መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (Door43 ULB 7.2, 2020)

ነህምያ 6

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ያንብቡ። የDivine Threads ጥናት በቅርቡ ይቀርባል።

1ምንም እንኳን እስከ አሁን በሮቹን በመግቢያዎቹ ላይ ገና ባንገጥምም፣ የቅጥሩን ሥራ መጨረሳችንንና ያልተጠገነ የፈረሰ ስፍራ አለመኖሩን ሰንበላጥ፣ ጦቢያ፣ ጌሳምና ሌሎች ጠላቶቻችን ሰሙ፡፡
2ስለዚህ ሰንበላጥና ጌሳም እንዲህ የሚል መልዕክት ወደ እኔ ላኩ፣ “ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን በሚገኘው ኦኖ በሚባለው ሜዳ መጥተህ እንነጋገር፡፡” ነገር ግን ይህን ያሉት እኔን ለመጉዳት አስበው እንደነበር ግልጽ ነው፡፡
3ስለዚህም እንዲህ ብለው እንዲነግሯቸው መልዕክተኞችን ላክሁ፣ “ከፍ ያለ ስራ እየሰራሁ ነው፣ እናም ወደዚያ ልሄድ አልችልም፡፡ እኔ ከእናንተ ጋር ለመነጋገር ወደዚያ በመሄድ ይህ ስራ መስተጓጎል አይኖርበትም፡፡
4እነርሱ ይህንኑ መልዕክት አራት ጊዜ ወደ እኔ ላኩ፣ እኔም በእያንዳንዱ ወቅት ተመሳሳይ መልስ ሰጠኋቸው፡፡
5ከዚያም ሰንበላጥ አምስተኛውን መልዕክት አስይዞ አንዱን አገልጋዩን ወደ እኔ ላከ፡፡ ይህኛው መልዕክት በጽሁፍ ነበር፣ በእርግጥ ማህተም ያልተደረገበትና ያልታሸገ ደብዳቤ ነበር፡፡
6በመልዕክቱ የተጻፈው ይህ ነበር፡ “በባቢሎን ንጉስ ላይ አመጽ ለማስነሳትና አንተም የእስራኤል ንጉስ ለመሆን አቅደህ አንተና ሌሎች አይሁዶች ቅጥሩን እንደገና እየገነባችሁ እንደሆነ በአቅራቢያ ባሉ አገሮች ያሉ አንዳንድ ሰዎች ወሬ ሰምተዋል፡፡ እውነቱ ይህ መሆኑን ጌሳም ነግሮናል፡፡
7ደግሞም ሰዎች፣ አንተ ነህምያ፣ አሁን የአይሁድ ንጉስ መሆንህን እንዲያውጁ ነቢያትን መሾምህን እየተናሩ ነው፡፡ ንጉስ አርጤክስስ በእርግጥ ይህን ወሬ መስማቱ አይቀርም፣ ያን ጊዜ ትልቅ ችግር ላይ ትወድቃለህ፡፡ ስለዚህ ተገናኝተን በዚህ ጉዳይ ላይ መነጋገር እንደሚኖርብን አሳስባለሁ፡፡”
8ያን መልዕክት ካነበብኩ በኋላ መልዕክተኛው ወደ ሰንበላጥ ይህን መልዕክት መልሶ እንዲያደርስ ላክሁ፣ “ከምትናገረው ውስጥ አንዱም እውነት አይደለም፡፡ ይህን የምትለው ከገዛ ልብህ ፈጥረህ ነው፡፡”
9ይህንን የምለው እነርሱ እኛን ለማስፈራራት እየሞከሩ እንደነበር ስለማወቅ ነው፣ ስለዚህም እንዲህ ብለው ያስባሉ፣ “ከዚህ በኋላ ቅጥሩን ለመስራት ፍጹም ተስፋ ይቆርጣሉ፣ ስራውም በፍጹም ከፍጻሜ አይደርስም፡፡” ስለዚህም እኔ፣ “አምላኬ ሆይ፣ ብርታትን ስጠኝ፡፡” ስል ጸለይኩ፡፡
10አንድ ዕለት የመሔጣብኤል የልጅ ልጅ፣ የድልያ ልጅ፣ ከሆነው ከሸማያ ጋር ለመነጋገር ሄድኩ፡፡ ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ወደ ቤቱ ሄድኩ፡፡ ከቤቱ እንዳይወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር፡፡ እርሱም እንዲህ አለኝ፣ “አንተና እኔ ከቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍሎች ወደ አንዱ መግባትና በሮቹን መቆለፍ አለብን፡፡ ዛሬ ምሽት ሊገድሉህ ይመጣሉ፡፡”
11እኔም እንዲህ ስል መለስኩለት፣ “እኔ እንዲያ ያለ ሰው አይደለሁም! ህይወቴን ለማትረፍ ራሴን ቤተመቅደስ ውስጥ ሸሽቼ ገብቼ አልደብቅም! አይ፣ ያንን አላደርግም!”
12የተናገረውን አሰላሰልኩ፣ ሸማያ እግዚአብሔር ያላለውን እንደነገረኝ አወቅሁ፡፡ ጦቢያ እና ሰንበላጥ ቀጥረውት ነበር፡፡
13እንዲያስፈራራኝ እነርሱ ቀጥረውት ነበር፡፡ እነርሱ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንዳልጠብቅ በመቅደስ ውስጥ በመደበቅ እንድበድል ይፈልጉ ነበር፡፡ ያንን ባደርግ፣ ስሜን ያጠፉና ከዚያም ያዋርዱኛል፡፡
14ስለዚህም እንዲህ ስል ጸለይኩ “አምላኬ ሆይ፣ ጦቢያና ሰንበላጥ ያደረጉትን አትርሳ፡፡ ነቢይቱ ኖዓድያ እና ሌሎች ነቢያት ሊያስፈራሩን የሞከሩትን አትርሳ፡፡”
15በኤሉል ወር በወሩ ሃያ አምስተኛው ቀን የቅጥሩን ጥገና አጠናቀቅን፡፡ ጠቅላላውን ስራ በሀምሳ ሁለት ቀናት አጠናቀቅን፡፡
16በአቅራቢያችን በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ጠላቶቻችን ይህንን ሲሰሙ፣ በጣም ፈሩ፣ ዕፍረትም ተሰማቸው ምክንያቱም ይህን ሥራ እንድናጠናቅቅ የረዳን እግዚአብሔር እንደሆነ አውቀው ነበር፡፡
17በዚህ ጊዜ ውስጥ፣ የአይሁድ መሪዎች ብዙ መልዕክቶችን ወደ ጦቢያ ይልኩ ነበር፣ ጦቢያም መልሶ መልዕክቶችን ወደ እነርሱ ይልክ ነበር፡፡
18በይሁዳ ያሉ ብዙ ሰዎች ታማኝታቸውን በመሀላ ለጦቢያ አረጋግጠውለት ነበር፡፡ እርሱም የኤራ ልጅ የሴኬንያ አማት ሲሆን፣ የጦቢያ ወንድ ልጅ የቤሪክያን ልጅ የሆሐና የሚሹ ሀላምን ሴት ልጅ አግብቶ ነበር፡፡
19ሰዎች ብዙ ጊዜ እኔ ባለሁበት ጦቢያ ስለ ሰራቸው መልካም ስራዎች ይናገሩና፣ ከዚያ እኔ የተናገርኩትን እያንዳንዱን ነገር ይነግሩታል፡፡ ስለዚህም ጦቢያ እኔን ለማስፈረራት በርካታ ደብዳቤዎችን ወደ እኔ ይልክልኝ ነበር፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ — Amharic Unlocked Literal Bible (am_ulb), version 7.2 (2020) — Door43 World Missions Community contributors. Original work available at door43.org. Source: pinned 2020 USFM source. License: Creative Commons Attribution-ShareAlike 4.0 (CC BY-SA 4.0). Changes to presentation: USFM verse-only rendering, layout and line-break flattening, omission of Scripture footnotes, editorial text and source-empty verse markers; original combined verse ranges are preserved. This Scripture presentation is offered under CC BY-SA 4.0, separately from independently authored Divine Threads study content. No endorsement by Door43 is implied. የDivine Threads ጥናቶች በአማርኛ በቅርቡ ይቀርባሉ።