1የይስዓር ልጅ ቆሬ የቀዓት ልጅ የሌዊ ልጅ፣ ከኤሊያብ ልጆች ከዳታንና አቤሮን ጋር፣ እንዲሁም የፍሬት ልጅ ኦን፣ የሮቤል ትውልዶች ሆነው ተሰበሰቡ፡፡
2እነርሱም ከእስራኤል ሌሎች ሰዎች ጋር ሆነው በሙሴ ላይ ተቃውመው ተነሱ፣ የማህበረሰቡ መሪዎች የሆኑ የታወቁ ሁለት መቶ ሀምሳ ሰዎች ተነሱበት፡፡
3ሙሴንና አሮንን ለመቃወም በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ ሙሴንና አሮንን እንደዚህ አሏቸው፣ “እናንተ ያለ ልክ አብዝታችሁታል፡፡ መላው ማህበረሰብ ቅዱስ ነው፣ ለያህዌ የተለየ ነው፣ እያንዳንዳቸው ንጹሃን ናቸው፣ ያህዌም በመሀከላቸው ነው፡፡ ለምን ራሳችሁን ከተቀረው የያህዌ ማህበረሰብ ከፍ ታደረጋላችሁ?”
4ሙሴ ይህንን ሲሰማ፣ በግምባሩ ተደፋ፡፡
5ለቆሬና ለእርሱ ወገኖች እንዲህ አላቸው፤ “ማለዳ ያህዌ የእርሱ የሆኑት እነማን እንደሆኑ ይለያል፣ ማን ለእርሱ እንደ ተለየ ይታወቃል፡፡ የመረጠውን ሰው ወደ ራሱ ይለያል፡፡ የመረጠውን ወደ ራሱ ያመጣዋል፡፡
6ቆሬና የአንተ ቡድን ሁላች ይህን አድርጉ፡፡ ማጠንት ያዙ
7ነገ በያህዌ ፊት እሳትና እጣን በላያቸው ጨምሩ፡፡ ያህዌ የሚመርጠው ሰው እርሱ፣ ለያህዌ የተለየ ይሆናል፡፡ እናንተ የሌዊ ትውልዶች ከልክ አልፋችኋል፡፡”
8እንደገና፣ ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፣ “አሁን ስማ፣ እናንተ የሌዊ ትውልዶች
9የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማህበረሰብ እናተን ለይቶ ወደራሱ ማቅረቡ፣ በያህዌ የማደሪያ ድንኳን እንድታገለግሉ ማድረጉ፣ እነርሱን እንድታገለግሉ በማህበረሰቡ ፊት እናንተን ማቆሙ ለእናንተ ትንሽ ነገር ነውን?
10እርሱ አንተን፣ የቅርብ ዘመዶችህንና የሌዊ ትውልዶችን ከአንተ ጋር አቅርቧችኋል፣ እናንተ ግን ክህነቱንም እየፈለጋችሁ ነው!
11አንተና የአንተ ተከታዮች ሁሉ በያህዌ ላይ በአንድ ላይ ተነሳችሁ፡፡ ስለዚህ ለምን እግዚአብሔርን በሚታዘዘው በአሮን ላይ ታጉረመርማላችሁ?”
12ከዚያ ሙሴ የኤልያብን ልጆች ዳታንንና አብሮንን ጠራቸው፣ እነርሱ ግን እንዲህ አሉ፣ “እኛ ወደዚያ አንመጣም፡፡
13እኛን በምድረበዳ ልትገድለን ወተትና ማር ከሚፈስባት ምድር ያወጣኸን ትንሽ ነገር ሆኖ ነውን? አሁን ራስህን በእኛ ላይ ገዢ ማድረግ ትፈልጋለህ!
14በተጨማሪም፣ እኛን ወተትና ማር ወደምታፈስ ምድር አላመጣኸንም፣ ወይም እርሻዎችንና የወይን ተክሎችን ውርስ አድርገህ አልሰጠኸንም፡፡ አሁን በባዶ ተስፋ ልታታልለን ትፈልጋህ? ወደ አንተ አንመጣም፡፡”
15ሙሴ እጅግ ተቆጥቶ ነበር፣ ወደ ያህዌ እንዲህ ሲል ጮኸ፣ “መስዋዕታቸውን አትቀበል፡፡ ከእነርሱ አንድ አህያ እንኳን አልወሰድኩም፣ ከእነርሱ አንዳቸውንም አልበደልኩም፡፡”
16ከዚያ ሙሴ ቆሬን እዲህ አለው፣ “ነገ አንተና የአንተ የሆኑ በያህዌ ፊት ይቅረቡ፤ አንተ፣ እነርሱና አሮን በያህዌ ፊት ቁሙ፡፡
17እያንዳንዱ የራሱን ማጠኛ ይያዝና በውስጡ እጣን ይጨምርበት፡፡ ከዚያ እያንዳንዱ ሰው ማጠኛውን በያዌ ፊት ያምጣ፣ ሁለት መቶ አምሳዎቹ ሰዎችህ ማጠኛዎቻቸውን ይዘው ይቅረቡ፡፡ አንተና አሮንም ደግሞ የየራሳቸችሁን ማጠኛ አምጡ፡፡”
18ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ማጠኛውን ወሰደ፣ በውስጡ እሳት አደረገ፣ እጣንም ጨመረበት ከሙሴና ከአሮን ጋር በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ቆሙ፡፡
19ቆሬ መላውን ማህበረሰብ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ በሙሴና በአሮን ላይ በተቃውሞ ሰበሰበ፣ የያህዌ ክብር ደግሞ ለማህበረሰቡ ሁሉ ታየ፡፡
20ከዚያ ያህዌ ለሙሴና ለአሮን እንዲህ ሲል ተናገረ፣
21”በቶሎ ከማጠፋው ከዚህ ማህበረሰብ መሀል ራሳችሁን ለዩ፡፡”
22ሙሴና አሮን በግንባራቸው ተደፍተው እንዲህ አሉ፣ “ የሰው ልጆች ሁሉ መንፈስ አምላክ የሆንክ እግዚአብሔር ሆይ፣ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሰራ ማህበረሰቡን በሙሉ ልትቆጣ ይገባልን?”
23ያህዌ ለሙሴ እንዲህ ሲል መለሰለት፣
24”ለማህበረሰቡ እንዲህ በል፣ ‘ከቆሬ፣ ከዳታንና ከኤብሮን ድንኳኖች ውጡ፡፡’”
25ከዚያ ሙሴ ተነስቶ ወደ ወደ ዳታንና አብሮን ሄደ፤ የእስራኤል መሪዎች እርሱን ተከተሉት፡፡
26ለማህበረሰቡ እንዲህ ብሎ ተናገረ፣ “አሁን የእነዚህን ክፉ ሰዎች ድንኳኖች ልቀቁ፣ የእነርሱ የሆነውን አንዳች ነገር አትንኩ፣ አለበለዚያ በእነርሱ ኃጢአቶች ሁሉ እናንተም ትጠፋላችሁ፡፡”
27ስለዚህ በቆሬ፣ በዳታንና በኤብሮን ድንኳኖች በእያንዳንዱ አቅጣጫ የሚገኝ ማህበረሰብ ከእነርሱ ራቁ፡፡ ዳታንና አብሮን ወደ ውጭ ወጥተው ከሚስቶቻቸው፣ ከወንዶች ልጆቻቸውና ከህፃናቶቻቸው ጋር በድንኳኖቸው ደጃፍ ላይ ቆሙ፡፡
28ከዚያ ሙሴ እንዲህ አለ፣ “በዚህም ያህዌ እነዚህን ስራዎች ሁሉ እንድሰራ እንደላከኝ ታውቃላችሁ፣ እኔ በራሴ ፈቃድ እነዚህን ነገሮች አልሰራኋቸውም፡፡
29እነዚህ ሰዎች በተለመደው ሁኔታ ተፈጥሯዊ ሞት ቢሞቱ፣ ያህዌ እኔን አላኝም ማለት ነው፡፡
30ነገር ግን ያህዌ ምድሪቷን ቢከፍትና እርሷ እንደ ተከፈተ አፍ ሆና፣ ከነቤተሰቦቻቸው ብትውጣቸው፣ ደግሞም በህይወታቸው ሳሉ ወደ ሲኦል ቢወርዱ፣ ያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች ያህዌን እንደናቁ ታውቃላችሁ፡፡”
31ሙሴ እነዚህን ቃላቶች ተናግሮ እንደጨረሰ፣ ምድሪቱ ከነዚህ ሰዎች በታች ተከፈተች፡፡
32መሬት አፏን ከፈተችና ዋጠቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው፣ እና የቆሬ ሰዎች ሁሉ እንዲሁም ያላቸው ሀብት ሁሉ ተዋጠ፡፡
33እነርሱና በየቤተሰባቸው እያንዳንዱ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ወረዱ፡፡ መሬት በላያቸው ተከደነች፣ እናም በዚህ መንገድ ከማህበረሰቡ መሀል ጠፉ፡፡
34በዙሪያቸው የነበሩ እስራኤላዊያን ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሳ ሸሹ፡፡ እንዲህ እያሉም ጮኹ፣ “መሬት እኛንም ደግሞ ልትውጠን ነው!”
35እሳት ከያህዌ ዘንድ ወጥታ የሚያጥኑትን 250 ሰዎች በላቻቸው፡፡
36ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣
37”ጥናዎቹ ለእኔ የተለዩ ናቸውና ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአላዓዛር ከሚጤሱት የተረፉትን ጥናዎች እንዲወስድ ንገረው፡፡ ከዚያ ረመጡን ይበትኑት፡፡
38በኃጠአታቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡትን ሰዎች ጥናዎች ውሰድ፡፡ ጥናዎቹ የተቀጠቀጡ ሰሀኖች ተደርገው ለመሰዊያው መሸፈኛነት ይዋሉ፡፡ ለእኔ የተለዩ ናቸውና፣ እነዚያ ሰዎች በእኔ ፊት ያቅርቧቸው፡፡ እነዚህም ለእስራኤል ሰዎች ለእኔ መገኘት ምልክት ይሆናሉ፡፡”
39ካህኑ አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩትን የናስ ጥናዎች ይውሰድና ለመሰዊያው መሸፈኛነት ይቀጥቅጣቸው፣
40ይህም፤ ለእስራኤል ሰዎች ማስታወሻ እንዲሆን፣ ማንም የአሮን ትውልድ ያልሆነ መጻተኛ በያህዌ ፊት ለማጠን እንዳያቀርብና እንደ ቆሬና እንደ እርሱ ተከታዮች እንዳይሆኑ ያህዌ በሙሴ በኩል እንዳዘዘው ልክ እንደዚያ እንዳይሆንባቸው ነው፡፡
41ነገር ግን በማግስቱ የእስራኤል ማህበረሰብ በሙሉ በሙሴና በአሮን ላይ በማጉረምረም ተነሱባቸው፡፡ እነዲህም አሉ፣ “እናንተ የያህዌን ሰዎች ገድላችኋል፡፡”
42ከዚያም እንዲህ ሆነ፣ ማህበረሰቡ በሙሴና በአሮን ላይ በተቃውሞ ሲሰበሰብ፣ ወደ መገናኛው ድንኳን አሻግሮ ሲመለከቱ፣ እነሆ ደመናው ድንኳኑን ሸፍኖት ነበር፡፡ የያህዌ ክብር ታየ፣
43እናም ሙሴና አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ወደፊት መጡ፡፡
44ከዚያ ያህዌ ሙሴን ተናገረው፡፡ እንደህም አለው፣
45“ከዚህ ማህበረሰብ ፊት ራቅ፣ እኔ በቶሎ አጠፋቸዋለሁ፡፡” ከዚያ ሙሴና አሮን በግምባራቸው ተደፉ፡፡
46ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፣ “ማጥንቱን ውሰድ፣ ከመሰዊያው እሳት ወስደህ አድርግበት፣ በውስጡ እጣን ጨምርበት፣ በቶሎ ወደ ማህበረሰቡ ውሰደው፣ እናም ለእነርሱ አስተሰርይ፣ ምክንያቱም ከያህዌ ዘንድ ቁጣ እየመጣ ነው፡፡ መቅሰፍቱ ጀምሯል፡፡”
47ስለዚህም አሮን ሙሴ እንደመራው አደረገ፡፡ ወደ ማህበረሰቡ መሃል ሮጠ፡፡ መቅሰፍቱ በህዝቡ መካከል በፍጥነት መስፋፋት ጀመሮ ነበር፣ ስለዚህም እርሱ እጣኑን ጨምሮ ለህዝቡ ማስተሰርያ አደረገ፡፡
48አሮን በሙታኑና በህያዋኑ መሀል ቆመ፣ በዚህ መንገድ መቅሰፍቱ ቆመ፡፡
49በመቅሰፍቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 14700 ነበር፣ ይህም በቆሬ ምክንያት የሞቱትን ሳይጨምር ነው፡፡
50አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ ወደ ሙሴ ተመለሰ፣ መቅሰፍቱም አበቃ፡፡