1ህዝቡ ያህዌ እየሰማ ስለ ችግሮቻቸው አጉረመረሙ፡፡ ያህዌ ህዝቡን ሰምቶ ተቆጣ፡፡ ከያህዌ ዘንድ እሳት መጥታ በሰፈሩ ዙሪየ ከነበሩ ሰዎች አንዳንዶችን በላች፡፡
2ከዚያም ህዝቡ ወደ ሙሴ ጮኸ፣ ስለዚህም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ እሳቱም ቆመ፡፡
3ስፍራው ተቤራ ተብሎ ተጠራ፣ ምክንያቱም የያህዌ እሳት ከመሀላቸው ሰዎችን አቃጥላለች፡፡
4አንዳንድ ባዕዳን ከእስራኤላውያን ትውልዶች ጋር መስፈር ጀመሩ፡፡ እነርሱ የተሻለ ምግብ መብላት ፈለጉ፡፡ ከዚያ የእስራኤል ሰዎች ማልቀስና “እንድንበላ ማን ስጋ ሊሰጠን ይችላል” ማለት ጀመሩ፡፡
5በግብጽ በነጻ እንበላ የነበረውን አሳውን፣ ዱባውን፣ በጢኹን፣ ባሮ ሽንኩርቱን፣ ቀይ ሽንኩርቱንና ነጭ ሽንኩርቱን እናስታውሳለን፡፡
6አሁን ደካሞች ነን፡፡ ከመና በስተቀር ምንም የምንበላው የለም፡፡”
7መና እንደ ድንብላል ፍሬ ያለ መልክ ነበረው፡፡ ሙጫ ይመስላል፡፡
8ሰዎቹ እየተዘዋወሩ ይሰበስቡታል፡፡ በወፍጮ ይፈጩታል፣ በሙጫ ያደቁታል፣ በገንቦዎቹ ይቀቅሉታል፣ ቂጣ አድርገውም ይጋግሩታል፡፡ እንደ ንጹህ የወይራ ዘይት ይጣፍጣል፡፡
9ምሽት በሰፈር ውስጥ ጤዛ ሲወርድ፣ መናውም ይወርዳል፡፡
10ሙሴ ህዝቡ በየቤቱ ሲያለቅስ አዳመጠ፣ ደግሞም እያንዳንዱ ሰው በእርሱ ድንኳን ደጃፍ ነበር፡፡ ያህዌ በጣም ተቆጥቶ ነበር፣ ደግም የእነርሱ ማጉረምረም በሙሴ እይታ ስህተት ነበር፡፡
11ሙሴ ወደ ያህዌ እንዲህ ሲል ጮኸ፣ “ለምን ባሪያህን እንዲህ አስጨነከው? ስለምን በእኔ ደስ አልተሰኘህም? የዚህን ህዝብ ሁሉ ሸክም እንድሸከም አደረግከኝ፡፡
12እኔ ይህን ህዝብ ሁሉ ፀንሼዋለሁን? ‘አባት ልጁን እነደሚያቅፍ ይህን ህዝብ ወደ ደረትህ አስጠግተህ ተሸከመው’ ትለኝ ዘንድ እኔ ወልጃቸዋለሁን?’ ትሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻቸው ወደ ማልክላቸው ምድር እንዲገቡ እኔ ልሸከማቸውን?
13ለእነዚህ ሁሉ ሰዎች የምሰጣቸውን ስጋ ከየት አገኛለሁ? በእኔ ፊት እያለቀሱ እንዲህ ይላሉ ‘የምንበላው ስጋ ስጠን፡፡’
14እኔ ብቻዬን ይህን ሁሉ ህዝብ ልሸከም አልችልም፡፡ እጅግ በዝተውብኛል፡፡
15እንዲህ እስካደረግኸኝ ድረስ፣ አሁኑኑ ግደለኝ፣ ለእኔ መልካም ከሆንክ፣ መከራዬን ከእኔ አርቅ፡፡”
16ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ከእስራኤል መሪዎች ሰባዎቹን ወደ እኔ አምጣ፡፡ የህዝቡ መሪዎችና አለቃዎች መሆናቸውን እርግጠኛ ሁን፡፡ ከአንተ ጋር እንዲቆሙ ወደ መገናኛው ድንኳን አምጣው፡፡
17እኔ ወርጄ በዚያ ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፡፡ ከአንተ ላይ ካለው መንፈስ ጥቂት ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፡፡ እነርሱ ከአንተ ጋር የህዝቡን ሸክም ይሸከማሉ፡፡ አንተ ብቻህን ሸክሙን አትሸከምም፡፡
18ለህዝቡ እንዲህ በል፣ ‘ነገ ራሳችሁን ለያህዌ ለዩ፡፡ ያህዌ እየሰማ አልቅሳችኋልና፣ በእርግጥ ስጋ ትበላላች፡፡ እንዲህ ብላችኋል፣ “እንበላ ዘንድ ማን ስጋ ይሰጠናል? ለእኛስ በግብጽ መሆን መልካም ነበር፡፡” ስለዚህ ያህዌ ስጋ ይሰጣችኋል፣ እናም ስጋ ትበላላችሁ፡፡
19ስጋ የመትበሉት ለአንድ ቀን፣ ለሁለት ቀናት፣ ለአምስት ቀናት፣ ለአስር ቀናት ወይም ለሃያ ቀናት አይደለም፣
20ነገር ግን በአፍንጫችሁ እስኪወጣ ድረስ ወር ሙሉ ስጋ ትበላላችሁ፡፡ ነገሩ ያስጸይፋችኋል፣ ምንያቱም በመሀላችሁ ያለውን ያህዌ እምቢ ብላችኋል፡፡ በፊቱ አልቅሳችኋል፡፡ እንዲህ ብላችኋል፣ “ለምን ከግብጽ ወጣን?”
21ከዚያ ሙሴ እንዲህ አለ፣ “እኔ ከ600000 ሰዎች ጋር ነኝ፣ አንተ ግን እንዲህ አልክ፣ ‘ወር ሙሉ እንዲበሉ ስጋ አበላቸዋለሁ፡፡’
22እነርሱን ለማጥገብ እኛ እንስሳትንና የከብት መንጋ ሁሉ እናርዳለን? እነርሱን ለማርካት የባህር አሶችን ሁሉ እናጠምዳን?”
23ያህዌ ሙሴን እንዲህ አለው፣ “እጄ አጭር ናትን? አሁን ቃሌ እውነት መሆን አለመሆኑን ታያለህ፡፡”
24ሙሴ ወጥቶ ለህዝቡ የያህዌን ቃላት ነገራቸው፡፡ ሰባዎቹን የህዝብ መሪዎች ሰበሰበና በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው፡፡
25ያህዌ በደመና ውስጥ ወረዳና ሙሴን ተናገረው፡፡ ያህዌ በሙሴ ላይ ከነበረው መንፈስ ጥቂት ወሰደና በሰባዎቹ ሽማግሌዎች ላይ አደረገው፡፡ መንፈሱ ሲያርፍባቸው፣ ትንቢት ተናገሩ፣ ነገር ግን በዚያ ወቅት እንጂ በሌላ ጊዜ ደግመው አልተነበዩም፡፡
26አልዳድና ሞድ የተባሉ ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፡፡ መንፈሱ በእነርሱ ላይም አረፈ፡፡ ስሞቻቸው በመዝገብ ተጽፎ ነበር፣ ነገር ግን ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ እነርሱም በሰፈር እያሉ ተነበዩ፡፡
27በሰፈር የነበረ አንድ ወጣት ሰው ወደ ሙሴ ሮጦ መጥቶ እንዲህ አለው፣ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ውስጥ እየተነበዩ ነው፡፡”
28ከእርሱ የተመረጡ ሰዎች አንዱ የሆነው የሙሴ ረዳት የነዌ ልጅ ኢያሱ ሙሴን እንዲህ አለው፣ “አለቃዬ ሙሴ ሆይ፣ ከልክላቸው፡፡”
29ሙሴ እያሱን እንዲህ አለው፣ “አንተ ለእኔ ተቆርቁረህ ነውን? እኔ መላው የያህዌ ህዝቦች ነቢያት ቢሆኑ እርሱ በሁሉም ላይ መንፈሱን ቢያደርግ እመኛለሁ!”
30ከዚያ ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ፡፡
31ከዚያ ከያህዌ ዘንድ ነፋስ ወጥቶ ከባህር ድርጭቶችን አመጣ፡፡ ከሰፈሩ በአንድ በኩል የአንድ ቀን የእግር መንገድ ርቀት ላይ፣ ደግሞም በሌላኛው በኩል በአንድ ቀን የእግር መንገድ ርቀት ድረስ ድርጭቶቹ ወደቁ፡፡ ድርጭቶቹ ሰፈሩን ከመሬት ሁለት ኪዩብ ከፍታ በሚሆን መጠን ሞሉት፡፡
32ሰዎቹ ያን ዕለት ምሽቱን ጨምሮ እንዲሁም በማግስቱም ድርጭቶችን በመሰብሰብ ሥራ ተጠምደው ነበር፡፡ ማንም ከአስር የቆሮስ መስፈሪያ ያነሰ ድርጭት አልሰበሰበም፡፡ በሰፈሩ ሁሉ ድርጭቶቹን ተከፋፈሉ፡፡
33ስጋው ገና በጥርሳቸው ውስጥ እያላመጡት ሳለ፣ ያህዌ በእነርሱ ላይ ተቆጣ፡፡ ህዝቡን በታላቅ በሽታ መታው፡፡
34በዚያ ሥፍራ ስጋ ለማግኘት የጎመጁትን ሰዎች ስለቀበሯቸው የስፍራው ስም ቂብሮት ሃታአባ ተባለ፡፡
35ሰዎቹ ከቂብሮት ሃታአባ ወደ ሰፈሩበት ወደ ሐጽሮት ተጓዙ፡፡