን እንዲህ አለው፣ “ምን እያደረግክብኝ ነው ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ አመጣሁህ፣ ነገር ግን እነሆ አንተ እነርሱን ባረካቸው፡፡”
12በለዓም መለሰለት እንዲህም አለ፣ “ያህዌ በአፌ ላይ ያደረገውን ብቻ ለመናገር መጠንቀቅ የለብኝምን?”
13ስለዚህም ባላቅ እንዲህ አለው፣ “እባክህ ከእኔ ጋር ልታያቸው ወደ ምትችልበት ሌላ ቦታ ና፡፡ ከእነርሱ ሁሉንም ሳይሆን፣ በቅርብ ያሉትን ብቻ ታያለህ፡፡ በዚያ እነርሱን ትረግምልኛለህ፡፡”
14ስለዚህ በለዓምን ወደ ጾፊም ሜዳ፣ ወደ ፊስጋ ተራራ ጫፍ ይዞት ሄደና ተጨማሪ ሰባት መሰዊያዎችን አበጀ፡፡ በእያንዳንዱ መሰዊያ አንድ በሬና አንድ አውራ ጠቦት ሰዋ፡፡
15ከዚያ በለዓም ባላቅን እንዲህ አለው፣ “እኔ በዚያ ያህዌን ለመገናኘት ስሄድ፣ አንተ እዚህ በሚቃጠል መስዋዕትህ አጠገብ ቁም፡፡”
16ያህዌ በለዓምን ተገናኝቶ በአፉ ምልክት አኖረ፡፡ እንዲህም አለው፣ “ወደ ባላቅ ተመለስና መልዕክቴን ንገረው፡፡”
17በለዓም ወደ ባላቅ ተመልሶ በሚቃጠል መስዋዕቱ አጠገብ አገኘው፣ የሞአብ መሪዎችም ከእርሱ ጋር ነበሩ፡፡ ባላቅ እንዲህ ሲል ጠየቅ፣ “ያህዌ ምን ነገረህ?”
18በለዓም ትንቢቱን መናገር ጀመረ፡፡ እንዲህም አለ፣ “ባላቅ፣ ተነስና አድምጥ፡፡ አንተ የሴፎር ልጅ እኔን አድምጠኝ፡፡
19እግዚአብሔር ይዋሽ ዘንድ ሰው አይደለም፣ ወይም ሀሳቡን ይቀየር ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፡፡ ላያደርግ አንዳች ነገር ቃል ይገባልን? ላይፈጽመውስ አንዳች ነገር አደርጋለሁ ይላልን?
20እነሆ፣ ለመባረክ ታዝዣለሁ፡፡ እግዚአብሔር በረከትን ለቋል፣ እኔ ልከለክል አልችልም፡፡
21እርሱ በያዕቆብ ላይ አንዳች ችግር ወይም በእስራኤል ላይ ድካም አላየም፡፡ ያህዌ አምላካቸው ከእነርሱ ጋር ነው፣ የንጉሳቸውም እልልታ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡
22እግዚአብሔር እንደ ጎሽ በሆነ ሀይል ከግብጽ አወጣቸው፡፡
23በያዕቆብ ላይ የሚሰራ ምንም አስማት የለም፣ የትኛውም ሟርት እስራኤልን አይጎዳም፡፡ ይልቁንም ስለያዕቆብና ስለ እስራኤል እንዲህ ይባልላቸዋል፣ ‘እግዚአብሔር ያደረገውን እዩ!’
24እዩ፣ ህዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይነሳል፣ እንደ አንበሳ ተነስቶ ያጠቃል፡፡ ያደነውን እስኪበላ የገደለውን ደም እስኪጠጣ አያርፍም፡፡”
25ከዚያ ባላቅ በለዓምን እንዲህ አለው፣ “እነርሱን ባትረግማቸው እንኳን ጨርሰህ አትባርካቸው፡፡”
26በልዓም ግን ባላቅን መልሶ እንዲህ አለው፣ “እንድናገር ያህዌ የነገረኝን ሁሉ መናገር እንዳለብኝ አልነገርኩህምን?”
27ስለዚህም ባላቅ ለበለዓም እንዲህ ሲል መለሰለት፣ “አሁን ና፣ እኔ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፡፡ ምናልባት በዚያ እነርሱን እንድትረግምልኝ እግዚአብሔር ይፈቅድልህ ይሆናል፡፡”
28ስለዚህም ባላቅ በለዓምን ምድረበዳውን ቁልቁል ወደሚያይበት ወደ ፌጎር ተራራ ጫፍ ወሰደው፡፡
29በለዓም ባላቅን እንዲህ አለው፣ “በዚህ ስፍራ ሰባት መሰዊያዎችን አብጅና ሰባት በሬዎች እንዲሁም ሰባት አውራ በጎች አዘጋጅ፡፡”
30ስለዚህ ባላቅ ባለዓም እንደነገረው አደረገ፤ በእያንዳንዱ መሰዊያ ላይ አንድ በሬና አንድ አውራ በግ ሰዋ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።