መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ነህምያ 8

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ህዝቡ ሁሉ በውሃ በር አጠገብ በሚገኘው አደባባይ በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ የሚነገረውን መረዳት የሚችሉ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ልጆች በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ እነርሱም ህግጋቱንና ትዕዛዛቱን ይጠብቁ ዘንድ፣ ያህዌ ለእስራኤል ህዝብ መመሪያ አድርጎ የሰጠውን ሙሴ የፃፈውን የህግ ጥቅልል መጽሐፍ እንዲመያጣ ዕዝራን ጠየቁት፡፡
2በቤተ መቅደስ መስዋዕቶችን በማቅረብ እግዚአብሔርን የሚያገለግለው ዕዝራ፣ ለወንዶችና ለሴቶች እንዲሁም ለማናቸውም የሚነበበውን መረዳት ለሚችሉ ህጉን አውጥቶ በህዝቡ ሁሉ ፊት አነበበ፡፡ ይህንን በዚያ አመት በሰባተኛው ወር በወሩ በመጀመሪያው ቀን አደረገ፡፡
3ስለዚህም መጽሐፉን አውጥቶ ለህዝቡ አነበበ፡፡ ጠዋት ከማለዳ አንስቶ እስከ እኩለ ቀን ድረስ የህጉን መጽሐፍ አነበበ፡፡ ወንዶና ሴቶች እንዲሁም የሚያነበውን መረዳት የሚችሉ ሁሉ ሰሙት፡፡ ዕዝራ ከህጉ መጽሐፍ የሚያነበውን፣ ህዝቡ በታላቅ ፍላጎት አደመጠ፡፡
4ዕዝራ ለዚህ ተግባር በህዝቡ በተዘጋጀ ከፍ ያ የእንጨት መድረክ ላይ ቆመ፡፡ ከእርሱ በስተቀኝ መቲትያ፣ ሽማዕ፣ ዓናያ፣ ኦርዮ፣ ኬልቅያስ እና መዕሤያ ቆመው ነበር፡፡ በስተግራው በኩል ደግሞ ፈዳያ፣ ሚሳኤል፣ መልክያ፣ ሐሱም፣ ሐሽበዳ፣ ዘካርያስና ሜሱላም ቆመው ነበር፡፡
5ዕዝራ በመድረኩ ላይ ሁሉም ሰዎች ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ቆሞ ጥቅልሉን ተረተረው፣ እርሱ መጽሐፉን ሲከፍት ህዝቡ ሁሉ ተነስቶ ቆመ፡፡
6ከዚያም ዕዝራ ታላቁን አምላክ ያህዌን አመሰገነ፣ ህዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን አንስተው፣ “አሜን! አሜን!” አሉ፡፡ ከዚያም ሁሉም በግምባራቸው ወደ ምድር እየሰገዱ ያህዌን አመለኩ፡፡
7ኢያሱ፣ ባኒ፣ ሰራብያ፣ ያሚን፣ ዓቁብ፣ ሳባታይ፣ ሆዲያ፣ መዕሤያ፣ ቆሊጣስ፣ ዓዛርያስ፣ ዮዛባት፣ ሐናን እና ፌልያ ሁሉም ሌዋውያን ነበሩ፡፡ እነርሱም የሙሴን ህግጋት ትርጉም በዚያ ቆመው ለነበሩ ህዝቦች አብራሩ፡፡
8እንደዚሁም እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ህግ ከመጽሐፉ ጥቅልሎች አነበቡ፣ ደግም ወደ አረማይክ ቋንቋ እየተረጎሙ ህዝቡ ሊረዱት እንዲችሉ ትርጉሙን ግልጽ አደረጉ፡፡
9ከዚያ አገረ ገዥው ነህምያ እና ጸሓፊውና ካህኑ ዕዝራ፣ እንዲሁም የተነበበውን ለህዝቡ ይተረጉሙ የነበሩ ሌዋውያን፣ እንዲህ አሏቸው፣ “ያህዌ አምላካችሁ ይህን ቀን ከሌሎች ቀናት ለይቶታል፡፡ ስለዚህ በዚህ ቀን አትዘኑ ወይም አታልቅሱ!” ይህን የተናገሩት፣ ዕዝራ ህጉን ሲያነብ፤ የሚሰሙት ሁሉ ያለቅሱ ስለነበር ነው፡፡
10ከዚያም ነህምያ እንደዚህ አላቸው፣ “አሁን ወደየቤታችሁ ሄዳችሁ መልካም ምግብ ተመገቡ ደስ የሚያሰኝ ጣፋጭ መጠጥም ጠጡ፡፡ ከምትበሉትና ከምትጠጡት የሚበሉትና የሚጠጡት ለሌላቸው አካፍሉ፡፡ ይህ ቀን፣ ጌታችንን ለማምለክ የተለየ ቀን ነው፡፡ ሀዘን አይሙላባችሁ! ያህዌ የሚሰጣችሁ ደስታ ብርቱ ያደርጋችኋል፡፡”
11ሌዋውያኑም ህዝቡን “ዝም በሉ አታልቅሱ፣ ይህ ቀን ለያህዌ የተለየ ቀን ነው፡፡ አትዘኑ!” በማለት ፀጥ አሰኙ፡፡
12ስለዚህም ህዝቡ ተነስቶ ሄደ፤ በሉም ጠጡም፣ እንዲሁም ምንም ለሌላቸው ከምግባቸው አካፈሉ፡፡ የተነበባላቸውን ቃላት ትርጉሙን ስለተረዱ በጣም ደስተኞች ነበሩ፡፡
13በማግስቱ፣ የየቤተሰቡ አባወራዎች እና ካህናቱ እንዲሁም ሌዋውያኑ የህጉን ቃላት ይበልጥ ለመረዳት በአንድነት ወደ ዕዝራ መጡ፡፡
14አያቶቻቸው በበረሃ ሲጓዙ በዳሶች ውስጥ እንደኖሩ ያስታውሱ ዘንድ፣ በእነዚያ ወራት ሁሉ የእስራኤል ህዝብ እንዴት በጊዜያዊ ዳሶች ውስጥ መኖር እንደሚገባቸው ያህዌ ለሙሴ የሰጠውን ተዕዛዝ በህጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፡፡
15እንደዚሁም ህዝቡ ወደ ኮረብቶች ሄዶ፤ ከወይራ ዛፎች ቅርንጫፎችን፣ ከበረሃ ወይራ ዛፎችና ከባርሰነት ዛፎች፣ ከዘንባባ ዛፎችና ሰፊ ጥላ ከሚሰጡ ዛፎች ዝንጣፊዎችን እየቆረጡ እንዲያመጡና በኢየሩሳሌምና በሌሎች ከተሞች ማወጅ እንዳለባቸው ተረድተዋል፡፡ ሙሴ እንደፃፈው፣ በበዓላቱ ወቅቶች ለመኖሪያነት የሚገለገሉባቸውን እነዚህን ዳሶች ከእነዚህ ዛፎች ቅርንጫፎች ማበጀት አለባቸው፡፡
16ስለዚህም ህዝቡ ከከተማ ወጥቶ ቅርንጫፎችን ቆርጦ ዳሶችን ለመስራት ተጠቀመባቸው፡፡ ዳሶችንም በየቤቶቻቸው ሰገነቶችች በየአደባባዮቻቸው፣ በቤተ መቅደስ አደባባዮች፣ እና በውሃ በር አጠገብ በሚገኘው አደባባይና በኤፍሬም መግቢያ ሰሩ፡፡
17ከባቢሎን የተመለሱ እስራኤላዊያን ሁሉ ዳሶችን ገንብተው ለአንድ ሳምንት ኖሩባቸው፡፡ እስራኤላዊያን ያንን በዓል ከኢያሱ ዘመን አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ እንዲህ አላከበሩም፡፡ ህዝቡ በጣም ተደስቶ ነበር፡፡
18ዕዝራ በዚያን ሳምንት በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ህግ ለህዝቡ ያነብ ነበር፡፡ ከዚያ በስምንተኛው ቀን፣ ድንጋጌውን ተከትለው ህዝቡ እንዲሰበሰብ አደረጉ፣ ይህም የበዓሉ ፍጻሜ ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።