1ቆይቶ፣ ሌሎቹ አንዳንድ አይሁዶች በሚያደርጉት ብዙዎቹ ወንዶችና ሚስቶቻቸው ፍትህ ለማግኘት ጮኹ፡፡
2አንዳንዶቹ እንዲህ አሉ፣ “እኛ ብዙ ልጆች አሉን፡፡ በልተን ለማደርና በህይወት ለመቆየት እንኳን ብዙ እህል ያስፈልገናል፡፡”
3ሌሎቹ ደግሞ እንዲህ አሉ፣ “በዚህ የረሃብ ወቅት የምንበላው እህል ለማግኘት የእርሻ መሬታችንን፣ የወይን ተክላችንንና ቤቶቻችንን ማስያዝ ግድ ሆኖብናል፡፡
4ሌሎቹም እንዲህ አሉ፣ “ለእርሻ መሬቶቻችንና ለወይን ተክላችን ለንጉሱ ግብር ለመክፈል ገንዘብ መበደር የግድ ሆኖብናል፡፡
5እኛም እንደ ሌሎቹ አይሁዶች አይሁዳውያን ነን፡፡ የእነርሱ ልጆች ለእነርሱ ጠቃሚ እንደሆኑ ሁሉ፤ የእኛም ልጆች ለእኛ እንደዚያው ናቸው፡፡ ነገር ግን መክፈል የሚገባንን ለመክፈል ስንል ልጆቻችንን ለባርነት ለመሸጥ ተገደናል፡፡ አንዳንድ ሴት ልጆቻችንን አሁን ለባርነት ሸጠናል፡፡ የእርሻ መሬቶቻችንና የወይን ተክሎቻችን ከእኛ ተወስደዋል፣ ስለዚህም መክፈል ያለብንን ገንዘብ ለመክፈል ገንዘቡ የለንም፡፡”
6እነዚህን እነርሱ የተጨነቁባቸውን ነገሮች በሰማሁ ጊዜ በጣም ተቆጣሁ፡፡
7ስለዚህም ማድረግ ያለብኝን ነገር አሰብ፡፡ ለመሪዎችና ለሹማምንቱ እንዲህ አልኳቸው፣ “ገንዘብ ሲበደሯችሁ የገዛ ዘመዶቻችሁን ወለድ ታስከፍላላችሁ፡፡ ይህ ልክ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ!” ከዚያም ክስ እንዲያቀርቡባችሁ ብዙ ሰዎችን በእነርሱ ላይ ሰብስቤ ጠራሁ፡፡
8እንዲህም አልኳቸው፣ “አንዳንድ አይሁዳዊ ወገኖቻችን የአህዛብ ባሪያዎች ለመሆን ራሳቸውን ለመሸጥ ተገደው ነበር፡፡ የቻልነውን ያህል፣ መልሰን ገዝተናቸው ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን እናንተ የገዛ ወገኖችሁን እንኳን እየሸጣችሁ ነው፤ ይኸውም የገዛ ወገኖቻቸው ወደ ሆኑ አይሁዶች ተመልሰው ይሸጡ ዘንድ ነው!” ይህን ስናገራቸው፣ ምላሽ አልሰጡም፡፡ አንዲት ቃል እንኳን አልመለሱም፡፡
9ከዚያ እንዲህ አልኳቸው፣ “የምታደርጉት ነገር ክፉ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ልትታዘዙና ትክክል የሆነውን ልታደርጉ አይገባችሁምን? ይህን ብታደርጉ፣ ጠላቶቻችን በንቀት እንዳያዩን ማድረግ ትችላላችሁ፡፡
10እኔና አይሁዳዊ ወገኖቼ እንዲሁም አገልጋዮቼ ለህዝቡ ገንዘብና እህል አበደርን፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ከእነዚህ ብድሮች በአንዱም ወለድ መቀበል እናቁም፡፡
11እንደዚሁም፣ የወሰዳችሁባቸውን የእርሻ መሬቶቻቸውን፣ የወይን ስፍራቸውን፣ የወይራ ዛፍ ቦታቸውን እንዲሁም ቤቶቻቸውን ልትመልሱላቸው ይገባል፡፡ እንደዚሁም ገንዘብ፣ እህል፣ ወይን፣ እና የወይራ ዘይት ሲበደሯችሁ ያስከፈላችኋቸውን ወለዶች ልትመልሱላቸው ይገባል፡፡ ይህን ዛሬውን ልታደርጉ ይገባል!”
12መሪዎች እንዲህ ሲሉ መለሱ፣ “ያልከንን እናደርጋለን፡፡ እንዲሰጡን ያስገደድናቸውን ነገር ሁሉ እንመልስላቸዋለን፣ ደግም ሌላ ተጨማሪ ነገር እንዲሰጡን አንጠይቅም፡፡” ከዚያ ካህናቱን ሰበሰብኩ፣ እናም ቃል የገቡትን እንዲያደርጉት አስማልኳቸው፡፡
13የክህነት ልብሴን እጥፋት አራግፌ እንዲህ አልኳቸው፣ “ልታደርጉት አሁን ቃል የገባችሁትን ባታደርጉ፣ እኔ ልብሴን እንዳራገፍኩ እግዚአብሔር ያራግፋችኋል፡፡” እነርሱም “አሜን እንዳልከው ይሁን!” ሲሉ መለሱ፤ ደግሞም ያህዌን አወደሱ፡፡ ከዚያ ለማድረግ ቃል የገቡትን አደረጉ፡፡
14አርጤክስስ የፋርስ ንጉስ በነበረበት በሀያኛው ዓመት የይሁዳ ገዥ ሆኜ ተሹሜ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከ ሰላሳ ሁለተኛው የንግስናው አመት ድረስ እኔም ሆንኩ የእኔ ሹማምንት ገዥ በመሆኔ ለቀለብ የተፈቀደልኝን ገንዘብ አልተቀበልንም፡፡
15ከእኔ አስቀድሞ ገዥ የነበሩ ሰዎች በየቀኑ አርባ የብር ሳንቲሞች ለምግብና ለወይን በመጠየቅ በህዝቡ ላይ ሸክም አክብደውበት ነበር፡፡ አገልጋዮቻቸው ጭምር ህዝቡን ይጨቁኑ ነበር፡፡ እኔ ግን ያን አላደረግኩም፣ ምክንያቱም ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት እፈልግ ነበር፡፡
16በዚህ ቅጥር ላይ መስራቴንም ቀጠልኩ፣ እኛም ከህዝቡ ምንም መሬት አልገዛንም፡፡ ለእኔ የሚሰሩት ሁሉ በቅጥሩ ስራ ተባበሩን፡፡
17እንዲሁም፣ በየዕለቱ ከገበታችን አይሁዶችንና ሹማምንቱን፣ አንድ መቶ ሀምሳ ሰዎችን፣ እና በዙሪያችን ካሉ አገሮች የመጡ ጎብኚዎችን እንመግብ ነበር፡፡
18በየቀኑ አገልጋዮቼ አንድ በሬ፣ ስድስት ሙክቶች እና የዶሮዎች ስጋ እንዲያቀርቡ አደርግ ነበር፡፡ በየአስሩ ቀን ብዙ የሆነ አዲስ ወይን ጠጅ አቀርብላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ህዝቡ እጅግ ብዙ ግብር በመክፈል ጫና እንደሚበዛበት አውቅ ነበር፣ ስለዚህም እንደ አገረ ገዥ የተፈቀደልኝን ገንዘብ እንኳን አልቀበልም ነበር፡፡
19አምላኬ፣ አስበኝ፣ እናም ለዚህ ህዝብ ላደረግኩት ሽልማት ስጠኝ፡፡