1በዚያው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ ህዝቡ በአንድነት ተሰበሰበ፡፡ ለጥቂት ጊዜ አልበሉም፣ ሰንዴና ሌላ እህል ለመያዣ የተዘጋጁ ጆንያዎችን ልብስ አደርገው ለበሱ፣ በራሳቸው ላይ የምድር ትቢያ ነሰነሱ፡፡
2የእስራኤል ትውልዶች ራሳቸውን ከሌሎች መጻተኞች ሁሉ ለዩ፡፡ በዚያ ቆመው የራሳቸውን ኃጢአትና አባቶቸው የሰሯቸውን ክፉ ነገሮች ተናዘዙ፡፡
3ቆመው ለሶስት ሰዓቶች ከያህዌ ህግ አነበቡ፣ ደግሞም ለሌላ ሶስት ሰዓቶች በያህዌ ፊት ኃጢአቶቻቸውን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ፣ ከዚያ በመሬት ላይ ተደፍተው እርሱን አመለኩ፡፡
4ሌዋውያኑ በደረጃው ላይ ቆመው ነበር፡፡ እነርሱም ኢያሱ፣ ባኒ፣ ቀድምኤል፣ ሰበንያ፣ ቡኒ፣ ሰራብያ፣ ባኒ፣ እና ከናኒ ነበሩ፡፡
5ከዚያ የሌዋውያኑ መሪዎች በህዝቡ ፊት ተሰየሙ፡፡ እነርሱም ኢያሱ፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ ነበሩ፡፡ እነርሱም እንዲህ አሉ፣ “ቁሙና ከዘለዓም እስከ ዘለዓለም ለነበረውና ለሚኖረው ለአምላካችሁ ለያህዌ ምስጋና አቅርቡ! ያህዌ፣ የከበረውን ስምህን እናወድሳለን! መልካምና ድንቅ ከሆነው ነገር ሁሉ ስምህ የበለጠ ጠቃሚ ነው!
6አንተ ያህዌ ነህ፣ ሌላ ማንም ዘለዓለማዊና በራሱ ህልውና ያለው የለም፡፡ አንተ ሰማይንና ሰማያትን ከሁሉም በላይ ሰራህ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽሙትን መላዕክት ሁሉ ፈጠርህ፡፡ ምድርንና በላይዋ ያሉትን አንተ አበጀህ፣ ባህሮችንና በውስጣቸው የሚገኙትን ሰራህ፡፡ አንተ ለሁሉም ነገር ህይወት ሰጠህ፡፡ በሰማይ ያሉ የመላዕክት ሰራዊት ሁሉ አንተን ያመልኩሃል፡፡
7ያህዌ፣ አንተ እግዚአብሔር ነህ፡፡ አንተ አብራምን መርጠህ ከኡር ከከለዓድ አወጣኸው፡፡ አብርሃም የሚል ስም ሰጠኸው፡፡
8አንተ የእርሱን ልብ አየህ፣ የታመነ ሰው እንደነበረ ታውቅ ነበር፡፡ ከዚያ ከእርሱ ጋር በደም ቃል ኪዳን አደረግህ፣ የከነዓናዊያንን፣ የኬጢያውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የጌርሳውያንን ምድር ለትውልዶች እንደምትሰጠው ቃል ገባህለት፡፡ እና አንተ ያህዌ፣ ቃል የገባኸውን ፈጸምክ፣ ምክንያቱም አንተ ሁልጊዜም ትክክል የሆነውን ታደርጋለህ፡፡
9አባቶቻችን በግብጽ ምን ያህል ይሰቃዩ እንደ ነበር አንተ አይተሃል፡፡ ቀይ ባህር አጠገብ በነበሩ ጊዜ ወደ አንተ ለእርዳታ ሲጮኹ ሰማሃቸው፡፡
10ንጉሱ፣ አገልጋዮቹና የእርሱ ህዝቦች ሁሉ እንዲጨነቁ የሚያደርግ ብዙ አይነት ተአምራቶችን አደረግህ፡፡ በዚህም፣ አንተ፣ ያህዌ፣ ለራስህ ስም አደረግህ፣ እናም ዛሬም ድረስ ስምህ ታላቅ መሆኑ ይታወቃል!
11ለሁለት ክፍል ከፈልህ፣ እናም ህዝብህ በደረቅ ምድር በመሀሉ ተራመደ፡፡ አንተ የግብጽን ወታደሮች በውሃዎች ስር አሰመጥክ፣ ድንጋይ በጥልቅ ውሃ እንደሚሰምጥ ሰመጡ!
12በቀን ደመና እንደ አምድ እየተከተላቸው መራሃቸው፣ በምሽት ወዴት እንደሚሄዱ ልታሳያቸው የእሳት አምድ ብርሃን ሰጠሃቸው፡፡
13አንተ ከሰማይ ወርደህ በሲና ተራራ ላይ አናገርካቸው፡፡ የታመኑና እውነተኛ የሆኑ ብዙ ድንጋጌዎችንና ደንቦችን ሰጠሃቸው፣ መልካም የሆኑ ትዕዛዛትንና ህግጋትንም ሰጠሃቸው፡፡
14ስለ ቅዱሱ ሰንበትህ አስተማርካቸው፣ ትዕዛዛትንና ህግጋትን እንዲሁም ይፈጽሟቸው ዘንድ የህግጋት አይቶችን በአገልጋይህ በሙሴ በኩል ሰጠሃቸው፡፡ እርሱ ለህዝቡ ይነግራቸዋል፡፡
15በተራቡ ጊዜ፣ ከሰማይ እንጀራ ሰጠሃቸው፡፡ በተጠሙ ጊዜ፣ ከአለት ውሃ አጠጣሃቸው፡፡ ትሰጣቸው ዘንድ በመሀላ ቃል የገባህላቸውን ምድር ሄደው እንዲወርሱ ነገርካቸው፡፡
16ነገር ግን አባቶቻችን በጣም ኩራተኞችና ግትሮች ነበሩ፡፡ እንዲያደርጉት ያዘዝካቸውን ለማስማት እንኳን ተቃወሙ፡፡
17አንተን ለመስማት አልወደዱም፡፡ ለእነርሱ ያደረግከውን ተአምራቶች ሁሉ ረሱ፡፡ ደንዳኖች ሆኑ፣ በአንተ ላይ ስላመጹ፣ ዳግም ባሪያዎች ወደሚሆኑበት! ወደ ግብጽ የሚመልሳቸውን መሪ መረጡ፡፡ ነገር ግን አንተ ደግመህ ደጋግመህ ይቅር የምትል አምላክ ነህ፡፡ ለመቆጣት አትቸኩልም፣ ለእነርሱ ያለህ ፍቅርም በፍጹም የማያልቅና ታላቅ ነው፡፡ እነርሱን አልተውካቸውም፡፡
18ስለዚህ፣ ምንም እንኳን የከበሩ ማዕድናትን አቅልጠው ጥጃ የሚመስል ጣኦት ቢቀርጹም ሙሉ ለሙሉ አልተወካቸውም፡፡ እግዚአብሔርን በመራገምና እርሱ የከለከለውን በማድረግ፣ ይህን ጥጃ ወደ ህዝቡ አቅርበው፣ ‘ይህ እናንተን ከግብጽ ያወጣችሁ አምላካችሁ ነው’ አሉ፡፡
19አንተ ሁልጊዜም መሃሪ ነህ፣ በበረሃ በነበሩ ጊዜም አልተውካቸውም፡፡ እንደ ታላቅ አምድ የሆነው ብሩህ ደመና በቀን ይመራቸው ነበር፣ የእሳት ደመናው በምሽት የሚሄዱበትን ይመራቸው ነበር፡፡
20መልካሙን መንፈስህን እንዲመራቸው ላክህላቸው፡፡ በተራቡ ጊዜ መናውን አልከለከልካቸውም፣ በተጠሙ ጊዜ ውሃ ሰጠሃቸው፡፡
21ለአርባ አመታት በበረሃ ተጠነቀቅክላቸው፡፡ በነዚያ ጊዜያት ሁሉ፣ የአንዳች ነገር ጉድለት አልነበረባቸውም፡፡ ልብሳቸው አላረጀም፣ እግሮቻቸው አላበጡም፡፡
22የአህዛብን ነገስታትና መንግስታት ሰጠሃቸው፡፡ በዚህ ምድር እጅግ ሩቅ የሆነውን ስፍራ እንኳን ርስት አድርገው ወሰዱ፡፡ ንጉስ ሴዎን የሚገዛውን ምድር ከሐሴቦን ወሰዱ እንዲሁም የንጉስ ዐግን ግዛት ባሳንን ወረሱ፡፡
23አባቶቻችንን በሰማይ እንዳሉ ከዋክብት እንዲበዙ ረዳሃቸው፣ አባቶቻቸው ይገቡባትና ይኖሩባት ዘንድ ወደ ነገርካቸው ወደዚህ ምድር አመጣሃቸው፡፡
24የእስራኤል ህዝቦች ገብተው በዚያ ከሚኖሩ ህዝቦች ምድሪቱን ወሰዱ፡፡ አንተ ከነአናዊያንንና ነገስታቶቻውን እንዲያሸንፉ ረዳሃቸው፣ አንተም በዚይ ምድር ህዝቦች ላይ ገዛህ፡፡ በእነዚያ ህዝቦች ላይ ማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ እንዲያደርጉ አንተ ረዳሃቸው፡፡
25አባቶቻችን ዙሪያቸው የተቀጠሩትን ከተሞች ያዙ፡፡ የለምለሚቱን ምድር ሀብት ወረሱ፡፡ በመልካም ነገሮች የተሞሉትን ቤቶችና የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶችን ወረሱ፡፡ የወይን እርሻዎችን፣ የወይራ ዛፎችን እና የፍራፍሬ ዛፎችን ወረሱ፡፡ የፈለጉትን ሁሉ በልተው ረኩ፡፡ አንተ በሰጠሃቸው ብዙ ስጦታዎች ራሳቸውን ደስ አሰኙ፡፡
26ነገር ግን አልታዘዙህም በአንተ ላይም አመጹ፡፡ በህግጋትህ ላይ ጀርባቸውን ሰጡ፡፡ ወደ አንተ መመለስ እንዳለባቸው ያስጠነቀቋቸውን ነቢያት ገደሉ፡፡ ስምህን ተራገሙ፡፡
27ስለዚህም ያሸንፏቸው ዘንድ ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው፡፡ ነገር ግን ጠላቶቻቸው ባሰቃይዋቸው ጊዜ፣ ወደ አንተ ጮኹ፡፡ አንተ ከሰማይ ጩኸታቸውን ሰማህ፣ አንተ እጅግ መሃሪ ስለሆንክ ከጠላቶቻቸው ነጻ የሚያወጧቸውን ሁሉ ላክህላቸው፡፡ እነርሱም ነፃ አወጧቸው፡፡
28ነገር ግን እንደገና የሰላም ጊዜ ከሆነ በኋላ፣ አባቶቻችን ዳግም አንተ የምትጠላውን ክፉ ነገሮች አደረጉ፡፡ ስለዚሀ ጠላቶቻቸው እንዲያሸንፏቸውና እንዲገዟቸው ፈቀድህ፡፡ ነገር ግን እንደገና እንድትረዳቸው በጮኹ ጊዜ ሁሉ አንተ ከሰማይ ሆነህ ትሰማቸዋለህ፣ አንተ በምህረት የተሞላህ ስለሆንክ ትታደጋቸዋለህ፡፡
29አንተ እንደገና ህግጋትህን እንዲታዘዙ ታስጠነቅቃቸዋለህ፣ ነገር ግን እነርሱ ኩራተኞችና ግትሮች ይሆናሉ፣ ድንጋጌዎችህንም ይጥሳሉ፡፡ እንዲያደርጉ ያዘዝካቸውን ሳይታዘዙ ይቀራሉ፡፡ ለትዕዛዛትህ አንዳች ትኩረት አይሰጡም፡፡ አንተን መስማትን በግትርነት ይቃወማሉ፡፡
30አንተ ለብዙ አመታት ታግሰሃቸው ነበር፡፡ መንፈስህ ለነቢያት በሚሰጣቸው መልዕክት አማካይነት ታስጠነቅቃቸዋለህ፡፡ ነገር ግን እነርሱን እነዚያን መልዕክቶች አይሰሙም፡፡ ስለዚህ እንደገና በአጠገባቸው ያሉ የአህዛብ ነገስታት እንዲያሸንፏቸው ትፈቅዳለህ፡፡
31ነገር ግን አንተ በይቅርታ ስለተሞላህ ሙሉ ለሙሉ አታጠፋቸውም ወይም ለዘለዓለም አትተዋቸውም አንተ መሀሪና ይቅር ባይ አምላክ ነህ!
32አምላካችን ሆይ፣ አንተ ታላቅ ነህ! አንተ ሃያል ነህ! አንተ አስደናቂ ነህ! አንተ እንደምታደርግልን በኪዳንህ ቃል እንደ ገባህልን በታማኝነት ትወደናለህ! ነገር ግን እኛ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ታላቅ ችግሮች አሉብን፡፡ መከራችን በፊትህ እንደ ቀላል አይታይ! ይህ በእኛ ነገስታት ልዑላን፣ ካህናት፣ ነቢያት፣ አባቶች እና በመላው ህዝብህ ላይ ከአሶር ነገስታት ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬ ደርሷል፡፡
33በቀጣኸን ጊዜ ሁሉ በጥፋታችን እንደተቀጣን እናውቃለን፡፡ እጅግ በድለናል፣ አንተ ግን በምህረትህ አይተኸናል እኛ ክፉ አድርገናል፡፡
34ንጉሶቻችን እና ሌሎች መሪዎች፣ ካህኖቻችን እና የእኛ አባቶች ህግህን አልጠበቁም፡፡ እነርሱ ትዕዛዛትን ወይም የሰጠኃቸውን ማስጠንቀቂያዎች አልሰሙም፡፡
35የራሳቸው ነገስታት በኖራቸው ጊዜ እንኳን፣ በዚህ በሰጠሃቸው ሰፊና ለም ምድር ለእነርሱ ባደረግካለቸው መልካም ነገሮች በተደሰቱ ጊዜ እንኳን፣ አንተን አላገለገሉህም ደግሞም ክፉ ማድረጋቸውን አላቆሙም፡፡
36ስለዚህ አሁን ምድሪቱ በምታበቅለው መልካም ነገሮች ሁሉ ደስ እንዲሰኙ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው በዚህች ምድር ባሮች ነን፡፡ እነሆ ዛሬም በዚህ ባሮች ነን!
37ስለበደልን ምድሪቱ የምታበቅለውን ነገሮች መብላት አልቻልንም፡፡ አሁን እኛን የሚገዙ ነገስታት በዚህ በሚበቅሉ ነገሮች ደስ እየተሰኙ ነው፡፡ እነርሱ ይገዙናል ከብቶቻችንንም ይወስዳሉ፡፡ እኛ እነርሱን የማገልገልና ደስ የሚያሰኛቸውን ነገሮች የማድረግ ግዴታ አለብን፡፡ በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እንገኛለን፡፡
38ከዚህ ሁሉ የተነሳ፣ እኛ የእስራኤል ሰዎች በጥቅልል ጽሁፍ ታላቅ ስምምነት እናደርጋለን፡፡ በጥቅልሉ ላይ የመሪዎቻችንን፣ የሌዋውያንን፣ የካህናትን ስሞች እንጽፍና ማህተም እናደርግበታለን፡፡”